Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በግንባታ አካባቢዎች የሚታዩ አብዛኞቹ አደጋዎች ሕግ ባለማክበር የሚደርሱ ናቸው!

  በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ግንባታዎች በስፋት ይካሄዳሉ፡፡ ከመኖሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ድረስ በሚካሄዱ ግንባታዎች ብዛት ያላቸው ዜጎች ከቀን ሠራተኝነት ጀምሮ በተለያዩ ሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡ በጣም ውስን ከሆኑት በስተቀር ለሠራተኛ ደኅንነትና ጤንነት ትኩረት ስለማይሰጥ፣ በግንባታ ሥራ ውስጥ የተሰማሩ በርካታ ዜጎች ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በደረሱ አደጋዎች በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከአደጋ በሕይወት ቢተርፉም ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ተዳርገው በአሳዛኝ ሁኔታ ቀሪ ሕይወታቸውን የሚመሩ ብዛት ያላቸው ዜጎች አሉ፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉም ሆነ በሕንፃ አዋጁ በግንባታ ወቅት መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችም ሆነ የሙያ ደኅንነት፣ ጤንነትና የሥራ አካባቢ በተመለከተ ድንጋጌዎች ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ሕጎች በአግባቡ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው ምክንያት ብቻ የበርካታ ዜጎቻችን ሕይወት ጠፍቷል፡፡ የበርካቶችም ሕይወት ተመሰቃቅሏል፡፡

  በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ 92 አሠሪዎች ከተጣሉባቸው ግዴታዎች መካከል፣ የሠራተኞችን ደኅንነትና ጤንነት በሚገባ ለመጠበቅ ተገቢ የተባሉ የመከላከያ ዕርምጃዎችን የመውሰድ ኃላፊነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በአዋጁ ስለሙያ ደኅንነትና ጤናማነት የተደነገጉ ሁኔታዎችን ማሟላት፣ በሥራ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችንና በጤንነት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ሥልጠና መስጠት፣ ጉዳቶችን ለማስወገድ ከጥንቃቄ በተጨማሪ የአደጋ ተከላካይ ሠራተኞች መመደብ፣ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ተከታታይ ኮሚቴ ማቋቋምና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ለሠራተኞች የአደጋ መከላከያ መሣሪያ፣ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶች ማቅረብ፣ ስለአጠቃቀሙ መመርያ መስጠት፣ በሥራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችንና አደጋዎችን መመዝገብና ለሥራ ሁኔታዎች መቆጣጠሪያ አገልግሎት ማስታወቅ፣ እንደ ሥራው ፀባይ አዲስ ለሚቀጠሩ ሠራተኞች በአሠሪው ወጪ የጤና ምርመራ እንዲደረግላቸውና በአደገኛ ሥራ ላይ ለሚሰማሩ ሠራተኞች እንደ አስፈላጊነቱ የጤና ምርመራ እንዲደረግላቸው ማድረግ፣ የድርጅቱ የሥራ ቦታ በሠራተኞች ደኅንነትና ጤንነት ላይ አደጋ የማያስከትል መሆኑን ማረጋገጥና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ሠራተኞችም በበኩላቸው በዚህ መሠረት ሥራቸውን በልዩ ጥንቃቄ እንዲያከናውኑ አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ሕግ እየተከበረ ነው ወይ ተብሎ ሲጠየቅ ግን መልስ የለም፡፡

