Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናኮማንድ ፖስቱ 11,607 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ይፋ ተደረገ

  ኮማንድ ፖስቱ 11,607 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ይፋ ተደረገ

  ቀን:

  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት 11,607 ተጠርጣሪዎችን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አስሮ እንደሚገኝ ፓርላማው ያቋቋመው መርማሪ ቦርድ ይፋ አደረገ፡፡

  ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን እንዲመረምር ከፓርላማ አባላትና ከሕግ ባለሙያዎች የተውጣጡ ሰባት አባላትን የያዘ መርማሪ ቦርድ ማቋቋሙ የሚታወስ ሲሆን፣ ይኸው መርማሪ ቦርድ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የታሳሪዎችን ብዛትና ማንነት የማሳወቅ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

  በዚሁ መሠረትም 11,607 ተጠርጣሪዎች በስድስት ማቆያዎች ታስረው እንደሚገኙ ኅዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡ የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ይፋ እንዳደረጉት፣ ከአጠቃላይ ተጠርጣሪ ታሳሪዎች ውስጥ የሴቶች ቁጥር 347 ነው፡፡

  የታሰሩባቸው ቦታዎችን አስመልክቶ ሲናገሩም በአዋሽ ማዕከል የታሠሩት 1,174 ተጠርጣሪዎች በዋናነት ከፊኒፊኔ፣ ከሰሜን ሸዋና ከምሥራቅ ሸዋ የተውጣጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በጦላይ የጦር ማሠልጠኛ 4,329 ተጠርጣሪዎች ተይዘው የሚገኙ መሆኑን በዋናነት የተያዙትም ከወለጋ፣ ከአርሲና ከምሥራቅ ሸዋ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

  በዋናነት ከጉጂ፣ ከምዕራብና ከምሥራቅ ሐረርጌ የተያዙ 3,048 ተጠርጣሪዎች በዝዋይ መታሠራቸውን፣ 2,114 የሚሆኑ ሌሎች ተጠርጣሪዎች በዋናነትም ከጌዴኦ የተያዙ በዲላ ይርጋለም ማቆያ ታስረው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

  በባህር ዳር ማቆያ ማዕከል ደግሞ 532 ተጠርጣሪዎች እንደሚገኙ፣ እነዚህም በዋናነት የተያዙት ከሰሜንና ምሥራቅ ከጎንደር አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የተያዙ 410 ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ የተለያዩ ማቆያ ቦታዎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

  የታሳሪዎቹን ማንነት በተመለከተም አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸውን፣ በርካታ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች እንደሚገኙበት ነገር ግን ከ18 ዓመታት በታች የታሰረ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

  መርማሪ ቦርዱ መረጃውን ያገኘው በራሱ አጣርቶ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ታደሰ፣ ኮማንድ ፖስቱ ለመርማሪ ቦርዱ ያቀረበው መረጃ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የእስረኞቹን አያያዝና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከዚህ በኋላ ቦርዱ ማጣራት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

  እስረኞቹ የተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች በርካታ ቢሆኑም ከዋና ዋናዎቹ መካከል ሁከት መፍጠር፣ ሰላም እንዳይኖር ሽብር መንዛት፣ የግለሰብ ቤት፣ የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን ማውደም፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ በተለይም ግብይት እንዳይካሄድ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ማድረስ፣ የመግደል ተግባር፣ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን መቅደድና ማቃጠል፣ ሕገወጥ መሣሪያ መሸጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

  የታሳሪዎቹ ዝርዝር ከቅዳሜ ኅዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁሉም የክልል መንግሥታት እንደተላለፈና ክልሎችም ይህንን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...