Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የ400 ሆቴሎችን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው አስገዳጅ ምደባና የሆቴሎች ሥጋት

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ሆቴሎችን በኮከብ ደረጃ በመመደብ ደረጃ ለመስጠት ሲሞክር አራት ዓመታት አሳልፏል፡፡ በ2003 ዓ.ም. ያልተሳኩ ሙከራዎች ማድረጉም አይዘነጋም፡፡ ከዘጠኝ ወራት በፊት ግን አንድ ስምምነት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ከሚታቀፉ ኤጀንሲዎች አንዱ የሆነው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት፣ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ጣይብ ሪፋይ ኢትዮጵያን ጎብኝተው ነበር፡፡ እግረ መንገዳቸውንም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር ጋር የፈረሙት የመግባቢያ ስምምነት እ.ኤ.አ. እስከ 2017 የሚቆይና በሁለቱ አካላት መካከል በቱሪዝም መስክ ትብብር እንደሚደረግ ይፋ ያደረገ ነበር፡፡

  በመሆኑም መንግሥት ሲያዘጋጀው የነበረውን የኮከብ ደረጃ የሆቴሎች ምደባ መስፈርትን ሲያስገመግም፣ አዲስ መስፈርት ማዘጋጀቱ እንደሚሻል ታመነበትና በዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባለሙያዎች ጥናት የተደረገበት ሰነድ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቶ በዚህ ወር ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

  የሆቴሎች የኮከብ ደረጃን ለመለካት በወጣው መስፈርት መሠረት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር 400 ሆቴሎችን መርጦ ለዓለም ቱሪዝም ድርጅት መዛኞች ዝርዝራቸውን ሰጥቷል፡፡ ከሃያ ዓመታት በላይ የምዘና ልምድ እንዳላቸውና ከ30 በላይ ሆቴሎችን እንደመዘኑ የተነገረላቸው መዛኞቹም አዲስ አበባ ከሚገኙት መካከል 132 ሆቴሎችን በማስቀደም ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ እስካሁንም ከ40 በላይ ሆቴሎችን እንደመዘኑ ይታመናል፡፡ እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ 39 ሆቴሎች የደረጃ ምዝና እንደተካሄደባቸው ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል፡፡

  በ12 ዋና ዋና የመመዘኛ ነጥቦች የተከፋፈለውን የሆቴሎች ምደባ መስፈርት፣ ከሆቴሎች ውጫዊ ገጽታ ይጀምራል፡፡ የሕንፃው ሁኔታ አዲስ ወይም አሮጌ ሆኖ ስንጥቃትና መነቃቃት የሌለው፣ ውበቱና ማራኪነቱ፣ አጸድና ቅጥረ ግቢው ወዘተ ውጫዊ የሆቴል ገጽታዎችን የሚገመግሙ መስፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡ መኝታ ክፍሎች ያላቸው ስፋት፣ መብራታቸው፣ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ አልጋ አነጣጠፍ፣ ግድግዳና ጣሪያ የመሳሰሉት ይገመገማሉ፡፡ መፀዳጃና መታጠቢያ ቤቶች፣ መመገቢያና መዝናኛ ሥፍራዎች፣ ወጥ ቤት፣ የእሳት አደጋ፣ የድንገተኛ አደጋ መከላከያ ዘዴዎች፣ ፅዳትና ጥገና የመሳሰሉትን ያካተተው መመዘኛ፣ ከአምስት ኮከብ በላይ ዴሉክስ የሚባሉት ሆቴሎች በመስፈርቱ ከ90 ከመቶ በላይ የሚያስመዘግቡት መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡

  ከ80 እስከ 89 ከመቶ ያመጡ፣ ባለአምስት ኮከብ፣ ከ70 እስከ 79 ያመጡት ባለአራት ኮከብ፣ ከ60 እስከ 69 ያመጡት ባለሦስት ኮከብ፣ ከ50 እስከ 59 ያመጡት ባለሁለት ኮከብ፣ ከ30 እስከ 49 ያመጡት ባለአንድ ኮከብ ሆቴሎች ተብለው ሲመደቡ፣ ከ30 ከመቶ በታች ውጤት የሚያገኙ ግን መሠረታዊ ሆቴሎች በሚለው ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ ተብሏል፡፡

