Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ስልሳ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በኪሳራ ሊዘጉ ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብሳቢና ተከፋይ ዕዳቸው ሊሰረዝ ነው

  ከ1989 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ወደ ግል ከተዛወሩ 263 የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ በ60 ድርጅቶች ስም የነበሩ ተሰብሳቢና ተከፋይ ዕዳዎችን ማግኘት ባለመቻሉ፣ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ ሊሰረዝ መሆኑን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ አስታወቀ፡፡ በዚህም ሳቢያ 60 የልማት ድርጅቶች በኪሳራ ይዘጋሉ ተብሏል፡፡

  ቦርዱ በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 208/92 በተሰጠው ሥልጣን ማለትም በኪሳራ የሚዘጉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሒሳብ የማጣራት ሥልጣን መሠረት፣ የ60 የልማት ድርጅቶችን ሒሳብ እያጣራ መሆኑን የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ዛፉ ተናግረዋል፡፡

  የቦርዱን የ2009 በጀት ግማሽ ዓመት ሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ማክሰኞ የካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በ60 የልማት ድርጅቶች ላይ በተደረገ የሒሳብ ማጣራት ሒደት የአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ ቡና ላኪዎች ማኅበርና ተዋሕዶ ጥበብ ፋብሪካን ሒሳብ አጣርቶ በማጠናቀቁ ሙሉ በሙሉ መሰረዛቸውን አቶ ዘውዱ አስረድተዋል፡፡ በጥቁር ዓባይ ኮንስትራክሽንና በብሔራዊ መሐንዲሶችና ተቋራጮች ማኅበርም የሒሳብ ማጣራት ሒደቱ እየተጠናቀቀ በመሆኑ፣ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚሰረዝም አክለዋል፡፡

  የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ የተሰጡት ኃላፊነቶች የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ ሲዛወሩ፣ ወደ አክሲዮን ማኅበሩ የማይተላለፉ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሒሳቦችን መረከብ፣ በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮችን ተከታትሎ ማስፈጸም፣ ንብረት ተረክቦ ማስወገድ፣ ሰነዶችን ተረክቦ ማስተዳደርና የሚፈርሱ የልማት ድርጅቶችን ሒሳብ ማጣራት መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ቀሪዎቹን የሚፈርሱ 55 ድርጅቶችን ሒሳብ እያጣሩ የሚሰበሰበውን በመሰብሰብና የሚከፈለውን በመክፈል ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ መሰብሰብ የቻሉትን ሒሳቦች እየሰበሰቡ መክፈል ያለባቸውንም እየከፈሉ ቢሆንም፣ 60 ድርጅቶች ግን እንደሚሰረዙና ለማፍረስ በሒደት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

  የሚሰረዙት ድርጅቶች ወደ ግል ከተዛወሩ አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

  በ2009 በጀት ግማሽ ዓመት የፋይናንስ የንብረት አጠቃቀም ውጤታማነትን በተመለከተ ቦርዱ የግማሽ ዓመት 4,602,512 ብር ዕቅድ ይዞ፣ 3,747,624 ብር ወይም 81.43 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

  ቦርዱ በግማሽ ዓመት ከ57 ግለሰቦች 877,221 ብርና ከ67 ድርጅቶች ደግሞ 4,688,788 ብር የገቢ ግብር ወይም በድምሩ 5.5 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ ለ143 ግለሰቦችና ለ16 ድርጅቶች ደግሞ በድምሩ 6,759,668 ብር የክፍያ አገልግሎት መፈጸሙንም አክለዋል፡፡

  ባለአደራ ቦርዱ ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ በነደፈው የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሠረት እየሠራ መሆኑን አቶ ዘውዱ ገልጸው፣ በተያዘው በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸው አኩሪና መላውን ሠራተኞች የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዕቅድ አፈጻጸሙን ሪፖርት ያቀረቡት የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነትና ኢንፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግዛው አቡቴ ሲሆኑ፣ በግማሽ ዓመቱ 1,112 ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ከተገልጋዮች ቀርቦ ለ948 ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ 

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች