Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበአልሸባብ ተልዕኮ የተለያዩ ተቋማትን በፈንጂ ሊያጠፉ ነበር የተባሉ ተከሳሾች ተፈረደባቸው

  በአልሸባብ ተልዕኮ የተለያዩ ተቋማትን በፈንጂ ሊያጠፉ ነበር የተባሉ ተከሳሾች ተፈረደባቸው

  ቀን:

  የአልሸባብን ተልዕኮ ለማስፈጸምና የአጥፍቶ መጥፋት የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ኤድናሞልን፣ ፍሬንድሺፕን፣ የመርካቶ የገበያ ማዕከላትንና አዲስ አበባ ስታዲየምን ዒላማ አድርገዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው ሰባት ተከሳሾች፣ በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡

  በነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም. በተጠቀሱት ተቋማት በተለያዩ በመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ ፈንጂውን በአጥፍቶ አጥፊዎች አማካይነት ለማፈንዳት ከተስማሙ በኋላ፣ አብዲና ሐሰን የተባሉ አጥፍቶ አጥፊዎች ፈንጂውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም መሄዳቸው በፍርዱ ተጠቅሷል፡፡ አጥፍቶ አጥፊዎቹ ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. የተነሱበትን ዓላማ ለማሳካት ወደ ስታዲየም የሄዱት በዕለቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ላይ የሚሰበሰቡትን ተመልካቾች ለመጉዳት የነበረ ቢሆንም፣ ፖሊስ ወደ ስታዲየም በሚገቡ ተመልካቾች ላይ ፍተሻ እንደሚያደርግ መረጃ ደርሷቸው መመለሳቸውንም ፍርዱ አካቷል፡፡ አጥፍቶ ጠፊዎቹ ወደ ተከራዩበት ቦሌ ሚካኤል አካባቢ እንደተመለሱ የያዙት ፈንጂ ፈንድቶ፣ ሁለቱን አጥፍቶ ጠፊዎች በመግደል ወ/ሮ ሰርቤሳ ሐሰን የተባሉ የቤት አከራይን ዘጠኝ ሰርቪስ ቤቶች ማውደሙን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

  ፍርደኞቹ መሐመድ አብዱራህማን ቅጽል ስም መሐመድ ሲዳ (ሶማሊያዊ)፣ መሐመድ አህመድ ቅጽል ስም ዓረብ (ሶማሊያዊ)፣ መሐመድ አብዱላሒ ቅጽል ስም መሐመድ ጆን (ሶማሊያዊ)፣ መሐመድ ዓሊ ቅጽል ስም ደገ ወይኒ (ሶማሊያዊ)፣ ኡስማን ሐሰን ቅጽል ስም ቅዱስ (ሶማሊያዊ)፣ መሐመድ አዌይስ ቅጽል ስም በቆርቶማ (ሶማሊያዊ) እና ሐሰን አብዱልቃድር (ሶማሊያዊ) ሲሆኑ፣ ከዘጠኝ እስከ ሁለት ዓመታት ከስምንት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ፈርዶባቸዋል፡፡

  ፍርደኞቹ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ የአልሸባብ አባል በመሆን በሶማሊያ ግዛት ውስጥ የሽብር፣ የወታደራዊ፣ የፖለቲካ፣ የመረጃ አሰባሰብና የፈንጂ ጥቃት እንዴት ማድረስ እንደሚቻል ሥልጠና የወሰዱ መሆናቸውን፣ ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ማረጋገጡን ፍርዱ ይገልጻል፡፡

  ፍርደኞቹ በሞቃዲሾ ከተማ ሲንቀሳቀሱ ከቆዩ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት፣ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ቤት ተከራይተው እንደነበር ተመስክሮባቸዋል፡፡ በተከራዩበት ቤት በኅቡዕ በመደራጀት የአልሸባብን ተልዕኮና ዓላማ ለማስፈጸም የሥራ ክፍፍል በማድረግ፣ ከላይ በተጠቀሱት ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ አጥፍቶ ጠፊ የሆኑ የአሸባሪ ቡድኑ አባላትን ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ ፈንጅ ይዘው እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ አብዲና ሐሰን የተባሉት አጥፍቶ ጠፊዎች ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. በተከራዩበት ቤት በእጃቸው ላይ የነበረው ፈንጂ ፈንድቶ ሕይወታቸው ማለፉንም ፍርዱ ገልጿል፡፡