  የሆቴል ምደባ በጅማሮው ስኬታማ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ ይህንኑ በማስመልከት የክልል ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ሰዎችንና የቱሪዝም ባለሙያዎችን በመጥራት በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ለሦስት ቀናት ውይይት አካሒዷል፡፡

  በውይይቱ ወቅት ለሆቴል ምዘና ሥራው ቅደመ ዕውቅና የሚሰጡ አራት የአዲስ አበባ ተቋማትም ስለ ሥራዎቻቸው ገለጻ አቅርበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ ቁጥጥርና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣንና የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል ከሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ጋር በተገናኘ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አሳውቀዋል፡፡ የባለኮከብ ሆቴሎች ለደረጃ ከመመዘናቸው በፊት ከእነዚህ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

  በመሆኑም የአዲስ አበባ ምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በሆቴሎችና በሌሎች ከምግብ አቅርቦት ጋር ተያያዥ ሥራ በሚሠሩ 27 ሺሕ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል፡፡ የባለሥልጣኑ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ በይፋ እንዳስታወቁት፣ በአዲስ አበባ ለምዘና ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሳኒቴሽንና ኃይጅን ቁጥጥር ከተደረገባቸው 45 ሆቴሎች ውስጥ፣ ሦስቱ ማሟላት ከሚገባቸው ዝቅተኛው መስፈርት በታች አስመዝግበዋል፡፡ አምስቱ ፈቃደኛም ዝግጁም ሳይሆኑ ቀርተው፣ ብዛታቸው ያልተገለጹ ሆቴሎችን ባለሥልጣኑ ሊያገኛቸው አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢና የግል ንጽህና አጠባበቃቸው ላይ ግምገማ የሚደረግባቸው ሆቴሎች ከማብሰያ ቤትና ከምግብ ግብዓቶች ክምችት፣ ከመጠቀሚያ ዕቃዎች ንፅህና እስከ መኝታ ቤት፣ ከሕንፃ ንፅህና እስከ ሠራተኞች ጤና አጠባበቅ ባሉትና በሌሎችም ላይ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል፡፡

  የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በበኩሉ የሆቴል ባለሙያዎች በተለይም ከምግብ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች በየጊዜው የጤና ክትትልና የጤና ምርመራ ማድረጋቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ መያዛቸውን የሚያመላክቱ ሰነዶች መሟላታቸውን እንደሚከታተል፣ ሠራተኞች የጤና መስፈርቶችን አሟልተው ሲገኙም ዕውቅና እንደሚሰጥ ይፋ አድርጓል፡፡

  የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲም ሆቴሎች ለኮከብ ደረጃ ከመመዘናቸው አስቀድመው የእሳት አደጋ ቢነሳ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የአደጋ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች፣ የእሳት አደጋ መከላከለያ ሥርዓቶችና አደጋ ጊዜ ማምለጫዎች በሆቴሎች መሟላታቸውን እያረጋገጠ ዕውቅና እየሰጠ ይገኛል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከልም በሙያቸው ከሆቴል ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች እየፈተነ ማረጋገጫ እየሰጠ ሲሆን፣ ከ132 ሆቴሎች ውስጥ በ128 ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች ላይ ምዘና መደረጉን፣ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ አሸብር ተክሉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በ43 ሆቴሎች ውስጥ ከሚሠሩ 1906 ሰዎች መካከል 1629 ብቁ መባላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

  አቶ አሸብር እንደገለጹት ትልልቅ የሚባሉት ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን ለማስመዘን ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም ነበር፡፡ በሒደት ግን ሸራተን አዲስ 56 ሠራተኞቹን፣ ሒልተን ሆቴል ደግሞ 34 ሠራተኞችን ለሙያ ብቃት ማስመዘናቸው ታውቋል፡፡ ሆቴሎች ካሏቸው ሠራተኞች መካከል ቢያንስ 75 ከመቶው የሙያ ብቃታቸው መረጋገጥ እንዳለበት አቶ አሸብር አስታውቀው፣ በርካታ ሆቴሎች ግን ሠራተኞቻቸውን ለማስመዘን ፈቃደኛ ሆነው አለመገኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የሆቴሎቹ ሥጋት ብቁ ያልሆኑ ሠራተኞቻቸውን ዕጣ ፈንታ የሚመለከት ሲሆን፣ አቶ አሸብር እንደሚሉት ግን በድጋሚ በማስፈተን ሠራተኞችን ብቁ ማድረግ የሆቴሎች ግዴታ ነው፡፡

  እንዲህ ያሉ ቅደመ መስፈርቶችን አሟልተው የሚገኙ ሆቴሎች ናቸው ለኮከብ ደረጃ ምዘና የሚደረግባቸው፡፡ ሆኖም ባለሙያዎችም ባለሆቴሎችም እኩል ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ አቶ አሸብር እንደሚገልጹት፣ ብዙ ዘግይቶ የማግባባትና ጥቅሙ ለራሳቸው እንደሆነ በመወትወት ለምዘና እንዲመጡ እየተደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማኅበርን የወከሉት አቶ ታዬ አለማየሁ በበኩላቸው፣ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ ማሠልጠኛ ተቋምትም ጭምር ምዘና ሊካሄድባቸው፣ ሥርዓተ ትምህርታቸው ሊታይ እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ አለልኝ አስቻለ፣ በአዲስ አበባ የሆቴልና መስተንግዶ ቢዝነስ ዋና ችግሮች በሚል ርዕስ ባጠኑት ጥናት፣ ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ሆቴሎች አሠራር ድረስ ባለው ሒደት አዲስ አበባ ውስጥ የሚሠሩ ሆቴሎች በርካታ ችግሮች እንደሚታዩባቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ከሆቴሎቹ ባሻገር በዘርፉ የሚመለከታቸውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ይተቻሉ፡፡ ከንፅህና ጉድለት፣ ከአሠራር ችግሮች፣ ከሙያ ብቃት ማነስና ከሌሎችም ችግሮች ጋር በተያያዘ በጥናት አገኘሁ ያሏቸውን ነጥቦች ጠቅሰዋል፡፡

  ይህም ቢባል ግን የሆቴሎችን ደረጃ ማውጣት ግዴታ ያደረገው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከሻይ ቤት፣ ከመንደር ሥጋ ቤት እስከ ትልልቅ ሆቴሎች ድረስ ያለውን የአሠራር ሥርዓት እንደሚቆጣጠርና ለአሁኑ ግን የኮከብ ደረጃ ያላቸውን ሆቴሎች ለመመዘን ቅድሚያ መስጠቱን ሚኒስትሩ አሚን አብዱልቃድር ይፋ አድርገዋል፡፡

  የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ምክትል ሰብሳቢና የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዜናዊ መስፍን ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ሆቴሎቹ ለመመዘን ፍላጎት እንዳላቸውና ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተረድተዋል፡፡ ለውውይት ባቀረቡት ጽሑፍም ሆቴሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚሰጠው የኮከብ ደረጃ ሊያስገኝላቸው የሚችለውን ጥቅም በአኃዝ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡ አንድ ሆቴል መሠረታዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ለውጦችን ቢያደርግ፣ ጠቅላላ ገቢውን እስከ 15 ከመቶ ማሳደግ እንደሚችል፣ የኮከብ ደረጃ ያገኘ ሆቴል እጥፍ የገቢ ጭማሪ ሊያገኝ የሚችልባቸውን የአሠራር ሥልቶችንም ዘርዝርዋል፡፡

  የሆቴሎች ሥጋት

  የብቃት ማረጋገጫ ከሚሰጡ ተቋማት፣ ከክልሎችና የምዘና ሒደቱን ከሚመሩት ባለሙያዎች እንደተሰማው ሆቴሎች ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ ከምዘናው በኋላ የሚኖራቸው ህልውና የሥጋት ውጥረት ውስጥ እንደከተታቸው ሲገለጽ ነበር፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የደብረ ዘይት ከተማ ሆቴል ቤት ኃላፊዎች ሥጋት ከአዲስ አበባዎቹም የባሰ ሆኗል፡፡ ‹‹በቂ ጊዜ አልተሰጠንም፡፡ በሰኔ ወር ልንመዘን እንዴት በሚያዝያ ይነገረናል፡፡ እንድንዘጋጅበት ጊዜ ማግኘት ነበረብን፡፡ አሁን የምንሰማው ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሆነ ነው፤›› በማለት የገለጹ የአንድ ሆቴል ኃላፊ (ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል)፣ ቢያንስ የሦስት ወራት ጊዜ ተሰጥቶ የደብረ ዘይትና የሌሎች አካባቢ ሆቴሎች እንዲዘጋጁ ቢደረግ ይሻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይህ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ በመጪው ሰኔ ወር 15 የከተማዋ ሆቴሎች ለኮከብ ሆቴልነት ሊመዘኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

  በሌላ በኩል በደብረ ዘይትና በአዳማ (ናዝሬት) 75 ሆቴሎች ምደባ እንደሚደረግባቸው የገለጹት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ወይሳ፣ በኦሮሚያል ክልል እሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን የሚቆጣጠር ተቋም እንደሌለና ለምደባው ሥራም የአዲስ አበባ እገዛ እንደሚያፈልግ ጠይቀዋል፡፡ ክልሉ እንዲህ ያለው ተቋም ሳይኖረው፣ የጤና ቢሮውም የሚጠበቅበትን ተቋማዊ መስፈርት ሳያሟላ ለምደባው የብቃት ማረጋገጫ እንዴት ሊሰጥ እንደሚችል የደብረ ዘይት ሆቴል ቤቶች ይጠይቃሉ፡፡

  ከደብረ ዘይት ሆቴሎች ባሻገር የአዲስ አበባ ሆቴሎችም ‹‹ዕድሳት ላይ ነን፣ አልተዘጋጀንም፣ ለአሁኑ ይለፈን፤›› የሚሉ ጥያቄዎችን እንደሚያነሱ ኃላፊዎች ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም የሆቴል ደረጃ ምደባው በሒደት ላይ እንደሆነና፣ የአዲስ አበባ 132ቱ ሆቴሎች ለቅድመ ምዘና ብቁ መሆናቸው እየታየ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

  ሆቴሎችን ለመመዘን ጊዜው አሁን ይሆን?

  መንግሥት ሆቴሎችን ለመመዘን አልተቻኮለም ወይ? ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም ፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ታደሠ እንዳይላሉ፣ ለሆቴሎች በቂ ጊዜ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዜናዊ በበኩላቸው ለሁለት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየ ሥራ በመሆኑ ጊዜ አንሷል፣ መንግሥት ተቻኩሏል ሊያስብለው እንደማይችል ጠቅሰዋል፡፡ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት፣ የመዛኞችን ቡድን የሚመሩትና ለ51 የአገር ውስጥ ዕጩ የምዘና ባለሙያዎች ሥልጠና የሚሰጡት ጄምስ ማክግሬጎርም ለሆቴሎች የተሰጠው ጊዜ አጥሯል እንደማይባል ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ሁለት ዓመት ይሰጥ ቢባል እንኳ፣ ሆቴሎች ዝግጁ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ጊዜው አሁን ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  ይህ ቢባልም የክልል ሆቴሎች ሥጋት ግን ቀጥሏል፡፡ አንዳንድ የሆቴል ቤት ኃላፊዎች አዲስ አበባ እየመጡ ምዘና የተካሔደባቸው ሆቴሎች ያለፉባቸውን መንገዶችና የተመዘኑባቸውን ሥልቶች ማጥናትና መረጃ መሰብሰብ ጀምረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ምዘና በሰኔ ወር እንደሚጠናቀቅ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ ሆቴሎች ላይ ከሰኔ ወር ጀምሮ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ምዘና ይደረጋል፡፡ ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ውስጥ የአገሪቱ ሆቴሎች የምዘና ሒደት ተጠናቆ ለመንግሥት ይቀርባል፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሁሉንም ውጤት ይፋ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው ከጥቅምት ወር በኋላ እንደሆነ ማክግሬጎር አስታውቀዋል፡፡Anchor

   

   

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች