Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሌላ ሚኒስትር መጡ

  • ዛሬ ከየት ተገኘህ ወዳጄ?
  • እርስዎን ማግኘት እኮ በጣም አስቸጋሪ ሆነ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ፈልገኸኝ ነበር?
  • እንዴት ነው ግን በሥራ ሰዓት የማይገኙት?
  • መቼ ሥራ ፈታሁ ብለህ ነው?
  • በተከታታይ ቀናት ቢሮ መጥቼ ላገኝዎት አልቻልኩም፡፡
  • አገሪቷ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለች ዘነጋኸው?
  • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • አገሪቷ ከባድ ቀውስ ውስጥ ናት እኮ፡፡
  • ታዲያ ይኸው እኛ አመራር እየሰጠን አይደል እንዴ?
  • እ…
  • እርስዎ እኮ ቢሮም የሉም፣ ከእኛም ጋር የሉም፡፡
  • ስማ አገሪቷ ቀውስ ውስጥ ስለገባች እኮ ነው የጠፋሁት፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • በዚህ ጊዜ ነገ የሚፈጠረው ስለማይታወቅ ንብረት በጊዜ መሰብሰብ ነው፡፡
  • የመንግሥትን ሥራ እርግፍ አድርገው የራስዎን ቢዝነስ እያሯሯጡ ነው?
  • ታዲያ ምን ማድረግ እችላለሁ?
  • ክቡር ሚኒስትር ግን አላበዙትም?
  • ምን አጠፋሁ?
  • በዚህ ሕዝብ ላይ ግን እየቀለዱ መሆኑን ያውቃሉ?
  • ይህ ሕዝብ እኮ ምስኪን ነው፣ ምንም አያውቅም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር የሚነዱትን መኪና፣ ያለዎትን ሀብት፣ የሚኖሩበትን ቤት ቢያምኑም ባያምኑም ይህ ሕዝብ ጠንቅቆ ነው የሚያውቀው፡፡
  • እሺ የእኔ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም?
  • እየቀለድኩ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ በዚህ ከቀጠልን እንደ እሱ መሆናችን አይቀርም፡፡
  • የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ሆነሃል ማለት ነው?
  • አሁን ያለውን ሁኔታ መካድ ምንም ስለማያዋጣ፣ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ነው የሚያዋጣን፡፡
  • እኔ ሕዝቡ ጥያቄ አለው ብዬ አላምንም፡፡
  • ማን ነው ጥያቄ ያለው?
  • አመራሩ ነው፡፡
  • አመራሩ የምን ጥያቄ ነው ያለው?
  • እከሌ የሰረቀው እከሌ ከሰረቀው ይበልጣል፣ ስለዚህ እከሌ እከሌን ሊያዘው አይችልም የሚል ነዋ፡፡
  • ምን እያሉ ነው?
  • እርስ በርሳችን ተናንቀናል፣ ማን ምን እንደበላ ይታወቃል፣ ማን ምን እንደሰረቀ ይታወቃል፡፡
  • እ…
  • አሁን ጤነኛ የሆነ ደፍሮ እጁን ያውጣ ቢባል ማን ያወጣል?
  • እሱማ ማንም አያወጣም፡፡
  • አሁን አንተ ለመሆኑ እኔን ስትወነጅል እኔ ነፃ ነኝ ለማለት ፈልገህ ነው?
  • እንደዚያ እያልኩ ሳይሆን ይህ የሕዝብ ጎርፍ ጠራርጎ እንዳይዋስደን ያስፈራል፡፡
  • ለነገሩ ዛሬ እኔ ጋ ለምን እንደመጣህም አውቃለሁ፡፡
  • ለምንድነው የመጣሁት?
  • ሥልጣኔን እንድለቅና መቀጣጫ እንድደረግ ልታደራድረኝ አይደል የመጣኸው?
  • እውነቱን ንገረኝ ካሉ ለዚያ ነው የመጣሁት፡፡
  • ስማ እኔም በቂ ሀብትና ንብረት ስለሰበሰብኩ ሥልጣኔን ብለቅ አይቆጨኝም፡፡
  • ታዲያ ለምን አይለቁም ክቡር ሚኒስትር?
  • መልቀቁን እለቃለሁ፡፡
  • ምን የሚፈልጉት ነገር አለ?
  • በእኔ በኩል ደግሞ እንዲደረግልኝ የምፈልገው ነገር አለ፡፡
  • ምን ክቡር ሚኒስትር?
  • በርካታ ቤቶችና ፋብሪካዎች አሉኝ፡፡
  • እሱማ ባንክ ያለዎትም ገንዘብ ከፍተኛ ነው፡፡
  • ከዚያ ውጪ አሁን የራሴን መርከብ እያስገነባሁ ነው፡፡
  • ለምን?
  • በራስህ መርከብ ዕቃህን ስታስመጣ ትርፉ የትየለሌ ነዋ፡፡
  • ከዚህ በላይ ታዲያ ምን ይፈልጋሉ?
  • ይኼ ሁሉ ሀብት እንዲወረስ የምፈልግ ይመስልሃል?
  • እ…
  • ምን እሱ ብቻ?
  • ሌላ ደግሞ ምን ቀረ?
  • ቂሊንጦ ልገባ እችላለሁ፡፡
  • እሱማ ልክ ነው፡፡
  • ስለዚህ እኔ ሥልጣኔን ስለቅ እንዲሰጠኝ የምፈልገው ነገር አለ፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • ከለላ!

  [ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ደወለ]

  • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አንተ ሰላቢ ምን ፈለግክ?
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን ቀርቶህ ነው የምትደውልልኝ?
  • ሰላም አይደሉም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ስሜን አትጥራ፣ ስምህን ቄስ ይጥራው፡፡
  • ዛሬ በግራ ጎንዎት ነው መሰለኝ የተነሱት?
  • ኧረ ግራ ጎንህን ጦር ይውጋው፡፡
  • እ…
  • አንተን ያወቅኩበት ቀን የተረገመ ነው፡፡
  • ዛሬ የምን ጉድ ነው?
  • ከአንተ በላይ ምን ጉድ አለ?
  • ከሰው ጋር ተጣልተዋል እንዴ?
  • አንተ ከራስ የተጣላህ ጥገኛ፡፡
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ዝም በል መልስ ልትሰጠኝ ነው ደግሞ?
  • ምንድነው የሚያወሩት?
  • እንደ አንተ ዓይነቱ መዥገር ነው ሕዝቡን እየመጠጠ ያለው፡፡
  • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
  • ሕዝቡ በአንተ ዓይነቱ እየተማረረ ነው አገሩን የሚጠላው፡፡
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ለመሆኑ ስንተኛ ክፍል ነው ያቆምከው?
  • ስምንተኛ ክፍል ነው ያቆምኩት፡፡
  • ዋናው ሥራህ ምንድነው?
  • ድለላ፡፡
  • ያለህ ሀብት ስንት ነው?
  • እ…
  • ባለፈው አምስተኛ ፎቅህን እንደጀመርክ ነግረኸኛል፡፡
  • እሱማ ያው በድለላ ነው የሠራሁት፡፡
  • በዚህ አሥር ዓመት ውስጥ አይደል እንዴ ይህን ሁሉ ሀብት ያካበትከው?
  • ያው አገሪቷም እኮ በአሥር ዓመት ውስጥ ነው በሚገባ ያደገችው፡፡
  • እንደ አንተ ዓይነቱ ነው እኛንም የሚያሰድበው፡፡
  • መስመር ያለፉ አልመሰልዎትም ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን?
  • ከእኔ የባሰ አገሪቷን ያቆረቆዟት ጊንጥ አይደሉ እንዴ?
  • ምን አልክ አንተ?
  • አገሪቷን እንደ ሸንኮራ መጠው ካደረቁ በኋላ የተፏት እርስዎ አይደሉ?
  • ሥርዓትህን ያዝ፡፡
  • ሕዝቡን አገልግሉ ተብለው ተሹመው በሕዝቡ ሲገለገሉ የቆዩ ኪራይ ሰብሳቢ አይደሉ?
  • እኔ ጠፋሁ?
  • አንዴ ስኳር፣ አንዴ ማዳበሪያ እያሉ ሕዝቡን ራቁቱን እንዳስቀሩት ረሱት እንዴ?
  • ምን እያልክ ነው?
  • በራስዎት ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳያወጡ፣ በእኔ ዓይን ውስጥ ያለውን ስንጥር ለማውጣት ባይሞክሩ ጥሩ ነው፡፡
  • በጣም ተናንቀናል ማለት ነው?
  • እኔ መቼ ናቅኩዎት?
  • ማን ነው የናቀኝ ታዲያ?
  • ሕዝቡ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸው አስጠሩት]

  • ምነው ተናደዋል ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን የሚያስደስት ነገር አለ ብለህ ነው?
  • ለነገሩ አገሪቷ ከድጡ ወደ ማጡ እየገባች ምን የሚያስደስት ነገር አለ ብለው ነው?
  • ግን እንደዛ የከፋ ነገር ውስጥ ናት አገሪቷ?
  • እንዲያውም የሰው ምሬት ከሚወራውም በላይ ነው፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • የብሔር ፖለቲካው ጦዞ ምን ላይ እንደደረሰ ያውቃሉ?
  • እኛ ምን እናድርግ ታዲያ?
  • ሰዎች የሚጠቀሙት በዜግነት ሳይሆን በደጋፊነት ነው፡፡
  • የምን ደጋፊ ነው?
  • የሥርዓት ደጋፊ ነዋ፡፡፡
  • እንዴት?
  • አንድ ዜጋ ስኬታማ የሚሆነው የሥርዓቱ ደጋፊ ከሆነ ነው፡፡
  • ሰው እንደዛ ነው የሚያስበው?
  • ክቡር ሚኒስትር ለደጋፊ እኮ በሩ ሁሉ ክፍት ነው፡፡
  • እ…
  • ጨረታው ለእሱ ነው፣ ሥራው ለእሱ ነው፣ ቢዝነሱ ለእሱ ነው፣ ብቻ ምን አለፋዎት ሁሉ ነገር ለእሱ ነው፡፡
  • ሥርዓቱን የማይደግፈውስ?
  • እሱማ ይታሰራል፣ ይሰቃያል፣ ይከስራል፣ ብቻ ምን አለፋዎት መከራውን ይበላል፡፡
  • አንተም እንደዚህ ነው የምታስበው?
  • ክቡር ሚኒስትር ይኼ እኮ እውነታ ነው፡፡
  • ምን?
  • ሕዝቡ ወዶ ይመስልዎታል እንደዚህ የተነሳው?
  • ምን እያልክ ነው?
  • የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ ስላልሆነ ነው፡፡
  • አንተም ፍትሐዊ አይደለህም ብለህ ነው የምታስበው?
  • ለእሱማ እኔ ጥሩ ምስክር ነኝ፡፡
  • ማለት?
  • እርስዎ ከአንድ አይሉ አምስት ቤት አለዎት፣ ከአንድ አይሉ አምስት መኪና አለዎት፣ ከአንድ አይሉ አምስት ሕንፃ አለዎት፡፡
  • ከእንደ አንተ ዓይነቱ ምቀኝ ጋር ነበር የምሠራው?
  • እውነቱን አይደል እንዴ የተናገርኩት?
  • አሁን እኔ ሀብታም ብሆን ምን አስቀናህ?
  • ቀንቼ አይደለም፡፡
  • ለማንኛውም አንተ የእኔ አማካሪ መሆንህ ያሳዝናል፡፡
  • እኔም ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን ላስገባልዎት ሳስብ ነበር፡፡
  • ምንድነው የምታስገባልኝ?
  • መልቀቂያዬን!

  [ክቡር ሚኒስትሩ በመሥሪያ ቤታቸው ከሠራተኛው ጋር አጠቃላይ ስብሰባ እያደረጉ ነው፡፡ ሠራተኞቹም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ክቡር ሚኒስትሩ ዕድሉን ሰጧቸው]

  • እዛ ጋ ያለኸው አስተያየትህን ቀጥል፡፡
  • ለምንድነው የሚቀልዱብን ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን እያልክ ነው?
  • ለምን ሥራ ያስፈቱናል?
  • አልገባኝም፡፡
  • ትርጉም ለሌለው ስብሰባ ለምን ጊዜያችንን ያባክናሉ?
  • ለምንድነው ትርጉም የሌለው?
  • የመንግሥትን ዲስኩር ከሚያሰሙን ሕዝቡን ብናገለግል ይሻላል፡፡
  • ሌላ አስተያየት ያለው አለ?