  በቅጽል ስሙ መሐመድ ሲዶ የሚባለው መሐመድ አብዱራህማን በ1997 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ተመልሶ ሞቃዲሾ በመሄድ፣ ወሎ አብዱላሂ በተባለ የአልሸባብ አመራር ተመልምሎ ወታደራዊ ሥልጠና ከወሰደ በኋላ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎችን እንቅስቃሴ እንዲያጠና ተልዕኮ ተሰጥቶት በ2001 ዓ.ም. መመለሱም ተመስክሮበታል፡፡

  ቦሌ ሚካኤል አካባቢ በተከራየው ቤት ለሽፋን ሱቅ በመክፈት የአልሸባብን ተልዕኮ የሚያስፈጽም ቡድን በህቡዕ በማደራጀትና ከሞቃዲሾ ወደ ኢትዮጵያ የሚመላለሱ አባላትን በመቀበል የቡድኑ የበላይ ኃላፊ፣ የፋይናንስ ኃላፊ፣ ለአልሸባብ አባላት መረጃ አቀባይ በመሆን ጥቃት የሚፈጽምባቸውን ቦታዎች ለመምረጥ ሲንቀሳቀስ እንደነበር በፍርዱ ተገልጿል፡፡ ፍርደኛው መርካቶ የገበያ ማዕከል፣ ቦሌ ፍሬንድሺፕ የገበያ ማዕከል፣ ኤድናሞል፣ አዲስ አበባ ስታዲየምና የተለያዩ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶችን በአጥፍቶ ጠፊዎች ለማውደም መዘጋጀቱንና ለአልሸባብ አመራሮች ሲገልጽ መቆየቱም ተብራርቷል፡፡

  ሐሰን የተባለው አጥፍቶ ጠፊ ቶጎ ውጫሌ ከሚባለው የኢትዮጵያ ግዛት ከነፈንጂው በ2005 ዓ.ም. ሐምሌ ወር አዲስ አበባ መግባቱንና ከግብረ አበሮቹ ጋር በነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም. ፈንጂውን መጀመርያ፣ የኢትዮጵያና የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድኖች በሚጫወቱበት ዕለት ለማፈንዳት በህቡዕ መስማማታቸውንም ፍርዱ ይገልጻል፡፡ ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረገውን ውደድር ለመመልከት በሚገባው ሕዝብ ላይ ለመፈጸም ከተስማሙ በኋላ፣ ፈንጂውን ቦሌ ሚካኤል በተከራዩበት ቤት ማስቀመጣቸውንም አክሏል፡፡ መሐመድ አህመድ የተባለውም ፍርደኛ በ2001 ዓ.ም. ከናይሮቢ በአልሸባብ ተመልምሎ ናይሮቢ ዌስት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመረጃ አሰባሰብና አሠለጣጠን ሥልጠና ከወሰደ በኋላ፣ በነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም. በቶጎ ውጫሌ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባቱንም ፍርዱ ያብራራል፡፡ ሁሉም ፍርደኞች የተለያዩ ሥልጠናዎች በማድረግ የአልሸባብን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3፣4(1ሀ) እና አንቀጽ 7(1)ን መተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ማረጋገጥ በመቻሉ፣ ጥፋተኛ መባላቸውን ፍርዱ ያክላል፡፡ ፍርደኞቹም ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ የተወሰነው ተይዞላቸው፣ አንደኛ ተከሳሽ በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት፣ ከሁለት እስከ አራተኛ ያሉ ተከሰሾች እያንዳንዳቸው በስምንት ዓመት ጽኑ እስራት፣ ስድስተኛ ተከሳሽ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት፣ ሰባተኛ ተከሳሽ በስድስት ዓመታት ጽኑ እስራትና ስምንተኛ ተከሳሽ በሁለት ዓመት ከስምንት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ስምንተኛ ተከሳሽ የእስራት ጊዜውን ከጨረሰ በኋላ የሚፈለግ ካልሆነ ከእስር እንዲፈታ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...