Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ውጥንቅጥ!

  እነሆ መንገድ፡፡ ከፒያሳ ወደ ጳውሎስ መድኃኔዓለም እያቀናን ነው። ‹‹ውኃ ወላዋይ . . .›› ይላል አንዱ መጨረሻ ወንበር ጥጉን ይዞ በፉጨት፡፡ ‹‹ኧረ ወንድሜ ትንሽ ቀነስ አድርገው፤›› ይለዋል ከጎኑ። ‹‹ኑሮ ሲንር ዝም እያላችሁ ፉጨት ታስቀንሳላችሁ?›› ይለዋል። ‹‹አይ እንግዲህ?›› ይቆጣል ያኛው፡፡ ‹‹አይ ሸገር ያልተወለደ። ሁሉ ነገር በተኮሳተረ ይመስለዋል። እኛ ተኮሳትረን ምን አመጣን? ዘጠና ሰባት ይጠየቅ እስኪ? ይልቅ አንተም አፏጭ ይቀልሃል፤›› ይለዋል ነገረኛው ፉጨተኛ አፉን አሹሎ። እንዲህ ሲባባሉ ወያላው ጫማ እያስጠረገ፣ ‹‹ግቡ! ግቡ!›› ይላል። ‹‹ወይ ጊዜ?›› ትላለች ከሾፌሩ ጀርባ የተየመች ወይዘሮ። ‹‹ተይው እሱም ቀን ወጥቶለት ‘ቪትዝ’ ገዝቶ እስኪያከራይ በጫማው ይደበር፤›› ይላታል ሳቂታ ዓይኖቹን እያንከባለለ ሾፌራችን። “ድሮስ?” ብላው አፏን ሰበሰበች። ይኼኔ ከጎኗ የተየመ ጎልማሳ፣ ‹‹አስታወሳችሁኝ፤›› ብሎ ወርዶ ጫማውን ማስወልወል ጀመረ።

  ‹‹ኧረ እንቸኩላለን ንዳው፣ እየሄድክ ትጭናለህ፤›› ትላለች ዶሴ የታቀፈች ቀጭን ጠይም ልጅ። ‹‹እሱ ድሮ ቀረ እህት። ሒሳብ ሳያወራርዱ በባዶ መሮጥ ድሮ ቀረ።  ዘንድሮ ልማታዊ ካልሆንሽ ማን ይዘክርሻል?›› ሾፌሩ ያላግጥብናል። ‹‹ኧረ እባክህ ዕድሜ ነው የምታባክነው፣ ተው . . . ተው . . .›› ይላሉ ከጎኑ ተደግፈው ገብተው የተሰየሙ አዛውንት። ‹‹አይ አባቴ? አሁን እኛ በረባ ባረባው የሚባክነውን ሀብታችንን ሳንቆጥርና ሳንቆጥብ ዕድሜ ብንቆጥብ ያምርብናል?›› ሲላቸው ፈገግ አሉ። ‹‹የዛሬ ልጆች ምላሳችሁ አይቻልም፤›› ሲሉ ያ የሚያፏጨው ልጅ ሰምቶ፣ ‹‹ምላስ ምን ጠቀመን ብለው ነው? አሾልነው፣ አሾልነው። ስናወጣባቸው እነሱ መልሰው ያወጡብናል። ስናስረዝመው ደግሞ ‘አርዝመው ቢያስሯት የፈቷት መሰላት’ እያሉ መግለጫ ይሰጡብናል። ሕይወታችን ሁሉ ግልባጭ ደብዳቤ ብቻ ሆነ። በፕሮፓጋንዳ ያበደ፤›› ብሎ ከለፈለፈ በኋላ ጨዋታው ጋብ አለ። ጫማ የሚያስጠርገውም አስጠርጎ ገባ። አፉን የሚያሿለውም አሹሎ የበቃው መሰለ። መንገድ ብቻ አላጥር እንዳለ አለ።

  ጉዞ እየቆየ ነውና የሚያስተያየው አንድ እርጉዝ ተሳፋሪ በረጅሙ ስትተነፍስ ሰማንና አስተዋልናት። ብዙም ሳትቆይ፣ ‹‹እኔስ ምን አማረኝ መሰላችሁ?›› ብላ ዓይናችን አስፈጠጠችው። በዚህ የኑሮ ውድነት እርጉዝ እናቶች እንዳማራቸው ሳይበሉ እንደሚወልዱ ድንገት ብናስብ ዘመኑን ክፉኛ ረገምነው። ‹‹ምን ይሆን የእኔ ልጅ?›› አሏት አዛውንቱ በትዝታ ወደ ኋላ እያጠነጠኑ ያሉ መስለው። ‹‹ዶላር!›› ብላ ቀጣዩን ቃል ሳትናገር፣ ‹‹ጉድ ሆንን ሾፌር! የዘንድሮ ፅንስ ደግሞ ምነው ምግብና መጠጡን ትቶ የገንዘብ ኖት ያምረው ጀመር? ምን አለ በሉ ይኼ ልጅ ወደፊት ኢንቨስተር ይሆናል፤›› ሲሉ ሳቅ በሳቅ ሆንን። ‹‹አሁን ይኼ ያስቃል? አገር በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደ ቆዳ ተወጥራ እያያችሁ በመጪው ትውልድ ራዕይ ትስቃላችሁ?›› ብለው እንደ መቆጣት አሉ።

  ‹‹ኧረ አይደለም። የእኛም ህልም እኮ አገራችን ኮምፒዩተር የሚመረትባት፣ ስልክ፣ መኪና፣ እንዲሁም ባቡር የሚመረትባት ሆና ማየት ነው። ግን ካለ ዶላር በቃ አይሆንልንም ማለት ነው?›› ስትል ባለ ዶሴዋ ውጥረቱ ጋብ አለ። ኋላ ደግሞ ያ ፉጨታሙ ልጅ፣ ‹‹ምናለበት የእኔዋም እንዳንቺ ቢያምራትና ዘርዝሬ ዘርዝሬ በረጨሁት። ግን እኔ የምለው ዶላር ላይ ድግምት አለ የሚባለው እውነት ነው? ‹ኢን ጎድ ዊ ትረስት› ምናምን ድግምት ነው ይባላል። በበኩሌ ‹ኮንስፓይሬሲ ቲዮሪ› ብዬዋለሁ . . .›› ብሎ ቀባጠረ። ዘንድሮ እኮ ጤነኛና ታማሚውን መለየት ከበደን እናንተ። ‹‹ውይ ሴቶች? ቆይ ግን እንዲህ ሁሉም ‘ብራንድ’ እየለበሱ፣ በዝነኛ ሽቶ እየታጠቡ፣ ሽቅርቅር ብለው በከተማው የምናያቸው የኑሮ ውድነቱን በምን ቢቆጣጠረሩት ነው? በዶላር እንዳትሉኝ ብቻ?›› ብሎ ከኋላችን ካሉት ወጣት ተሳፋሪዎች አንዱ ሌላውን ቢጠይቀው እንዳልሰማ ሆኖ ሌላ ወግ አስጀመረው። ‘ሰምተሃል!’ የሚሉዋት አማርኛ ደግሞ ፋሽን ሆናለች ዘንድሮ!   