  [ሌላ ሠራተኛ እጁን አወጣ]

  • አስተያየትህን ቀጥል፡፡
  • እኔ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡
  • የምን ጥያቄ?
  • የዛሬው ስብሰባ አበል አለው?
  • የምን አበል ነው?
  • በቃ አበል ከሌለው ጊዜያችንን አያቃጥሉብን፡፡
  • ሌላ አስተያየት ያለው አለ?

  [ሌላኛው ሠራተኛ እጁን አወጣ]

  • አንተ እዛ ጋ ያለኸው፡፡
  • መሥሪያ ቤቱ በወንዝ እንዲደራጅ አድርገውታል፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • ይኸው ሙሉ መሥሪያ ቤቱ በእርስዎ ዘመድ አዝማዶች ነው የተሞላው፡፡
  • ምን?
  • መሥሪያ ቤቱ የቤተሰብ ሆኗል፡፡
  • ሌላ አስተያየት ካለ?

  [ሌላኛው ሠራተኛ እጁን አወጣ]

  • ምንድነው አስተያየትህ?
  • ጓደኛዬ ያለው ላይ ለመጨመር ነው፡፡
  • ምንድነው የምትጨምረው?
  • በሠራተኛው መካከል ያለው የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊ አይደለም፡፡
  • እንዴት?
  • ለምሳሌ እርስዎ ያለዎት ሀብት ከሌላው ሠራተኛ ጋር ሲነፃፀር የሰማይና የምድር ያህል ይለያያል፡፡
  • ምን?
  • አምስት ቤት እንዳለዎት እናውቃለን፣ አምስት መኪና እንዳለዎት እናውቃለን፣ አምስት ሕንፃ እንዳለዎት እናውቃለን፡፡
  • እና ምን ይጠበስ?
  • ይኼ እብሪት አያዋጣዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ታዲያ ምንድነው የምትፈልጉት?
  • እንዲለቁ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምኑን ነው የምለቀው?
  • ሥልጣንዎን፡፡
  • ሥልጣኔን እንኳን አለቅም፣ ባይሆን ሌላ ነገር እለቃለሁ፡፡
  • ሌላ ምን?
  • ነጠላ ዜማ!

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ

  ፊፋ ከምርጫው በፊት የሥነ ምግባር ባለሙያ ሊልክ መሆኑ ተሰምቷል የኢትዮጵያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [ክቡር ሚኒስትሩ በስንዴ የተሸፈኑ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ከስንዴ ምርት ድጋፍና ክትትል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋር እየመከሩ ነው] 

  ክቡር ሚኒስትር እንደነገርክዎት በሁሉም ስንዴ አብቃይ አካባቢዎቻችን ያሉ አርሶ አደሮች ጥሪያችንን ተቀብለው መሬታቸውን በኩታ ገጠም አርሰው በስንዴ ዘር ሸፍነዋል። በጣም ጥሩ ዜና ነው። በጣም እንጂ። የሚገርምዎት...

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሚመሩት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አጀንዳ አድርጎ በያዘው ወቅታዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ቢጀመርም በስተመጨረሻ አጀንዳውን ስቶ ስለ መዋደድ እየተጨቃጨቀ...

  በዛሬው መደበኛው መድረካችን አጀንዳ የተለመደው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ይሆናል። ሌላ አጀንዳ የምታስይዙት አጀንዳ ከሌለ በቀር ማለቴ ነው። ክቡር ሚኒስትር... እሺ ...ቀጥል አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። መደበኛ አጀንዳው እንደተጠበቀ...

  [ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዎና መንገሣቸውን እያነሱ ደስታቸውን ሲገልጹ አገኟቸው]

  እሰይ አገሬ... እሰይ አገሬ እልልል ምን ተገኘ ደግሞ ዛሬ? የአትሌቶቻችንን ድል ነዋ! በክፉ ሲነሳ የቆየውን የአገራቸውን ስም በወርቅ እያደሱ እኮ ነው?  አየሽ፣ መንግሥት የአገራችን ችግር ያልፋል ስሟም...