Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናተቃዋሚ ፓርቲዎች ከአዲሱ ካቢኔ ምንም አዲስ ነገር አንጠብቅም አሉ

  ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከአዲሱ ካቢኔ ምንም አዲስ ነገር አንጠብቅም አሉ

  ቀን:

  የተቃዋሚ አመራሮች ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔ፣ የአገሪቱን አጠቃላይ ችግሮች ያልተረዳና በግለሰቦች የትምህርት ዝግጅት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው በማለት አጣጣሉት፡፡

  የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ‹‹በአዲሱ ካቢኔ የተመረጡት ሚኒስትሮች የተማሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙም ድንቅና አዲስ የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት ሚኒስትሮችም የተማሩ እንጂ ዝም ብለው ከመንገድ የተሰባሰቡና መኃይማን አልነበሩም፤›› በማለት ምንም አዲስ ነገር እንዳልተፈጠረ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  በሽግግሩ ወቅት ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው በሠሩበት ወቅት የገጠማቸውን ፈተና የሚገልጹት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹አዲስ የተሾሙት ሚኒስትሮች ፖሊሲው አያሠራቸውም የሚል እምነት አለኝ፤›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡

  ከአዲሱ ካቢኔ ብዙም የተለየ ነገር እንደማይጠብቁ የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ሹመቱ አሁን በአገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮችን ከመፍታት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤›› በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

  በተመሳሳይ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የጥናትና ምርምር ክፍል ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ፣ በአዲሱ ካቢኔ የታየ ምንም አዲስ ነገር የለም በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ሹመቱ በእኛ በኩል ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን አዲስ የተባሉትም ቢሆኑ ለእኛም ሆነ ለኢሕአዴግ አዲስ አይደሉም፡፡ ምናልባት አዲስ ከተባለ ካቢኔውን አዲስ የሚያደርገው ተሿሚዎቹ ከአካዴሚክ አካባቢ መምጣታቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

  አዲሱ ካቢኔ ከመዋቀሩ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በተደጋጋሚ ለለውጥ ተዘጋጅተናል ካቢኔያችንንም በአዲስ መልክ እናዋቅራለን ሲሉ አዲስ ነገር ጠብቀው እንደነበር አቶ ዋስይሁን ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ከዚህ አንፃር በአዲስ መልክ የሚዋቀረው ካቢኔ አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፖለቲካ፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል አዲስ አስተሳሰብ ያመጣል የሚል ከፍተኛ እምነት ነበረን፡፡ ነገር ግን ያንን ልናይ አልቻልንም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

  በቅርቡ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው የተሰየሙት አቶ ሰለሞን ተሰማ በበኩላቸው፣ ‹‹ተሿሚዎቹ የግል ብቃትና አቅም እንዳላቸው አይተናል፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍ ያለ አገልግሎትና የተሻለ የብቃት ደረጃ በተለያየ ተቋማት ውስጥ እንዳላቸው ተረድተናል፡፡ ነገር ግን ይህንን አቅምና ችሎታ አውጥተው ሊሠሩ የሚችሉባቸው ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ አደረጃጀቶች ከፍተኛ ማነቆዎች የበዛባቸው ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹መሥሪያ ቤቶቹ የሚመሩበት ፖሊሲና መመርያዎች አብዛኛዎቹ የሚያንቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዞሮ ዞሮ ተሿሚዎቹ የተሻለ አቅም፣ ዕውቀትና የሥራ ደረጃ ላይ ቢሆኑም የሥርዓቱ በርካታ ችግሮች ግን ገና አልተፈቱም፤›› በማለት የጥርጣሬያቸውን ምንጭ አስረድተዋል፡፡

  ‹‹በአዲሱ ካቢኔ ከፍ ያለ ብሔራዊ ስሜት አሁን እየመጣ እንደሆነ ተረድተናል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መሠረት በሞኖፖል የተያዙ ፖሊሲዎች፣ አዋጆችና የሕገ መንግሥቱ ዓብይ ጉዳይ ተሻሽለው የኢሕአዴግ ሞኖፖሊ በትክክለኛ መድበለ ፓርቲ እንዲተካ አስተዋጽኦ እናበረክታለን፤›› ሲሉ አጠቃለዋል፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...