Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ንግድ ሚኒስቴር የኮነነው የንግድ ምክር ቤቶች የምርጫ ሒደት

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የንግድ ኅብረተሰቡን ወክለው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን የሚመሩ ኃላፊዎችን ከመምረጥ ሒደት ከምርጫ ሥርዓት አፈጻጸም ጋር በተገናኘ የሚፈጸሙ የሕግ ጥሰቶች እንዳልተገቱ እየተገለጸ ነው፡፡

  በዚህ አኳኋን ታይተዋል የተባሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጣልቃ ከሚገቡ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ንግድ ሚኒስቴር፣ የንግድ ምክር ቤቶች ምርጫዎች አዋጅና መመርያን የተከተሉ እንዲሆኑ የሚያያሳስብ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ይሁንና ከአዋጁና ከመመርያዎቹ ውጭ አሁንም ምርጫዎች እየተካሄዱ በአመራር ቦታው ላይ የሚቀመጡት ሰዎችም በተደጋጋሚ ቦታውን በፈረቃ እየተቀራመቱ መምጣታቸው አነጋጋሪ እያደረገው ነው፡፡

  በተለይ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በቦርድ አባልነት ለማገልገል በሚካሄደው ምርጫ ብሎም በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት ውክልና ለማግኘት የሚደረጉ ሽኩቻዎች የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን እየተጻረረ እንደመጣ የሚገልጹም አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት፣ አባል ምክር ቤቶች እንዲገዙበት ያፀደቀው መመርያ የጣሰ ነው ተብሏል፡፡ በተለይ አንድ ተመራጭ ለምን ያህል ዓመታት በኃላፊነትና በተመራጭነት ማገልገል ይችላል የሚለው ሐሳብ በተለያዩ ወገኖች ትችት የሚሰነዘርበት ሆኗል፡፡ ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ማንኛውምም ተመራጭ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ ማገልገል አይችልም የሚል መመርያ ማጽደቁ ይታወቃል፡፡ ከዚህ መተዳደሪያ ደንብ ውጭ እየተሠራ ነው የሚለው ትችት በመበራከቱ ንግድ ሚኒስቴር ጉዳዩን ለመከታተል እንደተገደደ ታውቋል፡፡

  ከአንድ ሳምንት በፊት በንግድ ሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ ያላ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፣ ምርጫዎቹ ፍትሐዊና አሳታፊ እንዲሆኑ አሳስቦ ነበር፡፡ ከሚኒስትሩ ደብዳቤ በኋላ ምርጫ ያካሄዱት የአዲስ አበባና የአማራ ንግድ ምክር ቤቶች ግን ጥያቄ ያስነሱ ምርጫዎች አካሂደዋል በመባሉ ንግድ ሚኒስቴር እንደሚያጣራ ማስታወቁ ተነግሯል፡፡

  በተለይ እሑድ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና የምርጫ ሒደት የንግድ ሚኒቴርን ማሳሰቢያም ሆነ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን የተከተለ አይደለም ተብሏል፡፡ በዕለቱ የክልሉን የንግድ ምክር ቤት ምርጫ ተከትሎ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት አቶ ጌታቸው አየነው ናቸው፡፡ አቶ ጌታቸው ይህንን ንግድ ምክር ቤት በፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ ሲመረጡ ከአራት የምርጫ ዘመን በላይ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ንግድ ምክር ቤቶችን እንደ አዲስ ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሠረት የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲቋቋም፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የመጀመርያው ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው ቢሸነፉም፣ የክልሉን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ሳይለቁ እስካሁን ቆይተዋል፡፡ በእሑዱ ምርጫም ለአራተኛ ጊዜ ዳግመኛ መመረጣቸው ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ ማገልገል እንደማይቻል የተነገረውን መተዳደሪያ ደንብ ይጻረራል ተብሏል፡፡

  የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያካሄደው ምርጫ በአዋጁ የተመቀጡትን ድንጋጌዎችም ሆኑ የንግድ ምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ በጣሰ አካሄድ መካሄዱ ተመልክቷል፡፡ አቶ ጌታቸው ግን አዋጅና መመርያን የሚፃረር ነገር አልተካሄደም ይላሉ፡፡ ሕጋዊ ሒደቱን አልጠበቀም የሚሉ ወገኖች የሚያሰሙት ቅሬታ፣  የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን የሚያካሂደው በሥሩ ያሉ አባል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የየራሳቸውን ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደው ለክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲወከሉ ነው ከሚለው ነጥብ ይነሳል፡፡ ነገር ግን ይህ አሠራር በትክልል ሳይተገበር የተካሄደው ምርጫ ትክክል አይደለም ብለው ይሞግታሉ፡፡

  መስከረም 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ የተጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ከንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ምርጫ ጋር ተያይዞ የአሠራር ደንብን ያልተከሉና የአሳታፊነት ጉድለት የሚስተዋልባቸው፤ በተለይም ምርጫ ሳያካሂዱ ወደ ቀጣዩ እርከን ነባር አመራር ይዘው የሚቀርቡባቸው ምርጫዎች እየተካሄዱ ነው በሚል የተለያዩ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች እየቀረቡ ይገኛሉ፤›› በማለት ሒደቱን ኮንኗል፡፡ አያይዞም የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በተዋረድ በየደረጃው የሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 341/1995 እና በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት በሕጋዊ መንገድ ምርጫቸውን ማካሄዳቸውንና ተወካዮቻቸውን መሰየማቸውን መከታተል እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምርጫ ያላከናወኑ የክልልና የከተማ አስተዳሮች እንዲሁም በተዋረድ የሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ካሉም ሕጉን ተከትለው ግልጽ፣ ፍትሐዊና አሳታፊ ምርጫ እንዲያከናውኑ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግ ደብዳቤው መመርያ ይሰጣል፡፡

