Monday, August 15, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊመንግሥት ቃል የገባው አሥር ቢሊዮን ብር ፈንድ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ...

  መንግሥት ቃል የገባው አሥር ቢሊዮን ብር ፈንድ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዘዙ

  ቀን:

  መንግሥት በቅርቡ ተከስቶ ለነበረው ተቃውሞ በምክንያትነት የጠቀሳቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ቃል የገባው አሥር ቢሊዮን ብር የወጣቶች የሥራ ማከናወኛ ፈንድ፣ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዘዛቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡

  መንግሥት ቃል የገባው አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ለሥራ ዕድል መፍጠሪያ የሚውል ነው፡፡ ከይዞታቸው ለሚፈናቀሉ የሚሰጠው የካሳ ክፍያም በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥታት ተከልሶ ወደ ሥራ እንዲገባ መታዘዙ ታውቋል፡፡

  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመነሳቱ በፊት መንግሥት በኢኮኖሚ ዘርፍ ቃል የገባቸው ጉዳዮች ቢያንስ መጀመር እንዳለባቸው መታዘዙን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

  በዚህ መሠረት የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሱፊያን አህመድ፣ ማክሰኞ ኅዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. የዘርፉን ባለድርሻዎች በመሰብሰብ የአሥር ቢሊዮን ብር ፈንድ አጠቃቀም ረቂቅ መመርያ ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡

  በረቂቅ መመርያው መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንዱን እንዲያስተዳድር ኃላፊነት እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡

  በመመርያው መሠረት ቢያንስ ሦስት ሆነው የተደራጁ ወጣቶች አዋጭ የሆነ የንግድ ሥራ ዕቅድ ለባንኩ በማቅረብ የሥራ ማስኬጃ ብድር ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡ ብድሩ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መመለስ ያለበት መሆኑን፣ በዚህ ወቅት መመለስ ያልቻሉ እንደሆነ በባንኩ ብድር የተገዙ ማሽነሪዎችና ንብረቶችን ባንኩ መውረስ እንደሚችል በመመርያው ዝርዝር ውስጥ ተቀምጧል፡፡

  መንግሥት ለዚህ ፈንድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ንግድ ባንክ እንዲመድብ ማድረጉን የተናገሩት ምንጮች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና አቶ ሱፊያን አህመድ ግን ባንኩ ከሚያወጣው በተጨማሪ ለማግኘት መቀመጫቸው አዲስ አበባ ከሆነ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  እነዚህ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች በወጣቶች ልማት ዙሪያ ያሏቸውን ፕሮጀክቶች መንግሥት ከቀረፀው አዲሱ የሥራ ፈጠራ ዕቅድ ጋር እንዲያስማሙ፣ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

  በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የሁለቱ ምክር ቤቶችን የሥራ ዘመን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፣ መንግሥት ትኩረት እንዲያደርግባቸው ካሳሰቡት መካከል አርሶ አደሮች በልማት ምክንያት ሲነሱ የሚከፈላቸው የካሳ መጠን የፖለቲካ ቀውሱ አንዱ ምክንያት በመሆኑ እንዲሻሻል ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ረገድ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በፌዴራል ደረጃ አንድ ወጥ የካሳ ሥርዓት አጥንቶ ተግባራዊ እንዲያደርግ መታዘዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  በክልል ደረጃ ኦሮሚያ የካሳ ክፍያ ምጣኔውን በማሻሻል ላይ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ የመሬት ማስለቀቅና መልሶ ማልማት ኤጀንሲ ደግሞ ሰሞኑን ተግባራዊ ያደረገው አዲስ የካሳ ክፍያ መኖሩ ተገልጿል፡፡

  በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ሲፈናቀሉ ለሚያጡት የመሬት ይዞታና የግብርና ምርት በሔክታር እስከ 500 ሺሕ ብር እንዲከፈል የሚያደርግ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ከዚህ ቀደም መንግሥት ለሥራ ፈጠራ በማለት የብድርና ቁጠባ ተቋማት በኩል ለወጣቶች ያመቻቸው ብድር ሳይከፈል መቅረቱንና የተሳካ የሥራ ፈጠራ ዕድል መፍጠር አለመቻሉን የሚረዱ አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁንም በንግድ ባንክ በኩል የሚቀርበው ብድር ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ የሥራ ዕድሉ አይፈጠርም የሚል ሥጋት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡      

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...