Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎች ድርድር ብልሹውን የፖለቲካ ባህል ያስወግድ!

  ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል እያስቆጠረ ያለው የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ኋላቀር፣ ከሥልጣኔ ጋር የማይተዋወቅ፣ ለሰጥቶ መቀበል መርህ ቦታ የማይሰጥ፣ በጭፍን ጥላቻ የተዋጠ፣ ከውይይትና ከድርድር ይልቅ እልህና ጉልበት የሚበረታበት፣ በሸፍጥና በሴራ የተተበተበ፣ ቡድንተኝነት የሚያጠቃው፣ ወዘተ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ ወይ ጠቅልሎ የመውሰድ አለበለዚያም በዜሮ የመውጣት አባዜ የተጠናወተው የአገሪቱ ፖለቲካ ታሪክ ቅርፊቱ ላይ ዴሞክራሲ የሚል ታፔላ ቢለጠፍም፣ ውስጡ ግን በተቃራኒው ነው፡፡ መንበረ ሥልጣኑን የጨበጡም ሆኑ ለሥልጣን እንታገላለን የሚሉት በተለያዩ ጽንፎች ላይ ሆነው ቢቆራቆዙም፣ አንዳቸውን ከሌላኛው ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ ሞገደኝነታቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ከጊዜያዊ ኅብረት ምሥረታ እስከ ግንባርና ውህደት ድረስ በታዩ ውጣ ውረዶች፣ የጋራ አማካይ ፈጥሮና ልዩነትን አስታርቆ መሥራት ሲቻል ብዙ ነገሮችን አበለሻሽተዋል፡፡ ይህ የተበላሸ የፖለቲካ ባህል ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡

  ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የነበሩ ውጣ ውረዶችን ለሚታዘብ ማንኛውም ጤነኛ ዜጋ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር በጣም ከመበላሸቱ የተነሳ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እጅግ በጣም መዳከሙን ለማወቅ ምንም አይሳነውም፡፡ ዴሞክራሲ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ትርጉሙ ግራ እስከሚያጋባ ድረስ ፈሩን ስቷል፡፡ ጽንፈኝነትና ጭፍንነት የበላይነት እንዲያገኙና ሰላም እንዲደፈርስ በር ከፍቷል፡፡ ሕገወጥነት ስለተፀናወተው ለሕግ የበላይነት ክብር ነፍጓል፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ድምፃቸው ታፍኗል፡፡ ለእንግልትና ለመከራ ተዳርገዋል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለምን ይበጃል የሚል እሮሮ እንዲስተጋባ ምክንያት ሆኗል፡፡ የአገሪቱ ምርጫ ለዛውን አጥቶ የአንድ ወገን የበላይነት ተንሰራፍቷል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በመታፈኑ አገርን ችግር ውስጥ የሚከት አመፅና ብጥብጥ አስከትሏል፡፡ ሕግ ባለበት አገር ሕገወጥነት በዝቷል፡፡ ውጤቱም አስከፊ ሆኗል፡፡ ይህንን አስከፊ ገጽታ ለመለወጥ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ውይይትና ድርድር ለማድረግ ከዘገየ በኋላ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ‹‹ከመቅረት መዘግየት›› እንዲሉ ይህንን አጋጣሚ ማበላሸት አያስፈልግም፡፡

  የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎች ድርድር ብልሹውን የፖለቲካ ባህል እንዲያስወግድ ከተፈለገ፣ ሰከን ያለና የሠለጠነ ግንኙነት ለመጀመር መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሐሳቦች በነፃነት የሚሽንሸራሸሩበት፣ የማያስማሙ ጉዳዮችን እያቻቻሉ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ የሚግባቡበት፣ ከኃይል ይልቅ ውይይትን የሚያስቀድሙበትና ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ የሚሆኑበት መደላድል ነው፡፡ ሕዝብ ያለምንም መሸማቀቅና ፍራቻ ተወካዮቹን በነፃነት የሚመርጥበት ሥርዓት በመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል ሜዳ ላይ በነፃነት ሊወዳደሩ ይገባል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ሥርዓት ለመገንባት ደግሞ ሁሉም ፓርቲዎች እርስ በርስ ዕውቅና መሰጣጣትና ለሰጥቶ መቀበል መርህ ተገዥ ሊሆኑ የግድ ነው፡፡ ይህ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚንፀባረቅ ፍላጎት መሬት ላይ ወርዶ በተግባር እንዲታይ፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች መጀመሪያ ለሕግ የበላይነት መገዛት አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ በሕግ የበላይነት ሥር የሚመራ መንግሥታዊ ሥርዓት ነውና፡፡

  ውይይትም ሆነ ድርድር ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ወገኖች ያለፉትን ቂምና ቁርሾዎች ወደ ጎን በማድረግና ለአገርና ለሕዝብ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ከልብ በማመን፣ አዲሱን ጉዞ በሠለጠነ መንገድ ላይ ቢጀምሩ ጥቅሙ ለአገር ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ሁሉም የአገሪቱ ፓርቲዎች በእኩልነትና በነፃነት እንዲፎካከሩ ማድረግ የወቅቱ ዓቢይ ጥያቄ ነው፡፡ ከፖለቲካ ፍጆታነት የማይዘሉ አጓጉል ድርጊቶችን በማስወገድ የዜጎችን አንገት ሲያስደፋ የኖረውን አስከፊ የፖለቲካ ባህል መለወጥ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ድርድሩም ሆነ ውይይቱ በቀና መንፈስ እንዲጀመር ሲፈለግ በቅድመ ሁኔታዎች እያመካኙ ምክንያት መደርደር ሊቆም ይገባል፡፡ ድርድሩም ሆነ ውይይቱ ለሰጥቶ መቀበል መርህ ክፍት ከሆነ ቀዳሚው ጉዳይ የአገርና የሕዝብ ጥቅም ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁጠርኛ መሆን ግዴታ ነው፡፡

  የውይይቱም ሆነ የድርድሩ አካል የሆኑ በግራም በቀኝም ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በስብሰባ አመራር ሥርዓት፣ በድርድር ታዛቢነት፣ ከውይይቶችም ሆነ ከድርድሮች በኋላ ማን መግለጫ መስጠት እንዳለበትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ፕሮፖዛላቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ ተሰምቷል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ጅማሮዎች ላይ በአስቸኳይ ተስማምቶ ለሕዝብ ግልጽና ቢቻል አሳታፊ የሆነ ድርድር መጀመር ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ ይህንን ድርድር በትኩረት ተከታትሎ ያገባኛል የሚል ስሜት እንዲፈጠርበት የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ፓርቲዎች ነው፡፡ በተለይ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ የሲቪክ ማኅበረሰቦችና የመሳሰሉት ድምፃቸው የሚሰማበት መድረክ ሊመቻች ይገባል፡፡ ሕዝብ በባለቤትነት ስሜት የማይከታተለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የተለመደው አረንቋ ውስጥ ነው የሚዘፈቀው፡፡ ይልቁንም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አስተያየትና ሙያዊ እገዛ እንደ ግብዓት መጠቀም ፖለቲካውን ቢያንስ አንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከአሳዛኙና ከአስከፊው የፖለቲካ ባህል ውስጥ ጎትቶ ያወጣዋል፡፡

  ገዥው ፓርቲ የሕዝቡን የዓመታት የብሶት ጥያቄ ለመመለስ ቃል በገባው መሠረት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ሲወስን፣ ራሱን እንደ አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ መቁጠር አለበት፡፡ በምርጫ ተሸንፎ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሚሆን ሁሉ ራሱን ማሳመን ይኖርበታል፡፡ ይህ የዴሞክራሲ ፀጋ ነው፡፡ ሕግ ማክበር መጀመር ያለበት ከራሱ ነው፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት መሠረታዊ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብቶችን በውስጡ ይዟል፡፡ በዚህም መሠረት የአገሪቱ ሕዝብ የፈለገውን የፖለቲካ አቋም የመያዝ፣ የመደራጀት፣ የመምረጥና የመመረጥ፣ እንዲሁም በነፃነት የመኖር መብቱ በሕግ ዋስትና አግኝቷል፡፡ ይህ ሕግ መከበር አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የአገሪቱን ሕግ በማክበር የማይፈልጉት እንዲለወጥ፣ የሚሻሻለው እንዲሻሻል፣ የሚቀነስ ካለ እንዲነቀስ፣ የሚጨመር ካለም እንዲጨመር በሕጋዊ መንገድ የመታገል መብታቸውን ማስከበር አለባቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ሕጋዊውንና ሕገወጡን እየቀላቀሉ ትርምስ መፍጠር አይኖርባቸውም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በምኞት ሳይሆን በቁርጠኝነት በሚደረግ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ የአመፅ መንገድ ዴሞክራሲን ሳይሆን ውድመት ነው የሚያስከትለው፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲን በአጓጉል የቃላት ጨዋታ በመሸንገል ማምጣት አይቻልም፡፡ ዴሞክራሲ ሥርዓት የሚሆነው በዴሞክራቶች ብቻ ነው፡፡ ዴሞክራቶች ደግሞ ለሕግ የበላይነት ይገዛሉ፡፡ ሕግ ሲከበር ዴሞክራሲ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ የተበላሸው የፖለቲካ ባህል የሚወገደው በዚህ መንገድ ብቻ ነው! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...