Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየመጀመሪያ ዙር የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች በቀጣዩ ዙር ሙሉ በሙሉ ይደርሳቸዋል ተባለ

  የመጀመሪያ ዙር የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች በቀጣዩ ዙር ሙሉ በሙሉ ይደርሳቸዋል ተባለ

  ቀን:

  – ዕጣ ወጥቶባቸው የተረፉ ከ3,000 በላይ የ10/90 ቤቶች ድጋሚ ዕጣ ሊወጣባቸው ነው

  የመጀመሪያው ዙር የ1997 ዓ.ም. የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎችና እስከ 11ኛው ዙር ዕጣ ያልወጣላቸው ተመዝጋቢዎች፣ አሁን በግንባታ ላይ ካሉት ቤቶች ሁሉም እንደሚደርሳቸው ተገለጸ፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ እንደገለጸው፣ እስከ 11ኛው ዙር የኮንዲሚኒየም ቤቶች ዕጣ የወጣላቸው የከተማው ነዋሪዎች 176 ሺሕ ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ዙር የተመዘገቡ ነዋሪዎች ከ900 ሺሕ በላይ ነበሩ፡፡ በ2005 ዓ.ም. በዳግም ምዝገባ አብዛኞቹ ነባር ተመዝጋቢዎች የቤት ምዝገባቸውን ደረጃ በማሻሻል በአዲሱ የአመዘጋገብ ሥርዓት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ቀድሞ የተመዘገቡበትን በማደስ እስከ 11ኛው ዙር ድረስ ዕጣ የወጣላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ አሁን በመገንባት ላይ ካሉ ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንደሚደርሳቸው፣ የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ታምራት ተናግረዋል፡፡

  አቶ ሽመልስ፣ ምክትል ሥራ አስኪያጇ ወይዘሮ አፀደ ዓባይ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ የአንድ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መንበረ አስመረና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ብርሃኔ ገብረፃዲቅ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በ11ኛው ዙር ዕጣ ከወጣባቸው 30,634 ቤቶች ውስጥ 19,047 ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች ብቻ ቀርበው ተዋውለዋል፡፡ 16,0203 ሰዎች ቁልፍ ተረክበዋል፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች የመዋዋያ ቅጽ የወሰዱ ቢሆንም፣ 1,953 ሰዎች ግን አለመቅረባቸውንም ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም እስከ ኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ቀርበው ካልተዋዋሉ የማይስተናገዱና ቀሪዎቹ ቤቶች በድጋሚ ዕጣ እንደሚወጣባቸውም አሳውቀዋል፡፡ ነገር ግን በፍርድ ቤት ክርክር ላይ የነበሩ፣ በግዳጅ ላይ የነበሩ የመከላከያና የፀጥታ አባላት ግን በቀረቡ ጊዜ የሚስተናገዱ መሆናቸውን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡

  ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች ስማቸውን በጋዜጣ ላይ በማየት ሊዋዋሉ ሲሄዱ ‹‹የእናንተ አይደለም›› እየተባሉ ስለሚመለሱ፣ በአንድ መስኮት መስተንግዶ ሁሉንም የቤት ውል የሚፈጽሙ የአስተዳደሩ ሠራተኞች ስለሚያደርሱት በደል ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ፣ ነዋሪዎቹ በጋዜጣ ላይ የታተመውን ስማቸውን በማየት ወደ እነሱ ቢመጡም በሞክሼነት የቀረቡ እንጂ ትክክለኛና እስከ እናታቸው ስም ድረስ የተረጋገጠ ዕድለኞች እንዳልተመለሱ አስረድተዋል፡፡ በ11ኛው ዙር ዕጣ የወጣባቸው የጋራ ቤቶች መሠረተ ልማቶቻቸው የተሟሉ ቢሆኑም፣ ጥቂት የቀሩት ግን እየተሠሩና በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ቤቶቹ እየተሰነጣጠቁ ስለመሆናቸው፣ የመሠረተ ልማቶች ችግር እንዳለባቸው የሚገለጸው የተጋነነ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በስተቀር ሁሉም ከሞላ ጎደል እየተሳካ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  በ11ኛው ዙር ዕጣ ወጥቶባቸው የተረፉ ከ3,000 በላይ የ10/90 ቤቶች ስላሉ በድጋሚ ለ2005 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች በዕጣ እንደሚተላለፉ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ የ10/90 ፕሮግራም ከዚህ በኋላ እንደሚቆምም አክለዋል፡፡

  በ10ኛው ዙር ዕጣ የወጣባቸው ቤቶች ለዕድለኞች የተላለፉ ቢሆንም፣ መሠረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ግለሰቦቹ መቸገራቸውን በሚመለከት ለቀረበው ጥያቄ፣ ለማስተካከል እየተሠራ መሆኑን አቶ ሽመልስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ወይም ‹‹የደሃ ደሃ›› ለሚባሉት ነዋሪዎች አስተዳደሩ ቤቶችን በመሥራት ለማከራየት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ 5,000 ቤቶችን ለመገንባት የተዘጋጀ መሆኑንና የመጀመሪያዎቹ 2,000 ቤቶች ግንባታ በታኅሳስ ወር 2009 ዓ.ም. እንደሚጀምርም አስረድተዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...