Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ማይክሮ ፋይናንሶች ወደ ባንክነት ለማደግ ብሔራዊ ባንክ ልዩ ሕግ ያውጣልን እያሉ ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  አነስተኛ ብድሮችን በማቅረብ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን እንደሚያገለግሉ የሚታሰቡት ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በአሁኑ ወቅት  ቁጥራቸው 33 ደርሷል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝተው እንደማንኛውም የፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር የሚደረግባቸው እነዚህ ተቋማት በተለያየ የአቅም ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆንም፣ ቀደም ብለው የተቋቁሙት ግን አቅማቸው እየጎለበተ እንደመጣ ይነገርላቸዋል፡፡ ከሁለት እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያከማቹ ተቋማት እንዳሉም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ወልደይ አመኻ ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶቹ ማክሮ ፋይናንሶች ያካበቱት የካፒታል መጠን የግል ባንኮች ካላቸው ካፒታል ይበልጣል፡፡

  ከካፒታላቸው ባሻገር ለተበዳሪዎች የሚያቀርቡት የገንዘብ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የሰጡት ብድር ወደ ሃያ ቢሊዮን ብር ተሻግሯል፡፡ የተቋማቱ የተበዳሪዎች ቁጥርም ከ3.8 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ለተደራሽነታቸው መስፋፋት አመላካች ነው ተብሏል፡፡ ተቋማቱ ባለፈው በጀት ዓመት የነበራቸው የሀብት መጠን ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ካፒታላቸው በድምሩ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ታውቋል፡፡

  ይህ እንቅስቃሴ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አቅም እየጎለበተ መምጣቱን የሚያመላክት ስለመሆኑ ዶ/ር ወልዳይ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ለማደጋቸው ዋነኛ ምክንያቱ መንግሥት የሰጣቸው ማበረታቻ  መሆኑንም ዶ/ር ወልዳይ አጣቅሰዋል፡፡

  እነዚህ ተቋማት ዓመታዊ ትርፋቸውን በቀጥታ ለካፒታል ማሳደጊያነት የሚያውሉት በመሆኑ፣ የትርፍ ግብር እንዳይጠየቁ መንግሥት የሰጣቸው ልዩ ዕድል ለግስጋሴያቸው የሚጠቀስ ነው፡፡ ስለዚህ ካፒታላቸው እየጨመረ በመምጣቱም የሚሰጡት ብድር እያደገ ሊመጣ እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

  በዚህ ዕድገታቸውም ምክንያት አንዳንድ ማክሮ ፋይናንሶች ወደ ባንክነት ማደግ አለባቸው ወደሚለው አመለካከት ወስዷል፡፡ በካፒታላቸውና በሀብታቸው መጠን እየጎለበቱ ያሉት የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክነት ማደግ እንዳለባቸው ስለታመነበት፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ለሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ‹‹ወደ ባንክ እንድናድግ ይፈቀድልን፤›› የማለት ጥያቄ እስከማቅረብ አድርሷቸዋል፡፡ እርግጥ ይህ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆየት ያለ መሆኑም የሚታወስ ነው፡፡

  የተቋማቱን ጥያቄዎች ተገቢነት የሚገልጹት ዶ/ር ወልዳይ፣ የብሔራዊ ባንክ ምላሽ ግን ‹‹ባንክ መሆን ከፈለጋችሁ ማንኛውንም የግል ባንክ ለማቋቋም የተደነገገውን 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሟላት አለባችሁ፤›› የሚል ሆኗል፡፡

  ይህንን ካፒታል ሊያሟሉ የሚችሉ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቢኖሩም፣ ‹‹ባንክ ካቋቋማችሁ የምትተዳደሩት ባንክ ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ወይም ባንኮች በሚገዙበት ሕግ መሠረት ነው፤›› የሚለው የብሔራዊ ባንክ አቋም ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ የሚስማማ አልነበረም፡፡ ይህ የገዥው ባንክ አቋም መፈተሽ እንዳለበት የጠቆሙት ዶ/ር ወልደይ፣ ባንኮች በሚተዳደሩበት ሕግ መሠረት ይቋቋሙ ከተባለ ማክሮ ፋይናንሶች መንግሥት የሰጣቸውን ልዩ ዕድል ሊያሳጣቸው ስለሚችል በሕጉ መሠረት ወደ ባንክ ሥራ ለመግባት ይቸግራቸዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ካለው የባንኮች ማቋቋሚያ ሕግ ውጭ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚገዙበት ሌላ ሕግ ሊወጣላቸው እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ የምንፈልገውም ይህንን ነው ይላሉ፡፡

  ከመደበኛ ባንክ ውጭ ለሚቋቋሙ ባንኮች የሚሆን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና በዚያ ሕግ እንዲሠሩ ማድረግ በሌሎች አገሮች የተለመደ አሠራር ነው የሚሉት ዶ/ር ወልደይ፣ ተቋማቱ ለድህነት ቅነሳ ጭምር ጉልህ ሚና አላቸው ተብሎ እንደመቋቋማቸው በዚያው ልክ ወደ ባንክነት ሲያድጉም ለእነሱ ተብሎ የሚወጣ ሕግና ደንብ ያስፈልጋል በማለት አብራርተዋል፡፡

  ከመደበኛ ባንኮች በተለየ የሚገዙበትን ሕግ በማውጣት የእንዲህ ያሉት ተቋማት አገልግሎቶችን ለማስፋት በሌሎች አገሮች ኮሙዩኒቲ ባንክ፣ ማክሮ ፋይናንስ ባንክና የኅብረት ሥራ ባንክ እየተባሉ እንዲመሠረቱ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዓላማቸውን ያገናዘበ ሕግ ተቀርጾ ሥራ ላይ ያዋሉ አገሮች በመኖራቸው፣ እዚህ አገርም ይህ ሊደረግ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

  ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ ለተቋማቱ መንግሥት የሰጠውን ልዩ ዕድል አስተካክሎና አጣጥሞ ወደፊት የሚሄዱበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚኖርበት ዶ/ር ወልደይ ጠይቀዋል፡፡

  የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ ከገቡና እንደማኛውም ባንክ አገልግሎት ይስጡ ከተባለ፣ ለአገልግሎታቸውም ከመደበኛ ባንኮች የተለየ መብትና ተጠቃሚነት የሚያገኙ ከሆነ፣ በአንድ አገልግሎት የተለያየ ሕግ ማውጣት አይሆንም ወይ? ውድድሩንስ ሊያዛባ አይችልም ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

  ይህንኑ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ዶ/ር ወልዳይ፣ ይህ ሊከሰት እንደማይችል ሥጋቱም ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ ይሞግታሉ፡፡ ለማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ባንክ ቢሆኑ ተደራሽ የሚያደርጓቸው ያልነተሱ አካባቢዎች በማለት ጠቅሰዋል፡፡ በቅርቡ መንግሥት ለወጣቶች መመደቡን ያስታወቀው አሥር ቢሊዮን ብር አስታውሰዋል፡፡ ለወጣቶች ልዩ ልዩ ሥራዎችን ለመፍጠር የሚረዱ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ፋይናንስ ይቅረብ ከተባለ፣ ፋይናንሱ እንደ ማክሮ ፋይናንስ ባሉ ተቋማት በኩል የሚቀርብ ስለሆነ ይህንን ፋይናንስ ለማቅረብና ጥቅም ላይ ለማዋል የተለየ ሕግ ያስፈልጋቸዋል በማለት ዶ/ር ወልደይ ሐሳባቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

  እንዲህ ያሉ ልማት ተኮር ሥራዎችን የሚሠሩ ተቋማት ወደ ባንክነት መምጣታቸው ከመደበኞቹ ባንኮች ጋር ያልተገባ ውድድር አይፈጥርም፡፡ ተፅዕኖም አያሳድርም፡፡

  ‹‹መፈራት ካለበት ምናልባት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ከተፈቀደና ከእነሱ ጋር መወዳደር ካስፈለገ ነው፡፡ አሁን ባለው ደረጃ በልዩ ጥቅም የማክሮ ፋይናንስ ባንኮች ቢመጡ ውድድሩ ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም፡፡ ውድድሩም ካለ ጥሩ ነው፤›› ያሉት ዶ/ር ወልዳይ፣ ሌላኛው መከላከያ ሐሳባቸው የግል ባንኮች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በተለይ በተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ላይ እየተወዳደሩ ነው፡፡ አነስተኞቹ የፋይናንስ ተቋማት በዚህ መስክ ከባንኮች ጋር እየተፎካከሩ ነው ያሉት ዶ/ር ወልዳይ፣ ይህ ውድድር ጤናማ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ እንዲህ ካለው ውድድር ነው የተሻለ አገልግሎት የሚፈልቀው በማለት በአንድ አካባቢ የተለያዩ ፋይናንስ ተቋማት ውድድር ሲያደርጉ ኢንዱስትሪው ላይ የጎንዮሽ ተፅዕኖ እንደማያሳድር በመከራከር ሐሳባቸውን አሳርገዋል፡፡

  ብሔራዊ ባንክ ግን ቢያንስ ለጊዜው በአቋሙ ፀንቷል፡፡ የተለየ ሕግ እንዲያወጣላቸው የሚጠይቁ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በአቋማቸው እስከ ምን ደረጃ ገፍተው የገዥውን ባንክ ሐሳብ ያስቀይራሉ? የሚለው ወደፊት በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡ ለዓመታት እየተነሳ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች