Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በዓለም አቀፍ ደረጃ እያንሰራራ ላለው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥጋት መዘጋጀት ያስፈልጋል!

  በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋነኛው አነጋጋሪ ጉዳይ የቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሰውየው ሥልጣን በይፋ ከሚጨብጡበት ቀን አንስቶ ስለሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ጭምር ነው፡፡ ምንም እንኳ የአሜሪካ ጥብቅ ሕጎችና ከሁለት ክፍለ ዘመናት በላይ የቆየው ሥርዓት በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነቡ ናቸው ቢባልም፣ እሳቸውና በአውሮፓ ያሉ መሰሎቻቸው የጀመሯቸው ከመደበኛው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ባህል ያፈነገጡ አካሄዶች የቀኝ አክራሪ ኃይሎች እንዲያንሰራሩ እያደረጉ ነው፡፡ የቀኝ አክራሪ ኃይሎች ‹‹ፖፑሊዝም›› በሚባለው እንቅስቃሴ አማካይነት በመደበኛው ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ተቀባይነት ያላቸውን አሠራሮች በመጣስ ለአምባገነንነት የተመቻቹ ከባቢዎችን ይፈጥራሉ የሚሉ ሥጋቶች ይሰማሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ መደበኛ ሚዲያዎችን የሚያጣጥሉና በሐሰተኝነት የሚወነጅሉ ቅስቀሳዎች በብዛት እየተሰሙ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የፋሽስቶችና የናዚዎች እንቅስቃሴ በአውሮፓ የተከሰተው በዚህ መንገድ እንደሆነም ይወሳል፡፡ አሁን በአሜሪካና በተወሰኑ የአውሮፓ አገሮች መሰል እንቅስቃሴዎች በይፋ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ይህ ሥጋት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮችን ይመለከታል፡፡

  የአውሮፓ የቀኝ አክራሪ ኃይሎች በተለያዩ ማኅበራት ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመደራጀት በስደተኞች ላይ ያላቸውን ጥላቻና ተቃውሞ በማሰማት ይታወቃሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት ልዩነቶች ላይ ተመሥርተው በሰሜን አሜሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ ወዘተ. የተመሠረቱ ተመሳሳይ ፓርቲዎችም መገለጫቸው ጥላቻ ነው፡፡ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻቸውን በጀመሩበት ወቅት በጥቁሮች፣ በላቲኖች፣ በሙስሊሞችና በአጠቃላይ የመኖሪያ ፈቃድ በሌላቸው ስደተኞች ላይ ይሰነዝሩዋቸው የነበሩት በስድብ የታጀቡ ዘለፋዎች የዚህን የአክራሪ ቀኝ ኃይል ጎራ ሐሳብ የሚያቀነቅኑ ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳም በአሁኑ ጊዜ አሜሪካም ሆነች የተቀረው ዓለም የዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ዕርምጃዎች ምን ይሆኑ? ለሚለው ጥያቄ መጪውን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ የእሳቸው አድናቂ የሆኑ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ የሚገኙ መሰሎቻቸው ውዳሴ እያጎረፉላቸው ሲሆን፣ በየአገሮቹ በሚደረጉ ምርጫዎች ከፍተኛ መነቃቃት እያገኙ እንደሆነ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ይህ የዓለምን ባልታሰበ ሁኔታ መለወጥ አመላካች ነው፡፡ አሳሳቢም ነው፡፡

  በእኛም አገር እንደ መንግሥት፣ ሕዝብና አገር እያንሰራራ ካለው የቀኝ አክራሪ ኃይሎች ሥጋት አንፃር ከወዲሁ መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ዘመን እንደ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከምዕራቡ ወደ ምሥራቁ ወይም ከምሥራቁ ወደ ምዕራቡ ጎራ የሚገላበጡበት ሳይሆን፣ በተጠናና በተብራራ መንገድ የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ መረዳትና ለፖሊሲ ማስተካከያ መዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ አሜሪካ ፊቷን ስታዞር ወደ ቻይና፣ የአውሮፓ ኅብረት ሲያኮርፍ ወደ ቱርክ ወይም ሩሲያ ብለው የሚገላገሉት አይደለም፡፡ በሁለትዮሽም ሆነ በባለ ብዙ ወገን ግንኙነት ወቅት ሁሉም ተደራዳሪ ተቋምና አገር የሚቀርበው ከወቅቱ የዓለም አሠላለፍ አኳያ የተመረጠ ጥቅሙን በማስላት ነው፡፡ ከመደበኛው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አካሄድ ያፈነገጡ አዳዲስ ግንኙነቶች መፈጠር ሲጀምሩ ባይተዋር ከመሆን ከወዲሁ መዘጋጀት የግድ ይሆናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መደበኛው ግንኙነት ከአሁኑ ችግር እየገጠመው ስለሆነ ነው፡፡

  ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመጀመርያ ቀን የቢሮ ውሎአቸው የትራንስ ፓስፊክ አጋርነት ስምምነትን ውድቅ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ ይህ ዕርምጃ አሜሪካ በእስያ አካባቢ የነበራትን የንግድ ግንኙነትና የበላይነት ለቻይና አሳልፎ እንደሚሰጥ ቢወተወትም ሰሚ አላገኘም፡፡ አሜሪካ ሻምፒዮን ልትሆንበት ተዘጋጅታበት የነበረውና በቅርቡ ያፀደቀችው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተደረገ ስምምነት በትራምፕ መንታ አቋም ምክንያት ውሉ አለየለትም፡፡ ከታዳጊ አገሮች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትና ከዚህ  ቀደም የተፈጸሙ የንግድ ስምምነቶች ለአሜሪካ ጠቃሚ ሆነው ካልተገኙ ሊሰረዙ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሳቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ ታዳጊ አገሮች ይጎዳሉ፡፡ በአውሮፓ በተለያዩ አገሮች ሥልጣን ለመያዝ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ያሉትም ሆኑ ሌሎች ጊዜያቸውን የሚጠብቁ የቀኝ አክራሪ ኃይሎች፣ ዛሬ የተናገሩትን ነገ ከሚሽሩት ትራምፕ ጋር የአዲሱን ዓለም ሥርዓት ለመቅረፅ ተዘጋጅተዋል፡፡ በ1930ዎቹ የተፈጠሩት የፋሽስትና የናዚ ፓርቲዎች ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት የሆኑት በዚህ ዓይነቱ መሳሳብ ነበር፡፡ ይህንን መሳሳብ ያቀላጥፉ የነበሩት ወግ አጥባቂ ሚዲያዎች ዓይነት በዚህ ዘመንም በብዛት መታየት ጀምረዋል፡፡ ያኔ የወዳጅና የጠላት ጎራ የተለየው ጦርነቱ ከተጫረ በኋላ እንደነበር መዘንጋት አይገባም፡፡ እንደ አገር፣ ሕዝብና መንግሥት የውስጥ ችግሮችን በመግባባት በመፍታት ለመጪው ጊዜ መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡  

  በዚህ ዘመን ፖለቲካ የቀኝና የግራ ዘመሞች ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ በስመ ዴሞክራሲ ሥልጣን ላይ የሚወጡ አክራሪ ኃይሎች የሚንሰራፉበት እንደሆነ ምልክቶች ከወዲሁ እየታዩ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ ድንገት ብልጭ ያለው የነጭ የበላይነት ስሜትና በአውሮፓ እየታየ ያለው ተመሳሳይ ፍላጎት ብዙ ይናገራል፡፡ ይህ ደግሞ ለምዕራቡ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር እንደ ʻአብዮታዊ ትራንስፎርሜሽንʼ እየተመዘገበ ሲሆን፣ ከመደበኛው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥርዓት ጋር የተጣላ የአክራሪ ቀኝ ኃይሎች ‹‹ፖፑሊዝም›› እየፈጠረ መሆኑ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ይህ ንቅናቄ ከዓለም አቀፍ ግንኙነት የሰጥቶ መቀበል መርህ በማፈንገጥ በገዛ አገር ጥቅም ላይ ብቻ የማያነጣጥር ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ግሎባላይዜሽንን ከመድረኩ በመገፍተር ለዓለም አዲስ ገጽታ ያላብሳል፡፡ በዚህ ሒደት የሚቀየረው ዓለም ደግሞ በአዲስ ቅኝት ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ለውጥ ወይም አሠላለፍ ይሻል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ የወግ አጥባቂዎች ሚዲያዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በመነቃቃት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የነጮችን የበላይነት መስበክ፣ ሌሎችን ማንቋሸሽና የመሳሰሉት የአደገኛው ክስተት ማመላከቻ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሒደት ብሔርተኝነትን፣ ማኅበራዊ ወግ አጥባቂነትንና የፀረ ስደተኝነት ስሜትን እንዲጠናከሩ እያደረገ ነው፡፡

  አሁን በፍጥነት በመለወጥ ላይ ባለው ዓለም በተለያዩ አገሮች ውስጥ በፖለቲካ ልሂቃንና ተቋማት ላይ ተቃውሞ እየበረታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በርዕዮተ ዓለም፣ በፖሊሲ፣ በስትራቴጂዎችና በተለያዩ ጥቅሞች ተፃራሪ አቋም የነበራቸው ወገኖች በቀኝ አክራሪነት አስተሳሰብ የጋራ አጀንዳ እያራመዱ ነው፡፡ ከተለመዱት የፖለቲካ ፓርቲ ባህሎችና ልማዶች ወጣ ባለ መንገድ ራሳቸውን የሚገልጹት የግራም የቀኝም ወገን አለመሆናቸውን፣ ነገር ግን አክራሪ ቀኝ ክንፍ መሆናቸውን ነው፡፡ ሌሎች በጥርጣሬ የሚያዩዋቸውና ገለጻቸው ግራ የሚያጋባቸው ደግሞ፣ ‹‹በተውገረገሩ ቃላት የተሸፈኑ አዲሶቹ አምባገነኖች፣ ፋሽስቶች፣ ናዚዎች፣ ብሔርተኞች …›› በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ እነ ዶናልድ ትራምፕም ሆኑ በአውሮፓ በማቆጥቆጥ ላይ ያሉ ኃይሎች ግን የዓለምን ገጽታ እንደሚለውጡና ከዚህ ቀደም የነበሩ ግንኙነቶችን በሌላ ማዕቀፍ ሊተኩ እንደሚችሉ ከወዲሁ የብዙዎች ሥጋት ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ መንግሥት ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር መዘጋጀት ተገቢ የሚሆነው!          

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...