  በዚህ አዋጅ መሠረት ምን ያህሉ የመንገድ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የሕንፃ፣ የሪል ስቴት፣ ወዘተ. ሥራ ተቋራጮች ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ሲባል መልሱ አሳዛኝ ነው፡፡ በየሕንፃው ላይ ተንጠላጥለው የሚሠሩ የቀን ሠራተኞችንም ሆነ ሙያተኞችን ለሚመለከት ታዛቢ፣ የአደጋ መከላከያ አልባሳትና መጫሚያዎች እንዲሁም የራስ ቅል መከላከያ እንደሌላቸው በቀላሉ ይገነዘባል፡፡ በዚህም ምክንያት አፈር ተንሸራቶ መሠረት ሲደረመስም ሆነ፣ በብረት መሆን የሚገባው የሕንፃ መወጣጫ የእንጨት ርብራብ ሲገረሰስ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የዕድሜ ልክ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የሥራ ቦታ ደኅንነት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ወጥቶ ተግባራዊ የሚያደርግ በመጥፋቱ ብቻ፣ የዜጎች ሕይወት ከአደጋ ጋር ተፋጦ ይኖራል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች የተለያዩ ሥፍራዎች ችግሩ ተመሳሳይ በመሆኑ የመንግሥትንም ሆነ የባለድርሻ አካላትን ጠንካራ ምላሽ ይፈልጋል፡፡

  በሕንፃ አዋጁ ውስጥ የተጠቀሱ የጥንቃቄ ድንጋጌዎች በከፍተኛ ደረጃ ስለሚጣሱ፣ በተደጋጋሚ አደጋዎች ሲከሰቱ ማየት ተችሏል፡፡ በሕንፃ አዋጅ አንቀጽ 31 መሠረት ማንኛውም ግንባታ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን፣ የግንባታው ሠራተኞችን፣ ሌሎች ግንባታዎችን ወይም ንብረቶችን ደኅንነት በማያሰጋ መንገድ ዲዛይን መደረግና መገንባት ይኖርበታል ይላል፡፡ በተጨማሪም ከግንባታ ጋር የተያያዘ ቁፋሮ ማንኛውንም ንብረት ወይም አገልግሎት ደኅንነት ጉዳት ላይ የሚጥል ሲሆን፣ የግንባታ ቦታው ባለቤት የንብረቱን ወይም የአገልግሎቱን ደኅንነት ለመጠበቅ በቂ ድንጋጌ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የተቆፈረ ጉድጓድ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ከሆነ፣ ወይም በጉድጓዱ ውስጥ መሠረት በሚገነባበት ጊዜ ባለቤቱ ወይም ቁፋሮውን ያካሄደ ሰው ጉድጓዱን ለደኅንነት በማያሰጋ ሁኔታ መጠበቅ አለበት በማለት ያስታውቃል፡፡

  እንዲሁም ማንኛውም አዲስ የሚገነባ ሕንፃ መሠረት ጭነት በነባር መሠረቶች፣ የአገልግሎት መስመሮች ወይም በሌሎች ሥራዎች ላይ ችግር የሚፈጥር መሆን የለበትም ሲል ያስጠነቅቃል፡፡ ይህ ምን ያህል ተፈጻሚ ነው የሚል ጥያቄ ካለ መልሱ ዝም ነው፡፡ እንኳንስ እንዲህ ዓይነቱን ጥንቃቄ ማድረግ የግንባታ ቁሳቁሶችን መንገድ ዘግቶ ማራገፍና ማከማቸት፣ የእግረኛ መንገዶችን ጭምር ማጠር፣ የተቆፈሩ ጉድጓዶችን ክፍት በመተው ለዜጎች ሕይወትና አካል ጉዳት ምክንያት መሆን፣ ወዘተ. የተለመዱ ክስተቶች ናቸው፡፡ ሕግ አክባሪም አስከባሪም በመጥፋቱ ይህ ሁሉ አደገኛ ተግባር የተለመደ ሆኗል፡፡ አሁንማ የሕንፃ መሠረት ሲሠራ የመሬት መንሸራተት እየተፈጠረ የአስፋልት መንገድ ሳይቀር እየተናደ ነው፡፡ በሕዝብ ሕይወት ላይ አደጋ ተደቅኗል፡፡

  በግንባታ ወቅት ሦስት ተዋናዮች አሉ፡፡ አንደኛው የግንባታው ባለቤት፣ ሁለተኛው ሥራ ተቋራጩ፣ ሦስተኛው ተቆጣጣሪው (አማካሪ ድርጅት) ናቸው፡፡ ሦስቱ በሚገባ እየተናበቡ መሥራታቸውን ማረጋገጥ ያለበት ደግሞ በአካባቢው ያለ የመንግሥት መስተዳድር (ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ …) ነው፡፡ እነዚህ አካላት በአግባቡ ሥራቸውን ሲያከናውኑ አመርቂ ውጤት እንደሚገኘው ሁሉ፣ የሙስና ሰለባ ሲሆኑ ግን አደጋ ይፈጠራል፡፡ በተለይ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ሥራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉም ሆነ የሕንፃ አዋጁ ተግባራዊ ሲሆኑ አይታዩም፡፡ በመገንባት ላይ ያለ ሕንፃ ሠራተኞችን ተሸክሞ ሲገረሰስ፣ በቂ የደኅንነት ቁሳቁሶች የሌሉዋቸው ሠራተኞች አደገኛ የሆነ የእንጨት ርብራብ ላይ ሆነው ሲሠሩ፣ በሕጉ መሠረት ሳይጠናቀቁና የብቃት ማረጋገጫ ሳይሰጣቸው ሕንፃዎች ሲከራዩ፣ በግንባታ ላይ ካሉ ሕንፃዎች አናት የተለያዩ ቁሳቁሶች ወደ መሬት እየወረዱ ተላላፊ ሰዎችን ሲጎዱ፣ ጥራት የሌላቸው ግንባታዎች ለአገልግሎት እንዲውሉ ሲደረግ፣ ለሰው ልጅ ሕይወት ኢምንት ታህል አዘኔታ የሌላቸው ድርጊቶች በተደጋጋሚ ሲፈጸሙና የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ሕጉን በአግባቡ ማስፈጸም ሲያቅታቸው ለአገር ጭምር አደጋ እየሆነ ነው፡፡

  ሁሌም እንደምንለው የሕግ የበላይነት በሌለበት ሕገወጥነት የበላይነት ያገኛል፡፡ ሕግ ማክበር ወይም ማስከበር የሚጠቅመው የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ፣ የአገር አንጡራ ሀብትን ከብክነት ለመከላከል፣ ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ፣ ምዝበራን ለማጥፋት፣ በዜጎች መካከል ልዩነት እንዳይፈጠር፣ ወዘተ. ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለው ግን ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነትና ቸልተኝነት ነው፡፡ አዋጆቹን ተግባራዊ ለማድረግ ኃላፊነት የተሰጣቸው የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በቸልተኝነትም ሆነ በሙስና ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን ሲያቅታቸው፣ በተለያዩ ግንባታዎች ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከጥቅማቸው በላይ ማሰብ ሲሳናቸውና የዜግነት ግዴታዎቻቸውን መወጣት ሲያቅታቸው ሕገወጥነት ይበረታል፡፡ በዚህም ምክንያት የዜጎች ሕይወትና የአካል ደኅንነት ለጉዳት ይዳረጋል፡፡ በግንባታ አካባቢዎች የሚከሰቱ አብዛኞቹ አደጋዎች ሕግን ባለማክበር የሚደርሱ ናቸው የሚባለው ለዚህ ነው!        

          

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  በዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ለሚያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የዕድሜ ጣሪያ ተቀመጠ

  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኝ ነፃ የትምህርት...

  በደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ 11 ሰዎች ተገደሉ

  በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ

  ፊፋ ከምርጫው በፊት የሥነ ምግባር ባለሙያ ሊልክ መሆኑ ተሰምቷል የኢትዮጵያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...

  የሴራ ፖለቲካ መረብ ይበጣጠስ!

  ኢትዮጵያ አሁንም ከበርካታ ፈተናዎች ጋር እንደ ተፋጠጠች ነው ያለችው፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ግብፅ በጎረቤት አገሮች አማካይነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ፍጥነቷን ጨምራ እየተንቀሳቀሰች...