  ሆኖም ደብዳቤ ከወጣና ከተሠራጨ በኋላ የአማራ ንግድ ምክር ቤት ያካሄደው ምርጫ፣ ይህንን ማሳሰቢያ ያላገናዘበ ነው ቢባልም አቶ ጌታቸው ግን ተጻፈ የተባለውን የሚኒትሩን ደብዳቤ አለመመልከታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና የምርጫ ሒደትን ብቻ ሳይሆን፣ በቅርቡ የተካሄዱትን የአገር አቀፍ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራትን የምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ ሐደቶችም እንዲጣሩ ይደረጋል፡፡ በተለይ አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ እንደተባለው አዋጅና መመርያን የሚፃረር ሆኖ ከተገኘ፣ ንግድ ሚኒስቴር ምርጫው እንዲደገም ሊያደርግ እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ፡፡

  የአገር አቀፍ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነሐሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ ከጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ከደቡብ ክልል ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች ውክልና ትክልል ያለመሆኑን፣ ምርጫው ከአዋጁና ከመተዳደሪያ ደንብ ውጭ የተካሄደ መሆኑን በመግለጽ ንግድ ሚኒስቴር ሁኔታውን እንዲመረምርና በዕለቱ የተካሄደው ምርጫ እንዲደገም መጠየቁም አይዘነጋም፡፡ ከዚህም ባሻገር ከሥር ምርጫ ሳያካሂዱ አባላቱ በቀጥታ ወደ ላይኛው አካል ተወክለዋል የሚል ትችት የቀረበበት የአዲስ አበባ ዘርፍ ምክር ቤት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዘርፍ ምክር ቤት አባል በሆነበት የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተወከለው የራሱን ጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሂድ በመሆኑ የሕግ ጥሰት ፈጽሟል የሚሉ አቤቱታዎች ለንግድ ሚኒስቴር  መቅረባቸው አይዘነጋም፡፡

  የአገር አቀፍ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት እንዳልተፈጸመ በመግለጽ የቀረበውን ክስ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን ክስ እንደማይቀበሉትና መሠረተ ቢስ እንደሆነ ጭምር መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ግን ይህንኑ ክስ መነሻ በማድረግ ጉዳዩን እየመረመረ ነው፡፡  

  የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ምርጫም አንድ ዕጩ በብቸኝነት ቀርበው የተወዳደሩበትና የተመጡበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መካሄዱ አግባብ አይደለም ተብሏል፡፡ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተገኘው መረጃ አቶ ኤልያስ ገነቴ ብቸኛ ተወዳዳሪ የሆኑት መስፈርቱን የሚያሟላ ተቀናቃኝ ዕጩ ባለመቅረቡ ነው ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደምም ሁለት ፕሬዚዳንቶች ያለተወዳዳሪ ተመርጠዋል በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

  እንዲህ ያሉት ቅሬታዎች መበራከታቸው ምርጫው በቅርቡ በሚካሄደው የአገር  አቀፍ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡ የኢትጵያ ንግድ ምክር ቤት በበኩሉ በትክክለኛው መንገድ አልተካሄዱም የተባሉ ምርጫዎች መኖራቸው ከተረጋገጠ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

  እያንዳንዱ አባል ምክር ቤት፣ አሉኝ የሚላቸውን የአባላት ቁጥርና በትክክልም አባል መሆናቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች፣ ሕጋዊ ነጋዴዎች መሆናቸውን የሚያጣራ ኮሚቴ በመዋቀሩ ክትትል እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

  አቶ ጌታቸው ግን በዚህ አስተያየት አይስማሙም፡፡ ምርጫው በአዋጁ መሠረት ተከናውኗል ይላሉ፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች መተዳደሪያ ደንብ አንድ ተመራጭ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚያገለግል የገደበው ነገር ስለሌለ ተወዳድረን ተመርጠናል ብለዋል፡፡

  ከባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተወከሉ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አንድ ተመራጭ ለሁለት የምርጫ ዘመን ማገልገል አለበት የሚለው መመርያ እንደማይመለከታቸውም ገልጸዋል፡፡

  ‹‹እኛ የፕሬዚዲየም አባል በመሆናችን በቀጥታ ውክልና አለን፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ከሦስት ዓመት በፊት በተወሰነው ውሳኔ መሠረት በቀጥታ የጉባዔው ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ በማስረዳት ከሁለት ተፎካካሪዎቻች ጋር ተወዳድረው በማሸነፍ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

  የሥር ንግድ ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ሳያካሂዱ በክልል ደረጃ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ አይችሉም በሚለውም አይስማሙም፡፡ ይህንን በተመለከተ ሚኒስትሩ የጻፉትን ደብዳቤ እንዳልተመለከቱት ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተሳተፉ ምክር ቤቶች፣ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ያላካሄዱ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ጠቅላላ ጉባዔ ስላላካሄዳችሁ በክልሉ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አትሳተፉም ማለት አንችልም፡፡ ስለዚህ አሳትፈናቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች