Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ከአቢሲኒያ ባንክ ይዞታ ተቀንሶ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንዲሰጥ ተወሰነ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  አቢሲኒያ ባንክ ለሕንፃ ግንባታ በግዥ ከተረከበው ይዞታው ላይ 1,848 ካሬ ሜትር ቦታ ተቀንሶ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የቢሮ ማስፋፊያ ግንባታ እንዲሰጥ መወሰኑ ተገለጸ፡፡ ባንኩ ቦታውንም እንዲያስረክብ ተጠይቋል፡፡

  ባንኩ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው፣ ተቀንሶ ይሰጥ የተባለው ፍላሚንጎ አካባቢ ካሉት የባንኩ ሁለት ይዞታዎች ውስጥ ከአንደኛው 4,230 ካሬ ሜትር ስፋት ካለው ቦታ ላይ ነው፡፡

  ባንኩ ይኼንን ቦታ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት እንደገዛው፣ በይዞታው ሥር የነበረና በከተማው ማስተር ፕላን መሠረት ሕንፃ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደነበር፣ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታዬ መሠረት በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

  ይሁን እንጂ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከዚህ ይዞታው ላይ ተቀንሶ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ እንዲውል መወሰኑን አስረድተዋል፡፡ የባንኩ አመራርም ይኼንን ውሳኔ በመቃወም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅሬታውን ማቅረቡ ተገልጿል፡፡

  በአቢሲኒያ ባንክ ይዞታ ሥር ከነበረው ቦታ ተቀንሶ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንዲሰጥ የተወሰነው፣ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦታው እንዲሰጠው ባቀረበው ጥያቄ መሠረት አስተዳደሩ ፈቃድ በመስጠቱ ነው፡፡  

  ባንኩ ግን በቦታው ላይ ሕንፃ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ በመግለጽ ለሌላ አካል ሊሰጥብኝ አይገባም በማለት፣ ለሚመለከታቸው የክፍለ ከተማውና የከተማው አስተዳደር የበላይ የሥራ ኃላፊዎች ደብዳቤ በመጻፍ ጭምር እንዳስታወቁ አቶ ታዬ ገልጸዋል፡፡ ቦታው የሚገኝበት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቢሮ በአካል በመገኘት አቤቱታ ማቅረባቸውን የሚያሳየው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት፣ ሆኖም ይዞታው ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ማስፋፊያነት እንዲሰጥ በከተማው ካቢኔ የተወሰነ በመሆኑ አቤቱታው ተቀባይነት እንደሌለው ምላሽ ተሰጥቷል ብሏል፡፡

  በአስተዳደሩ ውሳኔ መሠረትም ባንኩ ከይዞታው ተቀንሶ ይሰጥ የተባለውን ቦታ እንዲያስረክብ በደብዳቤ ጭምር እንደተገለጸለት በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

  የባንኩ ኃላፊዎች ግን በክፍለ ከተማውና በሌሎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው ቢሮዎች በኩል የተሰጠው መልስ አሳማኝ ባለመሆኑ፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት ከከንቲባው ጋር በአካል በመገናኘት በጉዳዩ ላይ ውይይት እንደተደረገበት የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡ በከንቲባውና በባንኩ አመራሮቹ መካከል በተደረገው ውይይት የከተማው ካቢኔ በባንኩ ይዞታ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት ባንኩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ባንኩ ውሳኔው ታግዶ እንዲቆይና በከተማው አስተዳደር፣ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችና በባንኩ አመራሮች መካከል በጋራ ውይይት እንዲደረግና መፍትሔ ለማስገኘትም ነው ጥያቄውን ያቀረበው፡፡

  ሆኖም ውይይቱን ለማካሄድ ስምምነት ቢደረግም በአገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምክንያት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሊገኙ ባለመቻላቸው ቀጠሮ እየተራዘመ ውይይት ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ውይይት ለማድረግ ሳይቻል ቀርቶ ባንኩ ይዞታውን እንዲያስረክብ በድጋሚ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት በኩል ደብዳቤ እንደተጻፈለት፣ በዚህ ላይም በድጋሚ ባንኩ አቤቱታ ማቅረቡን የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች