Friday, August 19, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የዋስትና መብት ተከለከሉ

  የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የዋስትና መብት ተከለከሉ

  ቀን:

       – የአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ባለቤት ዋስትና ተፈቀደላቸው

  ተከላከሉ የተባሉበት የወንጀል ድርጊት ዋስትና እንደማይከለክል፣ ተከላከሉ ስለተባሉበት ክስ እየተከራከራቸው (እየከሰሳቸው) የሚገኘው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሥልጣን እንደሌለው በማስረዳት፣ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ላለፉት 90 ቀናት ሲከራከሩ የከረሙት የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ፣ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ብይን ተሰጠ፡፡

  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቱ በተሰየሙበት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ስማቸው ከበደ የጠየቁት የዋስትና መብት ተቀባይነት እንዳላገኘ ነግሯቸዋል፡፡ የተከሰሱበት የሙስና ወንጀል አንቀጽ ተቀይሮ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸውና ዋስትና እንደማይከለክላቸው በማስረዳት በዋስ እንዲለቀቁ ሲከራከሩ የከረሙት የአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ባለቤት ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬ፣ በ75,000 ብር ዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በሌላ መዝገብ በተከሰሱባቸው የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው በአሥር ዓመታት ጽኑ እሥራት እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የአገር ውስጥ ኃላፊ አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤልም፣ እነ አቶ ስማቸው ከበደ ተከላከሉ በተባሉበት መዝገብ ተከላከሉ በመባላቸው ዋስትና ጠይቀው ነበር፡፡ እሳቸውም የጠየቁት ዋስትና የሚፈቀድላቸው ቢሆንም፣ የተጣለባቸውን የአሥር ዓመታት ቅጣት ባለማጠናቀቃቸው ጥያቄያቸው ታልፏል፡፡

  በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ከተመሠረተባቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ጋር በመዝገብ ቁጥር 141352 የተካተቱት አቶ ስማቸው፣ ከሙስና ክስ ሐምሌ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በነፃ መሰናበታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ አቶ ስማቸው በነፃ የተሰናበቱት የሆቴል መገልገያ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው ቢሆንም ከአቶ መላኩ ፈንታ፣ ከአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስና ከአቶ በላቸው በየነ (ሦስቱም የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ነበሩ) ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ ከተፈቀደላቸው ዓላማ ውጪ ሲያውሉ በወንጀል ሳይጠየቁ ቀርተዋል በማለት በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ነበር፡፡

  እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው ደግሞ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ከ37ኛ እስከ 44ኛ ክሶች (በመዝገቡ በአጠቃላይ 93 ክሶች ናቸው) ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ ባደረጓቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ከሰበሰቡት ገቢ ላይ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ የነበረባቸውን፣ ወይም አሳውቀው መክፈል የነበረባቸውን እንዳልከፈሉ በክሱ ተገልጿል፡፡ ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. የግብር ዓመታት ግብርን አሳውቀው ባለመክፈላቸውና አሳሳች መረጃዎችን በማቅረብ መክፈል ይገባቸው የነበረን የትርፍ ግብር ባለመክፈላቸው፣ በአጠቃላይ መንግሥት ማግኘት ያለበትን ወይም ለመንግሥት መክፈል የነበረባቸውን ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ አለመክፈላቸውን፣ ከሳሽ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በሰው ምስክር ለፍርድ ቤቱ ማስረዳት ችሏል በማለት ነው ብይኑ የተሰጠው፡፡

  ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ብይን ከሰጠ በኋላ አቶ ስማቸው በጠበቆቻቸው አማካይነት ተከላከሉ የተባሉበት የወንጀል ድርጊት የሚመለከተው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ ዋስትና የማያስከለክል መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ በወቅቱ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የዋስትና ጥያቄውን እንደሚቃወም በመግለጹ፣ አቶ ስማቸው ዋስትና መብት ከመሆኑም ባለፈ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው መሆኑን በመግለጽ የዓቃቤ ሕግን መቃወሚያ ተቃውመዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የመጀመሪያ መቃወሚያ ባቀረበበት ወቅት ተቋሙ በሽግግር ላይ እንደነበር አስታውሶ፣ ቀደም ብሎ ያቀረበውን የዋስትና መቃወሚያ የሰበር አስገዳጅ ውሳኔዎችንና ተጨማሪ የሕግ አንቀጾችን በማካተት መቃወሚያውን እንዲያሻሽል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ አቶ ስማቸው ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 66 መሠረት ጥያቄያቸው በ48 ሰዓታት ውስጥ ውሳኔ ማግኘት ሲገባው፣ መጓተቱ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር መርምሮ በሰጠው ብይን የዋስትና መብት ጥያቄው የመነጨው ከክሱ ላይ በመሆኑ፣ የተሻለ ፍትሕ ለመስጠት ይረዳ ዘንድ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን መቃወሚያውን የማሻሻል ጥያቄ መቀበሉን አስታውቆ ነበር፡፡ የአቶ ስማቸው ጠበቆች በ48 ሰዓታት ምላሽ ማግኘት የሚገባው ጥያቄ ለሰባት ጊዜያት ቀጠሮ መሰጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ የተናገሩ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ መቃወሚያውን አሻሽሎ አቅርቧል፡፡

  የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ ያቀረበው የዋስትና መቃወሚያ እንደሚያስረዳው፣ አቶ ስማቸው ዋስትና ቢፈቀድላቸው ያላቸውን ኢኮኖሚ ተጠቅመው ከአገር በመውጣት ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም፡፡ በክስ መዝገቡ ከ37ኛ እስከ 44ኛ ድረስ የቀረቡባቸው ክሶች ተደራራቢ ናቸው፡፡ ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢሆንም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) መሠረት ሊነፈጉ የሚቻልበት ሁኔታም አለ፡፡ ተከላከሉ በተባሉባቸው ተደራራቢ ክሶች ጥፋተኛ ቢባሉ በድምሩ ከ65 ዓመታት በላይ በእስር ሊቀጡ እንደሚችሉና አስገዳጅ ያላቸውን የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች በመጥቀስ መቃወሚያውን አቅርቧል፡፡

  አቶ ስማቸው ባቀረቡት የመቃወሚያ መቃወሚያ እንዳብራሩት፣ ዋስትና ሕገ መንግሥታዊና ሕግ ከሚፈቅደው ውጪ ሊሸራረፍ የማይችል መብት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ተከላከሉ የተባሉባቸው ክሶች ከባድ ወንጀሎች ካለመሆናቸውም በተጨማሪ፣ አንዳንዶቹ አዲስ በወጣው የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ቀሪ የሆኑ ናቸው፡፡ በግብር ሥወራና ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዳለባቸው በኦዲት ተረጋግጧል የተባለው የገንዘብ መጠን፣ ወደፊት የሚከላከሉበትና ድርጅታቸውን በዋስ ያስያዙበት ጉዳይ መሆኑን ከሳሽ ዓቃቤ የሚያውቀው ጥሬ ሀቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  ዓቃቤ ሕግ በዋስ ቢለቀቁ ሊቀርቡ እንደማይችሉ በመግለጽ የተቃወመበትን ምክንያት በሚመለከት በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፣ አንድ ሰው እስካልተፈረደበት ድረስ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት እንዳለው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም ገና ለገና በዋስ ቢለቀቁ ሊጠፉ ይችላሉ በሚል ዋስትና ይከልከሉ ማለት፣ ተከራክረው ነፃ ሊወጡ ይችላሉ የሚለውን ከግምት ውስጥ ያላስገባና የሕግ መሠረት የሌለው ክርክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢኮኖሚ አቅም ስላላቸው የሚለው መከራከሪያ ሐሳብ የዋስትና መብት ማስነፈጊያ ይሆናል ተብሎ በሕግ ያልተደነገገና ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑን፣ አቅም ያለው ሁሉ የዋስትና ግዴታውን ባለማክበር ወደ ውጭ ይወጣል የሚል ግምታዊ መከራከሪያ ተገቢ ያልሆነ ክርክር በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተው ነበር፡፡

  ዓቃቤ ሕግ ዋስትናቸውን ለመከላከል የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67(ሀ)ን በመጥቀስ ያቀረበው መከራከሪያ፣ በጠባቡ መተርጎም እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(3) መደንገጉን፣ ተከሳሹ ንፁህ ሆነው የመቆጠር መብታቸውን ሊያሳጣቸው እንደሚችል፣ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸውና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) ያካተታቸውን የ1948 (እ.ኤ.አ.) ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 11(1)ን፣ እ.ኤ.አ. የ1966 የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ስምምነት (ICCPR) አንቀጽ 14(2) ድንጋጌዎችን የሚፃረር መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ አቶ ስማቸው ሌሎች ሰፋ ያሉና በርካታ የሕግ አንቀጾችን በመጥቀስ መቃወሚያቸውን በማቅረብ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀው ነበር፡፡

  ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር በመመርመር አቶ ስማቸው ‹‹ዋስትና ሊፈቀድላቸው ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ፣ ተገቢ ከሆኑ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር ሲመረምር ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ተቃውሞ ተገቢ ሆኖ በማግኘቱ ዋስትናውን እንዳልተቀበለው አስረድቷል፡፡ አቶ ስማቸው ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ከሰሙ በኋላ ‹‹የተነበበልኝ ውሳኔና እኔ ተከላከል የተባልኩበት ክስ አይገናኝም፡፡ አልገባኝም፤›› በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ በፍርድ ቤቱ የተሰጣቸው መልስ፣ ‹‹ይግባኝ ማለት ይችላሉ፤›› የሚል ነው፡፡ አቶ ስማቸው በመከፋት ስሜት ወደ መሬት ሲያቀረቅሩ ተስተውለዋል፡፡ ዋስትና ይፈቀድላቸዋል የሚል ተስፋ ይዘው ችሎቱን የታደሙት ቤተሰቦቻቸውም በሐዘን ስሜት ከችሎቱ ወጥተዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬን የዋስትና ጥያቄ በሚመለከት እንዳስታወቀው፣ ኮሎኔሏ ተከላከሉ የተባሉበት የሕግ አንቀጽ 684(3) ከስድስት ወራት የማይበልጥ ቀላል እስራትና የገንዘብ መቀጮ መሆኑን ጠቁሞ፣ በ75,000 ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ፈቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዘው በመገኘት ወንጀል እንዲከላከሉ የተፈረደባቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የአገር ውስጥ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም፣ በሌላ ክስ የአሥር ዓመታት እስር ስለተፈረደባቸው የቅጣት ጊዜያቸውን እንደጨረሱ ማቅረብ ይችላሉ በማለት ፍርድ ቤቱ ምንም ሳይል አልፎታል፡፡ በመዝገብ ቁጥር 141352 ተከላከሉ የተባሉት እነ አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ፣ እንዴት መከላከል እንዳለባቸው ዝርዝር መግለጫ እስከ ኅዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ በመንገር ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ አቀረበ

  መንግስት ስኳር ኢንተርፕራይዞችን ወደግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ባለሐብቶች እንዲሳተፉ...

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...