Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊአዲስ አበባ ፎምና ፕላስቲክ ፋብሪካ ለሰበር ያቀረበው የንግድ ምልክት ክርክር ውድቅ ተደረገበት

  አዲስ አበባ ፎምና ፕላስቲክ ፋብሪካ ለሰበር ያቀረበው የንግድ ምልክት ክርክር ውድቅ ተደረገበት

  ቀን:

  – በምልክቱ ተጠቃሚዎች ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ ከስሬያለሁ አለ

  አዲስ አበባ ፎምና ፕላስቲክ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለሚያመርታቸው የፎምና የፕላስቲክ ምርቶች ‹‹አዲስ አበባ ፎም – Addis Ababa Foam›› የሚለውን የንግድ ምልክት፣ ‹‹ሌላ የንግድ ማኅበር ተጠቅሞብኛል›› በማለት እስከ ሰበር ችሎት አድርሶት የነበረው ክርክር በሰበር ችሎት ውድቅ ተደረገበት፡፡

  ማኅበሩ የንግድ ምልክቱን በመጠቀም ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዳደረሰበት በመግለጽ እስከ ሰበር ችሎት ድረስ የተከራከረው ሌላው ተከሳሽ ድርጅት፣ ኒው ፍላወር አጠቃላይ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ‹‹ኒው ፍላወር ፎም – New Flower Foam›› በማለት የተጠቀመበት መሆኑን ለችሎቱ ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ይገልጻል፡፡

  የሁለቱ ማኅበራት (ድርጅቶች) ክርክር የጀመረው ሚያዝያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ አዲስ አበባ ፎምና ፕላስቲክ የንግድ ምልክቱን በአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ማስመዝገቡንና ከሰኔ 27 ቀን 1999 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ፀንቶ እንደሚቆይ ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ማግኘቱን ገልጿል፡፡ ኒው ፍላወር አጠቃላይ ንግድ ግን በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎም ‹‹ኒው ፍላወር – New Flower›› የሚል የንግድ ምልክት በመጠቀም ተመሳሳይ ምርትና አገልግሎት ለሕዝብ እያቀረበ መሆኑን በመግለጽ፣ ለንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ክስ መሥርቷል፡፡

  አዲስ አበባ ፎምና ፕላስቲክ ፋብሪካ አምርቶ በሚሸጣቸው የስፖንጅ/ፎም ምርቶችና በዋናነት የአልጋ ፍራሽ ምርቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በሚያሳድር ሁኔታ፣ ኒው ፍላወር በእንግሊዝኛና በአማርኛ የንግድ ምልክቱን በሚያመርተው ፍራሽ ላይ አትሞ በመሸጡ፣ 3,689,230 ብር ኪሳራ እንዳደረሰበት ለባለሥልጣኑ ፍርድ ቤት በክሱ አመልክቷል፡፡

  አዲስ አበባ ፎምና ፕላስቲክ የሚያመርታቸው ምርቶችን የአንድ ፋብሪካ ምርቶች እንደሆኑ የሚመስልና የሚያሳክር ማስታወቂያን ኒው ፍላወር ስለሚያስነግር የንግድ ምልክቱን እንዳይጠቀም፣ ያመረታቸው ምርቶች ወደ ገበያ እንዳይገቡና ቀደም ብሎ ያመረታቸው ተሰብስበው እንዲወገዱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቆ ነበር፡፡ መክሰሩን በመግለጽ ከ3.6 ሚሊዮን ብር ላይ ዘጠኝ በመቶ ወለድ ታስቦ እንዲከፈለው ውሳኔና ትዕዛዝ እንዲሰጥለትም ጠይቋል፡፡

  ኒው ፍላወር አጠቃላይ ንግድ ለባለሥልጣኑ ፍርድ ቤት በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ የንግድ ስምና ምልክቱን ከመጠቀሙ በፊት በንግድ ሚኒስቴር ከአርባ በላይ ስሞች ቀርበው እሱ ያቀረበው ስምና ምልክት አለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም በጋዜጣ ተቃዋሚ ካለ የሚል ጥሪ ተደርጎ የተቃወመ የለም፡፡ በመሆኑም በሚያመርተው ምርት ላይ ኒው ፍላወር የሚል የንግድ ስያሜ ቀርፆ ምርቱን ማከፋፈል ተገቢ እንደሆነና ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት እንደተሰጠው አስረድቷል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር ያገኘው የንግድ ስምና ቃላት፣ ዲዛይኖች፣ ፊደሎችና ቀለሞች ጋር በቅንጅት የተሠራ፣ ክብ ቅርፅ ላይ በመሀሉ የልብ ቅርፅ ያለው ሆኖ በልቡ መሀል የጽጌረዳ አበባ ተክል ያለውና በክቡ ዙሪያ ላይ የድርጅቱን ስያሜ የያዘ፣ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ጽሑፎች፣ አማርኛና እንግሊዝኛውን ጽሑፎችን የሚያካፍሉ ሁለት የስታር ምልክቶች የያዘ የንግድ ምልክት መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ከአዲስ አበባ ፎም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግለት የባለሥልጣኑን ፍርድ ቤት ጠይቋል፡፡

  የባለሥልጣኑ ፍርድ ቤት ከሳሽ አዲስ አበባ ፎምና ፕላስቲክ ፋብሪካ ወደ ገበያ በሚያቀርበው ምርት ላይ የሚገኘው ‹‹Addis Ababa Foam›› የሚለው ቃል፣ ተከሳሽ ከሆነው ‹‹New Flower Foam›› የሚለው ቃልና ከምርቶቹ ጋር በተገናኘ ማደናገርን ያስከትላል ወይስ አያስከትልም? የሚለውን ጭብጥ ይዟል፡፡ በተጨማሪም ‹‹መደናገር ያስከትላል›› ከተባለ ለከሳሽ ሊወሰን የሚገባው ዳኝነት ምን መሆን አለበት? የሚል ተጨማሪ ጭብጥ ይዞ አከራክሯል፡፡

  የባለሥልጣኑ ፍርድ ቤት የንግድ መልክቶቹ ማሳከር አለማሳከራቸውን የተለያዩ ድርጅቶች ስያሜ በመውሰድ ግምት መያዙን፣ የከሳሽ ምርት የቀነሰው እንዳለው ደንበኞች ተሳክረው ነው ወይስ በምርቶቹ ጥራቶች የሚሉትን ሁሉ መርምሯል፡፡ በተጨማሪም የከሳሽን ሁለት ምስክሮችና የተከሳሽን ሦስት ምስክሮች በማስቀረብ ሰምቷል፡፡ በመጨረሻ ላይ ከሕጉ አግባብ ጋር የቀረቡለትን ማስረጃዎችና የምስክሮች ቃል መርምሮ በሰጠው ውሳኔ፣ ከሳሽ አዲስ አበባ ፎምና ፕላስቲክ ፋብሪካ ያቀረበው የክስ አቤቱታ የሕግ ድጋፍ የሌለው መሆኑን ጠቅሶ ውድቅ አድርጎታል፡፡

  ፋብሪካው ለባለሥልጣኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፅንቶበታል፡፡ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንዳለበት በመግለጽ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም፣ ‹‹የቀረበው ጉዳይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተሠርቷል ለማለት አልተቻለም፤›› በማለት ይግባኙን ውድቅ ማድረጉን ገልጾ፣ ኒው ፍላወር ፎም በሕጋዊ መንገድ ያገኘውን የንግድ ስያሜና ምልክት መጠቀም የሚችል መሆኑን አረጋግጦለታል፡፡       

   
   

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...