Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዓለምየሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ወንድም ሞት እንቆቅልሽ

  የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ወንድም ሞት እንቆቅልሽ

  ቀን:

  የሰሜን ኮሪያ የቀድሞው መሪ ሟች ኪም ጆን ኢል የበኩር ልጅ ኪም ጆን ናም በድንገት ሞቶ መገኘት፣ የዓለም መነጋገሪያ ከሆነ ሳምንት አልፎታል፡፡ ከመነጋገሪያነት ባለፈ ግን እንዴትና በማን ተገደሉ በሚለው ላይ መላምት ከመሰንዘር ባለፈ የተረጋገጠ መግለጫ የሰጠ አካል የለም፡፡ ሲኤንኤንም በድረ ገጹ ‹‹ድንገተኛ የሆነው የጆን ናም ሞት በሚስጥር የተተበተበ ነው፤›› ሲል አስፍሯል፡፡

  በማሌዥያ ዋና ከተማ ኳላላምፑር አውሮፕላን ማረፊያ ከአሥር ቀናት በፊት ተመርዘው የተገኙት ጆን ናም የአሁኑ የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡን የአባት ልጅ ቢሆኑም፣ በሰው እጅ መገደላቸውንና በተለይም በግድያው የሰሜን ኮሪያ እጅ እንዳለበት ደቡብ ኮሪያ ትናገራለች፡፡

  በግድያውም አምስት ሰሜን ኮሪያውያን እንደተሳተፉበት እርግጠኛ መሆናቸውን በደቡብ ኮሪያ ዩኒፊኬሽን (የውህደት) ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም ሰሜን ኮሪያ በግድያው ስለመሳተፏ የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡

  የማሌዥያ ፖሊስ በግድያው እጃቸው አለበት ከተባሉት አምስት ተጠርጣሪዎች መካከል አንዷን ሰሜን ኮሪያዊት በቁጥጥር ሥር አውሎ አራቱን ለመያዝ በማደን ላይ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ፒዮንግያንግ ግን ግድያውን በተመለከተ እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም፡፡

  የማሌዥያ ፖሊስ አዛዥ ኑሪ ራሺድ ኢስማኤል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በመታደን ላይ ያሉትን ተጠርጣሪዎች ስምና ዕድሜ ይፋ በማድረግ ከኢንተርፖል አባላት ጋር በመሆን ፍለጋውን መቀጠላቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ተፈላጊዎቹ የያዙት ፓስፖርትም የዲፕሎማቲክ ሳይሆን መደበኛው መሆኑንም አክለዋል፡፡

  ኪም ጆን ናም የተመረዙት ከኳላላምፑር አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ማኮ ለመብረር በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ ነው፡፡ አደጋ እንደደረሰባቸው በኤርፖርቱ ለደንበኞች አገልግሎት ከሚሰጡ ሠራተኞች ዕርዳታ ለማግኘት ሞክረው ነበር፡፡ ‹‹ማንነታቸውን ያልለየኋቸው ሁለት ሴቶች ፊቴን በፍሳሽ ሲዳብሱኝ ወዲያውኑ ተዝለፈለፍኩ፤›› ብለው ለሠራተኞቹ መናገራቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ፡፡

  የኪም ጆን ናም አስከሬን ባለፈው ሳምንት ምርመራ የተደረገለት ሲሆን፣ ውጤቱን ለማወቅም ሁለት ሳምንት ይወስዳል ተብሏል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ግን አስከሬኑ እንዲላክላት በመጠየቅ፣ በማሌዥያ የሚሠራውን የአስከሬን ምርመራ ውጤት እንደማትቀበል አሳውቃለች፡፡

  ማሌዥያ ግን የዲኤንኤ ምርመራ እንደሚደረግለትና ለዚህም ከቤተሰቡ ናሙና መቀበል እንደሚገባ እየገለጸች ነው፡፡

  ከሰውየው አሟሟት ጋር በተያያዘ ሌሎች አራት ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ሪ ጆን ቾል የተባለ የሰሜን ኮሪያ ተወላጅ ነው፡፡ ሁለተኛው መሐመድ ፋሪድ ቢን ጃላአሉዲን የተባለ ማሌዥያዊ ሲሆን፣ ሦስተኛዋ ደግሞ የኢንዶኒዥያ ዜጋ የሆነች የቬይትናም ፓስፖርት ያላት ዶአን ታይ ሁንግ ትባላለች፡፡ አራተኛዋ ኢንዶኔዥያዊት ሲቲ አይሻ ናት፡፡

  ከሴኩሪቲ ካሜራ ተወስዶ በደቡብ ኮሪያና በማሌዥያ ቴሌቪዥኖች የተሠራጨው ፊልም እንደሚያሳየው፣ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ‹‹ኤልኦኤል›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ነጭ ቲሸርት የለበሰች ትታያለች፡፡

  እ.ኤ.አ. በሰኔ 1970 የተወለዱት ኪም ጆን ናም እ.ኤ.አ.. በ2003 ነበር ከሰሜን ኮሪያ በመሰደድ በሰሜን ኮሪያ በሚገኘው የቤተሰቦቹ አስተዳደር ላይ የሰላ ትችት መሰንዘር የጀመሩት፡፡ ለሞታቸው ምክንያት የሆነው ጉዳይ እስካሁን ባይታወቅም፣ የፖለቲካ ተንታኞች ከሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡን ጋር ያላቸው የፖለቲካ ልዩነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

  ናም በተደጋጋሚ ቻይናን በመጎብኘት ከቤጂንግ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንደፈጠሩም ይነገራል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ የቻይና ደጋፊ ናቸው የሚባሉትን በጠላትነት በመፈረጅ ትታወቃለች፡፡ በናም ግድያም የሰሜን ኮሪያ ስም የተነሳው ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ጋር ባላት ጥላቻ ነው፡፡ ናም ከተገደለ በኋላም ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ታስመጣ በነበረው የድንጋይ ከሰል ምርት ላይ ገደብ ጥላለች፡፡

  ናም የሰሜን ኮሪያ አስተዳደርን የሚቃወም ፓርቲ በማቋቋም ሰሜን ኮሪያን ሲተቹ ነበር፡፡ ሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ መዋሀድ አለባቸው በሚለው አቋማቸውም ይታወቃሉ፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...