Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 21.7 ሚሊዮን ብር በማጉደል የተጠረጠሩ ሥራ አስኪያጆችና ኦፊሰሮች ተከሰሱ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሳቸው ለማግኘትና ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ፣ ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ደንበኞችና ከሌሎች የተለያዩ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ከ21.7 ሚሊዮን ብር በላይ አጉድለዋል የተባሉ ሥራ አስኪያጆችና የደንበኞች አገልግሎት ኦፊሰሮች፣ በከባድ የሙስናና የእምነት ማጉደል ወንጀሎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

  ተከሳሾቹ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አበራ አስፋውና አቶ ብሩክ ከተማ፣ የደንበኞች አገልግሎት ኦፊሰሮች አቶ ፍሰሐ ገብረየስ፣ ሔኖክ ታሪኩ፣ ምናለ ትዕግሥቱ፣ ዘሪሁን በርሄ፣ ቅድስት ጥላሁን፣ ወይዘሮ እርጋት ገብረሥላሴ፣ ሔኖክ ተክሌ፣ ወንድወሰን ታምሩና እንዳለ ወንድማሰጥ መሆናቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

  ሥራ አስኪያጁና ምክትል ሥራ አስኪያጁ በቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ውስጥ የሚሠራውን ሥራ በሕግ፣ በደንብና በመመርያው መሠረት መሠራቱን የመቆጣጠርና የመከታተል፣ እንዲሁም ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ ከ1,000 ብር በላይ በባንኩ ላይ ጉዳት ሲደርስ ለባንኩ የበላይ አካል የማሳወቅ ኃላፊነትና ግዴታም እንደተጣለባቸውም ያክላል፡፡

  ነገር ግን ሥራ አስኪያጆቹ በተሰጣቸው ኃላፊነትና በተጣለባቸው ግዴታ መሠረት ግዴታቸውን ካለመወጣታቸውም በተጨማሪ፣ በባንኩ ውስጥ መደበኛ ገንዘብ ያዥ እንዳይኖር በማድረግና ጉድለት ሲፈጠር እንዳይታወቅ ለማድረግ፣ የባንኩን ሠራተኞችና ኦፊሰሮች በተለያዩ ቅርንጫፎች አፈራርቆ በማሠራት በባንኩ ላይ የ21,763,930 ብር ጉድለት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

  በቅርንጫፍ ባንኩ ውስጥ የሚደረገውን ማንኛውንም ግብይትና የገንዘብ መቆጣጠር ኃላፊነት ወደ ጎን በማለት፣ በባንኩ ካዝና ውስጥ መኖር ያለበት ገንዘብ ሳይኖር እንዳለ በማስመሰልና በኮምፒዩተር ሲስተም ውስጥ ካለው ገንዘብ ጋር እኩል  ገንዘብ ያለ በማስመሰል፣ እንደ ባንኩ ገንዘብ ተቆጣጣሪ ከጥቅምት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ሲፈርሙ መክረማቸውን ክሱ ጠቁሟል፡፡

  ሌሎቹም ተከሳሾች የቅርንጫፉ ዋና ገንዘብ ያዥና የገንዘብ ተቆጣጠሪ ኦፊሰሮች ሆነው ሲሠሩ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጽሙ መክረማቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

  ሥራ አስኪያጆቹ ሔኖክ ተክሌና ወንድወሰን ታምሩ ባንኩ የጣለባቸውን አደራ ወደ ጎን በማለት ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለማግኘትና ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ ከባንኩ ደንበኞችና ከተለያዩ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር፣ ምንም የሚላክ ገንዘብ ሳያቀርቡ ወይም ከአካውንታቸው እንዲንቀሳቀስ ሳያደርጉ በድምሩ 3,100,880 ብር ያላግባብ በአገር ውስጥ ሐዋላ መላካቸውንና ባንኩ ከዝውውሩ ማግኘት የነበረበትን 3,088 ብር ማሳጣታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

  በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ በከባድ የእምነት ማጉደልና የሙስና ወንጀሎች፣ ሕዝባዊ ድርጅትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት ሙስና ወንጀል ክስ በዓቃቤ ሕግ ቀርቦባቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለኅዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች