Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ላይ ለሰበር የቀረበው አቤቱታ ያስቀርባል...

  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ላይ ለሰበር የቀረበው አቤቱታ ያስቀርባል ተባለ

  ቀን:

  የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲስፕሊን ጥሰት ፈጽመዋል በማለት ጥር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሥራ ያሰናበቷቸው ዳኛ፣ ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጣስና ሕጉ የሚለውን ያልተከተለና መሠረታዊ የሕግ ጥሰት የተፈጸመበት መሆኑን ገልጸው፣ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ ያስቀርባል ተባለ፡፡

  ለሰበር ሰሚ ችሎቱ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ከስምንት ዓመታት በላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተለያዩ ችሎቶች ዳኛ ሆነው ይሠሩ የነበሩት አቶ አብረሃ ተጠምቀ ሲሆኑ፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የተለያዩ የዲሲፕሊን ጥፊቶች እንደፈጸሙ መረጋገጡ ተጠቅሶ ከሥራ መሰናበታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመግለጹ፣ ምክር ቤቱ ውሳኔውን አፅድቆታል፡፡

  አቶ አብረሃ ከዳኝነት ሥራ የተሰናበቱበትን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ውሳኔ በመቃወም ለሰበር ሰሚ ችሎት ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት፣ እሳቸው የዲሲፕሊን ጥሰት መፈጸማቸው ተገልጾ የጽሑፍ መልስ ስጡ የተባሉት፣ የቀረበባቸው የዲሲፕሊን ጥፋት ክስ ከነማስረጃው ሊሰጣቸው ሲገባ ይኼ ሳይደረግ ነው፡፡ ይኼ በነጠላ ወረቀት የቀረበ ግልጽ ያልሆነ ክስ ሳይመረመርና እሳቸውም ሳይጠይቁ ጉባዔው ጥፋተኛ ብሎ ውሳኔ እንደሰጣቸው በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡

  የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ውሳኔ የሰጠው ጉልህ የሆነ የሥነ ሥርዓትና ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥሰት ባለበት ሁኔታ መሆኑን የገለጹት አቶ አብረሃ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል በመሆኑ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የወሰነውን ውሳኔ ከማፅደቁ በፊት የክሱን አግባብነትና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው የተከበረ ስለመሆኑ ማጣራት ይገባው እንደነበር በአቤቱታቸው አስረድተዋል፡፡

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ያቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በቀጥታ ተቀብሎ ማፅደቁ ጉዳቱ በእሳቸው ላይ ብቻ የሚወሰን አለመሆኑንና የፍትሕ መጓደል ያስከተለ ውሳኔ መሆኑን አክለዋል፡፡ መሠረታዊ የሕግ ስህተትም እንደተፈጸመባቸው ተገልጾ ወደ ምድብ ሥራቸው እንዲመለሱ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡

  ሰበር ችሎቱ እሳቸው የጠየቈትን ዳኝነት የማይቀበል ከሆነ ወይም ሕጋዊ ምክንያት ካለ፣ ጉባዔው ያቀረበባቸው ክስ ከነማስረጃው ደርሷቸው የመከላከያ መልስና ማስረጃ አቅርበው ክርክር እንዲያደርጉ ውሳኔ እንዲሰጥበት በአማራጭ አመልክተዋል፡፡ ከጉዳዩና ከክርክሩ ባህሪ አንፃር ከጽሑፍ ክርክር በተጨማሪ የቃል ክርክር ማድረጉ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ስለሚጠቅም፣ የቃል ክርክር እንዲያደርጉ እንዲፈቀድላቸው ዘርዘር ያለ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

  አቶ አብረሃ ያቀረቡትን አቤቱታ የመረመረው ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰጠው ትዕዛዝ እንደገጸው፣ አቶ አብረሃ የተከሰሱበት ክስ ግልባጭ ከነዝርዝር ማስረጃው አልደረሳቸውም፡፡ በሰጡት መልስም የሰውና የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር አቅርበው አልታየላቸውም፡፡ በመሆኑም ማስረጃው ሳይሰማ በመታለፉ፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔው ሳይሟላ ውሳኔ በመስጠቱ አቶ አብረሃ የመሰማትና የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው አንፃር ሲታይ አግባብ አለመሆኑን ገልጾ፣ በአግባቡ እንዲጣራ ተጨማሪ ትዕዛዝ በመስጠት ለኅዳር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

     

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...