Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የሶማሊያን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ምርጫና የአልሸባብ እንቅስቃሴ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  በ1983 ዓ.ም. የዚያድ ባሬ መንግሥት ከፈራረሰ በኋላ፣ ሶማሊያ ለረዥም ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነትና በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ አልፋለች፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የመጀመሪያውን አገራዊ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡

  የዓለም አቀፉን ሚዲያ ቀልብ የሚስበው የሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ አለመረጋጋት ብቻም አይደለም፡፡ የዚያድ ባሬ መንግሥት ከተባረረ በኋላ መንግሥት አልባ ሆና ለረዥም ጊዜያት የዘለቀችው ሶማሊያ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ የዓለምን ሰላምና ደኅንነት እያናጋ ያለው የሽብርተኝነት መናኸሪያም ሆና ነበር፡፡

  9/11 በመባል በሚታወቀውና እ.ኤ.አ. በ2001 በአሜሪካ በተፈጸመው ጥቃትና በኬንያና በታንዛንያ ኤምባሲዎቿ የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆነችው አሜሪካ፣ ሽብርተኛነትን በመዋጋት ግንባር ቀደም ሆና የምትንቀሳቀስ አገር ናት፡፡ ነገር ግን የሶማሊያ ሁኔታ የራስ ምታት ሆኖባት ቆይቷል፡፡

  ከመቼውም ጊዜ በላይ ግን የሶማሊያ ኢስላማዊ ቡድኖች እ.ኤ.አ. በ1999 እንደፈጠሩት ኅብረት ተደራጅተው አያውቁም፡፡ በወቅቱ የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤት ኅብረት በመባል የሚታወቀው ቡድን መላ የደቡብ ሶማሊያ ክፍል ተቆጣጥሮ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ እስከማወጅ የደረሰበት ሁኔታ አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም የቡድኑን መገስገስ በትዕግሥት አልተመለከተው ከአንድም ሁለቴ የሽግግር መንግሥቱን ግብዣ እንደ ሽፋን በመጠቀም ጣልቃ በመግባት ድርጅቱን መበታተን ችሎ ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ የኅብረቱ የወጣቶች ክንፍ እንደ አዲስ በመደራጀት፣ አልሸባብ የተባለውን የሽምቅ ተዋጊ ቡድን አቋቁሞ ይኼው እስከ ዛሬ እየተዋጋ ይገኛል፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን (ተመድ) ዕውቅና ያገኘው ደካማው የሽግግር መንግሥት በወቅቱ ከተለያዩ ጎሳዎች ውክልና አግኝቶ እንዲቋቋም የተደረገው፣ ከመነሻው የኢትዮጵያ መንግሥትና የአሜሪካ መንግሥት ስፖንሰር ባደረጉት የሰላም ሒደት ነበር፡፡

  በኢትዮጵያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትም የአሜሪካ መንግሥት እጅ አለበት ተብሎ ይታማ የነበረ ሲሆን፣ ሁለቱም አገሮች የሽግግር መንግሥቱን ከአሸባሪ ቡድኖች የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳላቸው ሲገልጹ ነበር፡፡ የዘንድሮ የአውሮፓውያን ዓመት ግን ለፌደራላዊ የሽግግር መንግሥቱ ዘመን የሚያበቃበት ነው ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም የሽግግር መንግሥቱን የሚተካ መደበኛ መንግሥት ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ምርጫው በኅዳርና በታኅሳስ ወራት ላይ ይከናወናል፡፡

  ሒደቱ ምን ይመስላል?

  እ.ኤ.አ በ2012 የተቋቋመው ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ፓርላማ ከ135 የጎሳ መሪዎች የተውጣጣ ነው፡፡ በቅርቡ በሚካሄደው ምርጫ ግን የታህታይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ወደ 275 ከፍ የሚል ሲሆን፣ ለላዕላይ ምክር ቤት ደግሞ 54 አባላት ይመረጣሉ፡፡ ይኼው ምክር ቤት ዋናው የአገሪቱ የሥልጣን ባለቤት ተደርጎ የሚታይ ነው፡፡

  የምርጫ ሒደቱ የውክልናና የቀጥተኛ ግጽታ ሲኖረው፣ በአገሪቱ ባለው አለመረጋጋትና የፀጥታ ሁኔታ ሳቢያ በቀጥታ ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ ወደ ውክልና  ምርጫ እንዲተካ ተደርጓል፡፡ ያም ሆነ ይህ ባለፈው መስከረም ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ምርጫ ሁለት ጊዜ ተላልፎ በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ተመራጭ የፓርላማ አባላት በመጪው ታኅሳስ ወር የአገሪቱን ፕሬዘዳንት ይመርጣሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

  የተለያዩ አካላት የምርጫው ሒደት በተለያዩ ውስጣዊና ውጪያዊ ምክንያቶች ሊደናቀፍ ይችላል በማለት ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የአሁኑ ፓርላማ አባል የሆኑት አብዲወሊ ካንያር ግን ሒደቱ ላይ እስከ አሁን የቀረበ ከፍተኛ ቅሬታ አለመኖሩን ለአሜካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ ምርጫ ነውና ቅሬታ አይኖርም ብሎ መገመት ይከብዳል፤›› ብለዋል፡፡ በአደጉት አገሮች ሳይቀር ዕንቅፋቶችና ቅሬታዎች በምርጫ ወቅት እንደሚቀርቡም አስታውሰዋል፡፡ የተመድ ዋና ጸሐፊ የሶማሊያ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ማይክል ክቲንግ ግን፣ ምርጫውን በማካሄድ ሒደት አንዳንድ እንቅፋቶች እየገጠሙ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡

  መልዕክተኛው እንደሚሉት ከሆነ፣ ከሦስት አሥርት ዓመታት ጦርነትና ሕግ አልባነት ጠቅልላ ለመወጣት በመጣር ላይ ባለችው ሶማሊያ በተለይ አልሸባብ ከተባለው የሽምቅ ተዋጊ አሸባሪ ቡድን እያደረሰ ያለው የፀጥታ መስተጓጎል ሒደቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡ ሒደቱን በተገቢ መንገድ ሊያከናውኑ የሚችሉ ተቋማት ስለመኖራቸውም ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ‹‹በጥርጣሬ የምመለከተው ጉዳይ ቢሆንም፣ በጥሩ ሁኔታ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ምናልባት ግን አንድ ሰው እንዳለኝ ከሆነ የምርጫ ሒደቱ እስከዛሬ በምድራችን ከታዩ የምርጫ ሒደቶች እጅግ የተወሳሰበ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

  አካሄዱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱም አይጠፉም፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር አብዲ ስማታር የተባሉ በሜኔሶታ ዩኒቨርሲቲ የመልክዓ ምድር መምህር ሶማሊያዊ፣ ‹‹ይኼ ምርጫ ሳይሆን መረጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎች ቅሬታዎችም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ተመድ፣ የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት ባወጡት የጋራ መግለጫ ከወንጀል፣ ከአሸባሪና ከሁከት ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ስማቸው የሚነሳ ግለሰቦች ለላዕላይ ምክር ቤት ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ያሠጋናል ብለዋል፡፡

  ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ግን ከዕጩዎቹ መካከል ባለፉት አምስት ዓመታት በፍርድ ቤት ወንጀለኛ ሆኖ ያልተገኘ ግለሰብን ከሒደቱ ለማግለል የሚያስችል መንገድ የለም ይላሉ፡፡

  አልሸባብና ምርጫ

  የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ከዘለቁ ጊዜ ጀምሮም ሆነ በኋላ፣ የአፍሪካ ኅብረት  ሰላም አስከባሪ ኃይል በአገሪቱ ከተሰማራ ጊዜ ጀምሮ አልሸባብ ከዋና ዋና የአገሪቱ ይዞታዎች ለቆ ወጥቶ ነበር፡፡ ከአካባቢው የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ቡድኑ ከፍተኛ ሽንፈት እየገጠመው እንደ ድርጅት ህልውናው አደጋ ላይ ወድቆ ነበር፡፡

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሶማሊያ ምርጫ እየቀረበ በሄደ ቁጥር፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቁጥጥራቸው ሥር የነበሩ የአገሪቱን ደቡባዊ ዋና ከተሞች ለቀው እየወጡ መሆናቸው እየተዘገበ ነው፡፡ እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ለማፈግፈግ ውሳኔው የገፋፋው ነገር ግልጽ ባይሆንም ዕርምጃው ለአልሸባብ መልካም ዕድል እንደፈጠረለት እየተነገረ ነው፡፡

  አልጄሪያዊው ጋዜጠኛ ሐምዛ አህመድ በቅርቡ የኢትዮጵያ ወታደሮች የለቀቁዋቸው አካባቢዎች ድረስ በመሄድ ባጠናቀረው ዘገባ፣ ከ4,500 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአሥር በላይ ዋና ዋና ከተሞችን ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ለቀው መውጣታቸውን ገልጿል፡፡

  አራቱ ከተሞች የተለቀቁት ደግሞ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ነው ብሏል፡፡ እንደ ሐምዛ ሪፖርት፣ አልሸባብ አንዳች ጥይት መተኮስ ሳያስፈልገው የተለቀቁ አካባቢዎች መልሰው በመያዝ ላይ ናቸው፡፡

       ሐምዛ ያነጋገራቸው የአልሸባብ መሪዎች የኢትዮጵያ ወታደሮች አካባቢውን ለቀው እየወጡ ያሉት በአገራቸው ውስጥ በተፈጠረው አመፅ ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ፡፡

  የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ግን፣ ኢትዮጵያ ወታደሮችዋን ለማፈግፈግ የተገደደችው አገር ውስጥ ካለው ሁኔታ የሚያያዝ እንዳልሆነ ተናግረው ነበር፡፡ እሳቸው እንዳሉት፣ መንግሥት ዕርምጃው ለመውሰድ የተገደደው በፋይናንስ ምክንያት ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተራው የራሱን አስተዋጽኦ ሊጫወት ይገባል ብለዋል፡፡

  ባለፈው ሳምንት ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ፣ አልሸባብ የተባለው የሽብር ቡድን እያደረገ በሚገኘው መስፋፋት የኢትዮጵያ መንግሥት ሥጋት የለውም ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት አሁንም በሥራው ላይ መሆኑን፣ ከዚህ ውጪ ያለው ደግሞ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጥንቃቄና ኃላፊነት የተሞላበት ስለሆነ የአልሸባብ መስፋፋት በኢትዮጵያ ላይም ሆነ በአካባቢው ሥጋት አይፈጥርም ብለዋል፡፡ 

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -