Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ከ380.6 ሚሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉ የቡና ነጋዴዎች ተከሰሱ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የተሟላ የቢሮ ዕቃዎችና ወደ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች ሳይኖሯቸው በአንድ ጉዳይ አስፈጻሚ አማካይነት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር የቡና ላኪነት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ያገኙ ቡና ላኪዎች፣ ከ380.6 ሚሊዮን ብር በላይ ወይም ከ19.8 ሚሊዮን ዶላር በላይ መንግሥትን የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉ ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

  አቶ ሁምኔሳ አብደታና አቶ ታምራት ኃይሌ የተባሉት ተከሳሾች በግብርና ሚኒስቴር የላኪነት ብቃት ማረጋገጫ ቢሮ ኃላፊዎች መሆናቸውን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ አቶ ዳንኤል ይህደጎ የተባሉት ጉዳይ አስፈጻሚ፣ አንድ ተመሳሳይ ወንበርና ጠረጴዛ ለአራት የቡና ላኪነት ብቃት ማረጋገጫ ጠያቂዎች ማለትም አቶ በርሄ ገብረ መድኅን፣ አቶ አብዲልአዲ ሰባርቃዳ (ያልተያዙ)፣ አቶ አብዱራህማን ተመስገን (ያልተያዙ)፣ አቶ ብርሃኑ አለበል (ያልተያዙ) የሚል ተመሳሳይ የሠራተኞች የቅጥር ውል ሲቀርብላቸው ድርጊቱ ሕገወጥ በመሆኑ ‹‹ሊሰጥ አይገባም›› ማለት ሲገባቸው፣ ማረጋገጫውን መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

  በመሆኑም ነጋዴዎቹ በተሰጣቸው የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ኤክስፖርት የሚደረግ የቡና ግዢ ውል ተፈራርመው 1,696.69 ቶን (16,966.9 ኩንታል) ቡና የገዙ ቢሆንም፣ ቡናውን ኤክስፖርት ከማድረግ ይልቅ በመሰወራቸው 6,672,904 ዶላር ወይም 125,639,001 ብር የውጭ ምንዛሪ መንግሥት እንዲያጣ ማድረጋቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

  አቶ በርሄና አቶ ኪዳኔ ገብረ ሳሙኤል (ያልተያዙ) ዳንኤል ይህደጎ የተባለውን ጉዳይ አስፈጻሚ ንግድ ፈቃድ እንዲያወጣ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተሰጠ የሚመስል ሐሰተኛ ቀበሌ መታወቂያ እንዲያወጣ በማድረግ፣ ውክልና በመስጠትና የተለያዩ ሐሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ ከግብርና ሚኒስቴር የቡና ላኪነት የብቃት ማረጋገጫና የንግድ ፈቃድ ማውጣቱን ክሱ ይጠቁማል፡፡

  በሐሰተኛ ሰነድ የብቃት ማረጋገጫና ንግድ ፈቃድ የተሰጠው ጉዳይ አስፈጻሚው አቶ ዳንኤል፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 1,087.03 ቶን (10870.3 ኩንታል) ቡና ገዝቶ ኤክስፖርት ሳያደርግ በመሸሸጉ፣ መንግሥት 3,497,104 ዶላር ወይም 69,346,731 ብር የውጭ ምንዛሪ እንዲያጣ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

  ተከሳሾቹ በቅደም ተከተል ሁለቱ የመንግሥት ሠራተኞች አቶ ሁምኔሳ አብደታና አቶ ታምራት ኃይሌ ናቸው፡፡ ነጋዴዎቹ አቶ በርሄ ገብረ መድኅን፣ አቶ አብዲልአዲ ባርቀዳ (ያልተያዙ)፣ አቶ አብዱራህማን ተመስገን (ያልተያዙ)፣ አቶ ድራር ፍሰሐዬ (ያልተያዙ)፣ አቶ ብርሃኑ አለበል (ያልተያዙ) እና አቶ ነፃነት ተፈራ (ያልተያዙ) ናቸው፡፡

  አቶ አብዲልአዲ፣ አቶ አብዱራህማንና አቶ ድራር የተባሉት ተከሳሾችም በተመሳሳይ ሁኔታ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 1,905.3 ቶን (19,053.6 ኩንታል) ኤክስፖርት የሚደረግ ቡና የገዙ ቢሆንም፣ ሳይልኩ በመሸሸጋቸው 6,502,895 ዶላር ወይም 129,407,612 ብር መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እንዲያጣ ማድረጋቸውን በክሱ በዝርዝር ተገልጿል፡፡

  አቶ በርሄና አቶ አብዲልአዲ የተባሉትም ነጋዴዎች 445.4 ቶን (4,454 ኩንታል) ኤክስፖርት የሚደረግ ቡና ገዝተው ሳይልኩ በማስቀረታቸው መንግሥት 1,58,349 ዶላር ወይም 27,753,637 የውጭ ምንዛሪ እንዲያጣ ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

  ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 362.44 ቶን (3624.4 ኩንታል) ኤክስፖርት የሚደረግ ቡና ገዝተው የነበሩት አቶ አብዲልአዲና አቶ ብርሃኑ ሳይልኩ በመቅረታቸው፣ መንግሥት 1,538,174 ዶላር ወይም 31,332,609 ብር የውጭ ምንዛሪ እንዲያጣ ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡

  ተደጋጋሚ ክስ የተመሠረተባቸው አቶ አብዲልአዲና አቶ ነፃነት ተፈራም በተመሳሳይ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 30.46 ቶን (304.6 ኩንታል) ቡና የገዙ ቢሆንም፣ ወደ ውጭ ሳይልኩ በመቅረታቸው መንግሥት 129,275 ዶላር ወይም 2,206,023 ብር የውጭ ምንዛሪ እንዲያጣ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ገልጿል፡፡ በድምሩ መንግሥት 19,848,701 ዶላር ወይም 380,685,613 ብር የውጭ ምንዛሪ እንዲያጣ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስታውቋል፡፡

  በችሎት የተገኙት ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡና ያልተያዙት ተከሳሾችን ፖሊስ አፈላልጎ በመያዝ እንዲያቀርብ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች