Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊቂሊንጦን በማቃጠል ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች በከሳሻችን ልንጠበቅ አይገባም አሉ

  ቂሊንጦን በማቃጠል ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች በከሳሻችን ልንጠበቅ አይገባም አሉ

  ቀን:

  ቂሊንጦ የተከሳሾች ማቆያ ቤቶችን በማቃጠል፣ በ23 ሰዎች ሞትና ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ንብረት ማውደም ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው 38 ተከሳሾች፣ ‹‹በከሳሻችን ልንጠበቅ አይገባም›› ሲሉ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታ አቀረቡ፡፡

  ተከሳሾቹ ለዓርብ ታኅሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. መቃወሚያ ካላቸው ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረውና መቃወሚያቸውን አዘጋጅተው እንዲቀርቡ፣ ወይም መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ተነጋግረው እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

  በተሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ከሁለት ተከሳሾች በስተቀር ሁሉም በጠበቃ ተወክለው የቀረቡ ቢሆንም፣ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ የመቃወሚያ ምላሽ ሳይዙ ቀርበዋል፡፡

  በዕለቱ ችሎቱ ሲሰየም ከተቀመጡበት የተነሱት ተከሳሾቹ እንዲቀመጡ ሲነገራቸው ቤተሰቦቻቸው በችሎት ካልታደሙ እንደማይቀመጡ ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲቀመጡ ካደረገ በኋላ ድርጊታቸው አግባብ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ለችሎት ክብር መስጠት እንዳለባቸው፣ የሚያሳዩት ባህሪ ጥሩ አለመሆኑን፣ የሕግ የበላይነትን ማክበር ሲኖርባቸው እየፈጸሙት ያለው ነገር ችሎት መድፈር በመሆኑ፣ ተጨማሪ ቅጣት እንደሚያስከትልባቸው አስታውቋል፡፡ መናገር የሚችሉት በጠበቆቻቸው ብቻና በጽሑፍ መሆኑን በማስታወቅ፣ ጠበቃ የሌላቸውን ተከሳሾች እንዲናገሩ ፈቅዷል፡፡ የተወሰኑ ወንበሮች እንዲዘጋጁ በማድረግም ከአሥር የማይበልጡ የተከሳሾች ቤተሰቦች እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

  ተከሳሾቹ ሁሉም ብድግ ብለው በመቆም፣ ‹‹የህሊና ፀሎት እናድርግ›› በማለት ለአንድ ደቂቃ ቆመው ተቀምጠዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ቀጠሮ ስላልቀረቡት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እንዲያስረዱ የማረሚያ ቤቱን ተወካይ ሲጠይቅ፣ ዶ/ር ፍቅሩ በሌላ ክስ ፍርደኛ በመሆናቸው ቂሊንጦ እንደሌሉ ምክትል ሳጂን እንዳሻው ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ብሎ የተሰጠውም ትዕዛዝ እንዳልደረሳቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

  ሁሉም ተከሳሾች እጃቸውን በማውጣት አቤቱታ እንዳላቸው ሲገልጹ፣ ፍርድ ቤቱ በጽሑፍ እንጂ በቃል እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የቃል አቤቱታ እንደማይቀበል የገለጸ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ግን ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የሐሰት ክስ እንደተመሠረተባቸው፣ የተወሰኑት በሌላ ክስ ተፈርዶባቸው በዝዋይ እስር ቤት እንደነበሩና ከቃጠሎው በኋላ ወደ ቂሊንጦ መምጣታቸውን፣ ቃላቸውን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 27 መሠረት እንዲሰጡ የተደረጉት በግዳጅ በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግላቸው ተናግረዋል፡፡

  ቂሊንጦ እስረኛ ማቆያ ቤት በተለየ ሁኔታ እንደታሰሩና ለሌሎች ታሳሪዎች የሚደረገው ለእነሱ እንደማይደረግላቸው ገልጸው፣ ቤተሰቦቻቸው የሚጠይቋቸው ለ30 ደቂቃ ብቻ መሆኑንና የሌሎቹ ታሳሪዎች ግን ሙሉ ቀን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ታስረው ሲመረመሩ የተገረፉት አንሶ ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ምክንያት ወደ ቂሊንጦ ሲመለሱ እንደሚደበደቡና በካቴና ታስረው እንደሚያድሩ ገልጸው፣ ኢሰብዓዊ ድርጊት እየተፈጸመባቸው መሆኑን በመጯጯህ አስረድተዋል፡፡ የተወሰኑ እስረኞች ሲገረፉ እነሱ እንዲሰሙና እንዲሳቀቁ እንደሚደረግም ታሳሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ በሕጉና በሥርዓት እንዲናገሩ በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ፣ ‹‹እኛ እኮ እየጠየቅናችሁ ያለነው ብሶታችንን እንድትሰሙን ነው፡፡ ይህ ፍርድ ቤት በነፃነት እንድንናገር ካልፈቀደልን የት ልንናገር ነው? ስሙን፣ ስሙን…›› በማለት ተናግረዋል፡፡

  በርከት ላሉ ተከሳሾች የቆሙ ጠበቃ ተከሳሾቹ አንድ በአንድ በተራ እንዲናገሩ ወይም እሳቸው እንዲናገሩላቸው በማስረዳት ካረጋጓቸው በኋላ ለችሎቱ እንዳስረዱት፣ ‹‹እንዲህ የሚያደርጋቸው ብሶት ስለሆነ ተጠርጣሪዎች እንጂ ወንጀለኞች ስላልሆኑ ሰብዓዊ መብታቸው ይጠበቅ፤›› ብለዋል፡፡

  ጠበቃው መቃወሚያቸው ብዙ መሆኑን ጠቁመው በተለዋጭ ቀጠሮ በጽሑፍ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡ ተከሳሾቹ ግን እንዳይናገሩ ቢከለከሉም፣ ‹‹ጠበቆቻችን እንደ እኛና የእኛን የውስጣችንን ሁሉ መናገር አይችሉም፤›› በማለት ፍርድ ቤቱ እንዲሰማቸው ተማፅነዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሊሰጥ ሲል ለመናገር ቢፈልጉም፣ ፍርድ ቤቱ ያላቸውን አቤቱታ ሁሉ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ በመንገር አልተቀበላቸውም፡፡

  ማረሚያ ቤቱ በተደጋጋሚ በእስረኛ አያያዝ ሁኔታ አቤቱታ ስለቀረበበት ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ፣ ዶ/ር ፍቅሩ የት እንዳሉና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አጣርቶ እንዲያቀርብ፣ መቅረብ የሚችሉም ከሆነ እንዲያቀርባቸው ፍርድ ቤቱ አስታውቆ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...