Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የመንግሥት ሹማምንት የተጠያቂነት ዳር ድንበር በግልጽ ይታወቅ!

  የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት በማያወላዳ መንገድ አስፍሮአል፡፡ በዚህ የሕገ መንግሥት አንቀጽ መሠረት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ መሆኑን፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት እንደሚቻልና ዝርዝሩም በሕግ እንደሚወሰን ያስታውቃል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ይህንን የመሰለ ተጠያቂነትን በግልጽ የሚያብራራ ሕገ መንግሥት እያለ፣ የመንግሥት ሹማምንት የተጠያቂነት ወሰን ምን ድረስ እንደሆነ ግራ ሲያጋባ ይታያል፡፡ የተወሰኑ ማሳያዎችን እንነጋገርባቸዋለን፡፡

  በብዙዎቹ መንግሥታዊ መሥርያ ቤቶች ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ከወረቀት ጌጥነት የዘለለ፣ ለታይታ ያህል ከሚደረጉ ዲስኩሮች ያለፈ ቦታ የላቸውም፡፡ ብዙዎቹ ተቋማት በማቋቋሚያ አዋጃቸው ሥልጣንና ኃላፊነታቸው በዝርዝር ቢቀመጥም፣ የተሿሚዎች ኃላፊነትና ግዴታ ቢሠፍርም፣ የሠራተኞች የሥራ መደብና ሥምሪት በደንቦችና በመመርያዎች ውስጥ ቢካተትም ከመርህ ይልቅ ገጠመኝ ይበዛል፡፡ በመርህ መመራት ይቀርና በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ሥር የሚተዳደሩ ተቋማት ይበዛሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ከመልካም አስተዳደር መጓደል ጀምሮ አገርን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚከቱ ብልሹ አሠራሮች ይሰፍናሉ፡፡ ይህም በተግባር በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ አሁንም እየታየ ነው፡፡

  የብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ችግር የሚጀምረው ከሕዝብ ግንኙነት ክፍሎቻቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባልደረቦቻቸው መረጃ ከመስጠት ይልቅ መደበቅ፣ ተቋማቱ እንዲጠናከሩ የሚበጁ አማራጮችን ከመፈለግ ይልቅ በዘፈቀደ እንዲመሩ ማድረግ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በተቋማቱ ውስጥ የሚከናወኑ ድርጊቶችን አለማወቅና ለቦታው ያለመመጠን ችግር ይታይባቸዋል፡፡ አንድ ችግር ሲፈጠር አለቆቻቸውን በቂ መረጃ አስታጥቀው በግልጽነት መርህ መሠረት ማብራሪያ እንዲሰጡ ከማድረግ ይልቅ፣ ከሕዝብ ዕይታ እንዲሸሹ በማድረግ በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በሕዝቡ ውስጥ መደናገር ይፈጥራሉ፡፡ መረጃዎችን በመስጠት ግልጽነት እንዲኖር ከማድረግ በላይ፣ ለተቋማቱም መልካም ስምና ዝና መፍጠር ሲገባቸው መሰናክል ይሆናሉ፡፡ በዚህ መሀል መረጃ አፈትልኮ ሲወጣ ለማስተባበል ሲሉ አቧራ ያስነሳሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ የደካማ የሕዝብ ግንኙነት መሪዎች ድርጊት ብዙዎቹን መንግሥታዊ ተቋማት ተዓማኒነት ከማሳጣቱም በተጨማሪ፣ ሕገጦች እንዲነግሡና ሙስና እንዲንሰራፋ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል፡፡

  በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ተሰግስገው ከግል ጥቅማቸው በላይ ማሰብ የተሳናቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲጠፋ በማድረግ፣ ቅን ሠራተኞች የሚፈለግባቸውን የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ እያጠፉ ነው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ለሚታየው የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ መቆርቆዝ ዋናው ምክንያት፣ ለሕዝብ ደንታ የሌላቸውና በሙስና የተዘፈቁ ኃይሎች መበራከት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲና መንግሥት በአንድ በኩል በጥልቅ ለመታደስ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በየጊዜው ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ለሕግ የማይገዙ ኃይሎች የአገር ሀብት ይዘርፋሉ፡፡ በሕዝብ ላይ ይቀልዳሉ፡፡ በቅርቡ በ15 ሲኖትራኮች የተጫነ አርማታ ብረት መዘረፉ ተሰማ፡፡ ዘራፊዎቹ ከቀናት በኋላ በፖሊስ ተይዘው እየተመረመሩ መሆናቸውም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ዝርፊያው የተፈጸመበት ተቋም ኃላፊዎችስ እየተጠየቁ ነው? ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት አያስጠይቅም? ወይስ የተጠያቂነት ወሰኑ ከቦታ ቦታ ይለያያል? ሕግ ይከበር፡፡

  የግልጽነትና የተጠያቂነት ጉዳይ ሲነሳ ሌሎች የአገር ሀብቶች የሚጠበቁት እንዴት ነው? በአገር ሀብት ላይ ዝርፊያ ሲፈጸምም ሆነ አገርን የሚጎዱ ድርጊቶች ሲከሰቱ በመጀመሪያ ተጠያቂነት ያለባቸው ተቋማትን የሚመሩ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ እንጂ በገዛ ፈቃድም ከኃላፊነት በመልቀቅ ለተጠያቂነት ዝግጁ መሆን እንኳንስ በአውሮፓና በአሜሪካ በአፍሪካም እየተለመደ ነው፡፡ አገር የሚመራው በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው እርስ በርስ ከሚያደርጉት ቁጥጥር በተጨማሪ፣ ሚዲያው በትክክል እየተናበቡ መሥራታቸውን እየተከታተለ ለሕዝብ ይዘግባል፡፡ ባለመታደል ግን አገር በዘፈቀደ እንድትመራ የሚፈልጉ ወገኖች የሚዲያውን ሚና እያንኳሰሱ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲጠፉ ያበረታታሉ፡፡ የሕገ መንግሥቱ ትዕዛዝ እየተጣሰ የግለሰቦች ሕገወጥነት ሲበረታ፣ ለሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ፀር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

  አሁንም በድጋሚ አፅንኦት የሚሰጠው የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ይከናወን፡፡ ኃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣ ሹም ተጠያቂ ይደረግ፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ ከፈጻሚዎቹ ጀምሮ አስፈጻሚዎቹ ድረስ ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መምራት ያቃተው ተሿሚ በደካማ የሕዝብ ግንኙነት አማካይነት ከሚንፈራገጥ ይልቅ፣ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት መርህ ራሱን ያስገዛ፡፡ መረጃን መደበቅና ለማድበስበስ መሞከር በራሱ የብልሹ አሠራር ውጤት ነው፡፡ በየትኛውም መንግሥታዊ ተቋም ውስጥ ዝርፊያ ሲፈጸም፣ አስተዳደራዊ በደል ሲደርስ፣ ሥራን በአግባቡ መምራት ሳይቻል ሲቀር፣ ለአገርና ለሕዝብ አደገኛ የሆነ ክስተት ሲያጋጥም፣ ወዘተ. ከምንም በፊት መጠየቅ ያለባቸው ኃላፊዎች መሆን እንዳለባቸው ይታወቅ፡፡ ይህ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 ያሰፈረው ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ ሀቅ ጋር መተናነቅ ደግሞ ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም የሹማምንት የተጠያቂነት ዳር ድንበሩ በግልጽ ይታወቅ!        

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...