Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበርካታ ቦታዎች አጥሮ ዓመታት የዘለቀው ሚድሮክ አሁንም በሌላ ማስጠንቀቂያ ታለፈ

  በርካታ ቦታዎች አጥሮ ዓመታት የዘለቀው ሚድሮክ አሁንም በሌላ ማስጠንቀቂያ ታለፈ

  ቀን:

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ያህል ሚድሮክ ኢትዮጵያ አጥሮ ባስቀመጣቸው ቦታዎች ላይ አሁንም በድጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡

  ሚድሮክ በሥሩ በሚገኙ ኩባንያዎች ስም በአዲስ አበባ ከተማ 17 ቦታዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ እነዚህ ቦታዎች አብዛኛዎቹ ታጥረው ያለ ሥራ መቀመጣቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ የፈጠረ ሲሆን፣ ከዚህ በመነሳትም የከተማው አስተዳደር ለሚድሮክ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች በመስጠት ግንባታውን ለማስጀመር ሙከራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ሚድሮክ የሚታይ ግንባታ ማካሄድ ባለመቻሉ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሚያገኙት መድረክ በግልጽ ቅሬታቸውን ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

  ከዚህ በመነሳት ባላፈው ሳምንት ቅዳሜ ጥቅምት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የመሬት ልማትና ማኔጀመንት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታው፣ የሚድሮክ ተወካይ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ሚድሮክ ከያዛቸው 17 ቦታዎች ውስጥ ስምንቱን በመጎብኘት ውይይት አድርገዋል፡፡

  በወቅቱ አቶ አባተ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ታጥረው ወደ ግንባታ ሳይገቡ የቆዩ ቦታዎች በፍጥነት ወደ ሥራ የማይገቡ ከሆነ፣ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጽ ጉዳዩን አልፈውታል፡፡

  ከተጎበኙት ቦታዎች መካከል መሀል ፒያሳ ታጥሮ ለዓመታት የተቀመጠው ቦታ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሚድሮክ 52 ፎቅ ከፍታ ያለው የገበያ ማዕከል ሕንፃ ለመገንባት ቦታውን የተረከበው ከ1990 ዓ.ም. በፊት ነው፡፡ የሚድሮክ ልሳን በሆነው ጥረት መጽሔት 1992 ዓ.ም. ዕትም ላይ እንደገለጸው ከነሐሴ 1990 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 1991 ዓ.ም. ድረስ በቦታው ላይ ለሚካሄደው ግንባታ የአፈር ምርመራ ተካሂዷል፡፡ ቦታውን የማጠር ሥራም በወቅቱ መካሄዱን መጽሔቱ ጨምሮ ይገልጻል፡፡

  ነገር ግን እስካሁን በቦታው ላይ ግንባታ አልታየም፡፡ ሌላው የሚድሮክ አራት ቦታዎች የሚገኙት በአፍሪካ ጎዳና (ቦሌ መንገድ) ወደ ወሎ ሠፈር በሚወስደው መተላለፊያ ድልድይ አካባቢ ወሰን ሕንፃ አጠገብ ያለው ላይ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ አራት ቦታዎች ሲኖሩ፣ በሁለቱ ቦታዎች ላይ ሕንፃ ተገንብቷል፡፡ በሁለቱ ቦታዎች ላይ ግን ግንባታ አልተካሄደም፡፡ እነዚህ ቦታዎች ለሚድሮክ ከተሰጡ ከ15 ዓመታት በላይ ይሆናል፡፡ ሕንፃዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ ቢጀምሩም፣  ለዓመታት ያለ ሥራ ተዘግተው ተቀምጠዋል፡፡ አቶ አባተ በእነዚህ ቦታዎች ግንባታው በፍጥነት እንዲጀመር አስጠንቅቀዋል፡፡

  ሌሎቹ ቦታዎች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኙ ሁለት ቦታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቦታዎች በኢምፓየር ሪል ስቴት ስም የሚገኙ የሚድሮክ ቦታዎች ሲሆኑ፣ ከመሠረት ግንባታ የዘለለ የሚታይ ግንባታ አይገኝባቸውም፡፡ በዶ/ር አርከበ ዕቀባይ የሥልጣን ዘመን በካዛንቺስ የተጀመረው የመልሶ ማልማት ቀጣና በሆነው በዚህ አካባቢ የበርካታ ባለሀብቶች ግንባታዎች ተጠናቀው ወደ ሥራ ከገቡ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ የሚድሮክ ቦታዎች ግን ታጥረው ተቀምጠዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ለሸራተን ማስፋፊያ የተወሰደው ቦታም የቂርቆስና የአራዳ ክፍላተ ከተሞች ሁለት ቀበሌዎች ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች ተነስተው ሚድሮክ ቦታውን ቢረከብም ቦታው ታጥሮ ይገኛል፡፡ ሌላው ቦታ በልደታ ክፍለ ከተማ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው ነው፡ ይኼ ቦታ እንደ ሌሎቹ ቦታዎች ግንባታ ሳይካሄድበት በመቆየቱ ካርታው እንዲመክንና ለሌላ አልሚ እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር፡፡  ነገር ግን ሚድሮክ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባቀረበው አቤቱታ የመከነው ካርታ ቢመለስለትም፣ በቦታው ላይ ምንም ግንባታ አለመካሄዱ ታይቷል፡፡

  አቶ አባተ እንደተናገሩት፣ ለግንባታው መዘግየት ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው በራሱ በሚድሮክ ያሉ የውስጥ ችግሮች ናቸው፡፡ በሁለተኛው ደረጃ በከተማ አስተደደሩ መፈታት ያለባቸው መለስተኛ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ‹‹ያም ሆነ ይህ ግን ፕሮጀክቶቹ ተጓተዋል፡፡ ስምንት ቦታዎችን አይተናል፡፡ አራቱ ከሞላ ጎደል ሥራ ተጀምሮባቸዋል፤›› በማለት አቶ አባተ ተናግረዋል፡፡

  የሚድሮክ ተወካይ አቶ አብነት ለግንባታዎቹ መዘግየት የተለያዩ ምክንቶችን አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የውስጥ ችግር አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ በጊዜው መፍትሔ ባለመስጠትና በግንባታ ዲዛይኖች ለውጥ ምክንያት መዘግየት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ አሁን ግን ወደ ሥራ ለመግባት ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

  በነዚህ ቦታዎች ግንባታ ለመጀመር 23 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን የገለጹት አቶ አብነት፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች በእርግጥ ይገነባሉ ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹መማማል ትርጉም የለውም፡፡ መተማመኛው ሠርቶ ማሳየት ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...