  - Advertisement -

  ጥቂት እንደ ተጓዝን ወያላው ሒሳብ አምጡ እያለ ማፋጠጥ ጀመረ። ‹‹ምንድነው ነገሩ?  በርጫ  ጠፋና ተሳፋሪም ‘ይጠፋል’ ብለህ ሰግተህ ነው? አገራችን ቃሚና አቃቃሚ ብታበዛም ይኼን ያህል ሁላችንም በሀራራ አልተወገርንም። ተረጋጋ ‘ፍሬንድ!” አለው አንዱ። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ደግሞ፣ ‹‹ገና ሳይነጋ መስኮት ይከፍታል እንዴ? ‘ዝጋው! አልዘጋውም!’›› እየተባባሉ አንዱ ላይ ይወርዱበታል። ‹‹ውይ! ኧረ የመስኮት አምላክ ይኼን የዘመናት ንትርክ እባክህ ቋጨው? ዛሬም በመስኮት መዝጋትና መክፈት አልተስማማንም? እንኳን ይኼን ይኼን የአሰብን ነገር እርግፍ አድርገን ረስተን የለም ወይ?›› ትላለች አጠገቤ የተቀመጠች ዘመናይ። ‹‹አንቺ የመስኮቱ ይገርምሻል እንዴ? መቼ በምርጫና በምርጫ ቦርድ፣ በትምህርትና ማስተማር ሒደቱ በሚሠራው መሠረታዊ የለውጥ ሥራ፣ በሚታይ በሚጨበጠው ነገርስ ተስማማን? መስማማት ሞታችን ሆኗል እኮ?›› አላት ከአዛውንቱ አጠገብ የተቀመጠው ወጣት አንገቱን እስኪያመው ተጠምዝዞ።

  ‹‹ወደን መስሎህ ነው ልጄ? ባይልልን እኮ ነው! እሱ ባይልልን ነው!›› ቢሉ አዛውንቱ ጣልቃ ገብተው ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ጎልማሶች እየተቀባበሉ፣ ‹‹‘አንድ ለአንድ መታገል ሲያቅተው ሰው ሁሉ፣ አንተ ሰው በሰው ላይ ትጥላለህ አሉ፤›› ብለው ይገጥሙ ጀመር። ‹‹እዚሁ እርስ በርሳችን መጠቋቆም ሳያንሰን ደገሞ ፈጣሪም መጨመሩ እኮ ነው የሚደንቀኝ?›› ሲል አንደኛው የወዲኛው መልሶ፣ ‹‹ሁሉም ነገር እኛ ላይ ጀምሮ እኛ ላይ የሚጨረስ የሚመስለን ስለምንበዛ ምናልባት ፈጣሪም ኢትዮጵያዊ እየመሰለን ይሆናላ፤›› አለው። ይኼን ጊዜ ደግሞ መጨረሻ ወንበር ላይ የተሰየሙት ተሳፋሪዎች በአንዴው ፍቅር ሆነው ተገኝተው፣ ‹‹ታዲያስ! ሰው የምድሩን ትቶ ስለሰማዩ በማያውቀው እየገባ በሚፈላሰፍበት ዘመን እኛ ስለሲቲና ዩናይትድ ስንቀድ ብንውል ለምን እንወቀሳለን?›› ማለት ያዙ። ዙሩ ከመክረሩ በፊት ግን ታንቡር የሚቀድ የስልክ ጩኸት ነገሩን አበረደው። የአንዳንዱ ጩኸት ለአንዳንዱ መብረጃ ባይሆን ኖሮ ሰውም አንሆን ነበር እኮ እስካሁን!

  ‹‹ምናለበት እንዲህ ራሳችንን ከመቃብር በላይ እንደምናፈቅረው ቢያንስ ‘ይህችን ታህል’ ሌላውን ብናፈቅር?›› ራሰ በራው የአዛውንቱን ጨዋታ ሲያደምጥ ቆይቶ ነው መናገር የጀመረው፡፡ ‹‹በቃ እስከ መቃብር እየተዋደድን ተያይዘን ማለቅ ሆነ የእኛ ታሪክ?›› ማንም አይመልስለትም። ብቻውን ያነበንባል። ‹‹ምንድነው ሰውዬው የሚነጫነጭብን? አግብቶናል እንዴ?›› ትለኛለች ከጎኔ ሹክክ ብላ። ይኼን ስትል የሰማት ያ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ጠይም ጎረምሳ፣ ‹‹ምናልባት ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ‘ፌስቡክ’ ሲጠቀም ቆይቶ ይሆናል የተሳፈረው፤›› አላትና ሳቀ።

  ‹‹ታዲያ እኛ የእንካ ሰላንትያ ሰሌዳ ነን እንዴ? አንዳች ደህና ነገር አይታየውም? ደግሞስ ፌስቡክ እስካሁን አልተዘጋም እንዴ?›› ብላ አፏን እንደ ከፈተች አዛውንቱ፣ ‹‹ልይስ ቢል ማን ያሳየዋል ልጄ? ቪፒኤን እንዳትይን። ጠማማ ነው ብለሽ የተውሽውን እንጨት ‘የቀና ነው’ ብለው ወስደው ማገር አድርገውት ያሳዩሻል። ‘የቀና ነው’ ያልሽውን ደግሞ ጎባጣ ነው ብለው ይተቹብሻል። ከጠማማው ጋር ስትጣመሚ ከቀናው ጋር ስትቀኚ እንዲችው አንቺ ራስሽን ሳትሆኝ ታልፊያለሽ። እህ ታዲያ? ስታስቢው ገና መንገድሽን ሳታጋምሺው አጨራረሱን እያሰብሽ አጀማመርሽን ታበላሺውና ታርፊያለሽ፤›› ሲሉዋት ክው አልን። ገና በጅማሬ እንዲህ ከባሰብን መጨረሻችን እንዴ ይሆን ይሆን ጎበዝ?!

   ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹የዓለም ዋንጫ አልናፈቃችሁም?›› ይላል መጨረሻ ከተቀመጡት ወጣቶች አንደኛው። ‹‹እኔን የናፈቀኝ ሩሲያን ማየት ነው። የአሜሪካ ነገር የሚያወጣ አይመስልም። ቃኘት ቃኘት አድርገን በስክሪን ያልተበላበት ቢዝነስ ሩሲያ መፈለግ ሳያዋጣ አይቀርም፤›› ይለዋል ከአጠገቡ። ጎልማሳው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹እንዳያያዛቸውስ መቼም ዘንድሮ ጉድ የሆነ የዓለም ዋንጫ እናያለን። ብቻ ያን በረዶ አደራ ማለት ነው። አስቡት እስኪ ኳሱ ወደ ጎል ሲለጋ ድንገት መሀል ላይ በረዶ ሠርቶ ደርቆ ቢቀር? ያኔ ነው አብዮቱን ማየት፤›› አለ። ‹‹አብዮትና በረዶን ደግሞ ምን አገናኛቸው?›› ሦስተኛው ረድፍ ላይ ቦርሳዋን ስትከፍትና ስትዘጋ ያየናት ቀዘባ ግራ ተጋብታ ታጉተመትማለች።

  ጎልማሳው ስሜታዊነት ይታይበታል። ‹‹የደላው ሙቅ ያኝካል አሉ። ደልቶሃል ወንድሜ። እኛ እዚህ የአገር ሚዛን መጠበቅ በተሳናቸው አዋቂ ነን ባዮች ፔዳል ዓመታት ተሳቀናል፣ አንተ በሩራሺቺቷቷሩሲያ በረዶ ከቦልሼቪክ አብዮት ጋር ኳስ ትጫወታለህ?›› አለው በድፍረት ፉጨቱን አልተው ያለን ተሳፋሪ። ‹‹ምን ማለት ነው?›› ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹ችግሩ እኮ እሱ ነው ወንድሜ። ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲያ ሆነናል እያለህ ነው፡፡ አገር ውስጥ ያለውን ውጥንቅጥ ሳታስተካክል፣ ዝም ዝሙን ሳትገስፅ ገና ከስንት ወር በኋላ ስለሚካሄድ ዋንጫና ፖለቲካ ታወራብናለህ። የእኛስ ዋንጫ? የእኛስ ብርድ? እኮ መቼ ይወራ?›› ሲለው ታክሲያችን ቀጥ አለና። ‹‹መጨረሻ›› ተባለና ለሌላ ጉዞ ስንበታተን፣ የውጥንቅጣችን ጉዳይ አንገታችንን አስደፍቶን ነበር። መልካም ጉዞ!

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት