Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአገር ውስጥ ተቋራጮች ብቻ የተሳተፉባቸውና ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበላቸው መንገዶች ግንባታ ተጀመረ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በ2008 በጀት ዓመት እንዲገነቡ የውል ስምምነት ከተፈረመባቸው መንገዶች ውስጥ ከ5.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ የአራት መንገዶች ግንባታ ሥራ  ሲጀመር፣ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው ሁለት መንገዶች ተጠናቀው ለትራፊክ ክፍት መደረጋቸው ተገለጸ፡፡

  ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአራቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚከናወኑት በአገር በቀል ኮንትራክተሮች ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካለፈው ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ቀናት ውስጥ ግንባታቸው የተጀመሩት እነዚህ መንገዶች ከአይከን ዙፋን አንገረብ፣ ከበለስ መካነ ብርሃንና ከሶሮቃ እርጐዬ ከዳበት አጅሬ ድረስ የሚዘረጉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

  እነዚህ በሰሜን ጐንደር ውስጥ የሚገኙት አራቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ5.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ሲሆን፣ የኮንትራት ስምምነታቸውም ባለፈው በጀት ዓመት የተፈረመ ነው፡፡ አራቱ ፕሮጀክቶች ውስጥ አይከን ዙልፋን አንገረብ ድረስ የሚዘልቀውንና ከሶሮቃ – እርጐዬ ድረስ ያለውን 92 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን ጨረታውን አሸንፎ ሥራውን የጀመረው ሱር ኮንስትራክሽን እንደሆነ አቶ ሳምሶን ገልጸዋል፡፡

  ሱር ኮንስትራክሽን ከሶሮቃ እርጐዬ ድረስ ያለውን መንገድ ለመገንባት አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 1.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከአይከን – ዙፋን – አንገረብ ድረስ ያለው መንገድ 1.9 ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል ተብሏል፡፡

  ከበለስ – መካነ ብርሃን ድረስ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት ዲዛይንና ግንባታውን ለማከናወን ባለፈው ዓመት ኮንትራት የፈረመው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሳምሶን፣ ዲዛይንና ግንባታውን በማጣመር የሚገነባው ይህ መንገድ ባለፈው ዓርብ መስረከም 27 ቀን ጀምሮ ግንባታው ተጀምሯል ብለዋል፡፡

  መከላከያ ኢንጂነሪንግ ይህንን ግንባታ ለማከናወን አሸናፊ የሆነበት ዋጋ አንድ ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከአደባት እስከ አጅሬ ድረስ የሚዘረጋውን 43 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት በጨረታ በማሸነፍ ግንባታውን መስከረም 28 ቀን ማካሄድ የጀመረው ኩባንያ፣ ፓወር ኮን የተባለው አገር በቀል ተቋራጭ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ኮንትራክተሩ እንዲህ ባለው የመንገድ ፕሮጀክት ውስጥ ሲሠማራ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ሰብ ኮንትራት ሥራዎችን ሲሠራ እንደቆየ የተነገረለት ፓወርኮን ኮንስትራክሽን፣ የዳባት – አጅፌ መንገድ ግንባታን ለማከናወን ያሸነፈበት ዋጋ 931 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

  ከእነዚህ መንገዶች በተጨማሪ አማራና ትግራይ ክልሎችን ከሚያካልሉት አንዱ ከደባርቅ – ዛሬማ የሚዘልቀው እንዲሁም ከአዲራመፅ – አዲባሀከር የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የሚያስችል የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡

  እነዚህ መንገዶች ‹‹ለኮንትራክተሮች ባይሰጡም በቅርቡ የጨረታ ውጤቱ ታውቆ በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ ይገባሉ፤›› ተብሏል፡፡ ግንባታቸው ከተጀመሩት መንገዶች በተጓዳኝ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሁለት መንገዶችን  ባለሥልጣኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ግንባታቸው ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት መንገዶች በትግራይ ክልል የሚገኙት ከጠገደ ከተማ ንጉሥ ድረስ የሚዘልቀው 23 ኪሎ ሜትር መንገድ አንዱ ነው፡፡ በራማ ኮንስትራክሽን ተገንብቶ የተጠናቀቀው ይህ መንገድ 540 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡

  ከትናንት በስቲያ ግንባታው የተጠናቀቀውና ሥራ የጀመረው ሌላው መንገድ ደግሞ ከዳንሻ – አኩራፊ – ማይከዶራ ድረስ ያለው 118 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በሦስት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ቢታቀድም፣ ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ በሁለት ዓመት ከመንፈቅ እንደተጠናቀቀ መረጃው ያመለክታል፡፡

  1.7 ቢሊዮን ብር የፈጀው ይህ ፕሮጀክት የተገነባው በሱር ኮንስትራክሽን መሆኑን የገለጹት አቶ ሳምሶን፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ መሠረት ግንባታ ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

  ለመሠረተ ልማት ግንባታው እንደ ወሰን ማስከበርና ግንባታዎችን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ሌሎች ችግሮች ካላጋጠሙ በቀር፣ ግንባታዎችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ እንደሚቻል እየታየ ነው ብለዋል፡፡

  የሱር ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ የማነ በበኩላቸው፣ የመንገዱን ግንባታ ከኮንትራት ውሉ ቀድሞ ለመጨረስ ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

  ‹‹አንድም አገር በቀል ኮንትራክተር የወሰደውን የግንባታ ፕሮጀክት ከተያዘለት ጊዜ በፊት ማጠናቀቅ አልቻለም የሚለውን ተደጋጋሚ ትችት መስበር አለብን ብለን የገባንበት ፕሮጀክት በመሆኑ፣ በዕቅዳችን መሠረት ቀድመን ጨርሰን ለማስረከብ ችለናል፤›› ብለዋል፡፡

  ሱር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቱን ቀድሞ ለመጨረስ ካደረገው ዝግጅት ባሻገር ወሰን ከማስከበር አኳያ ችግር እንዳይገጥመው መንገዱ ከሚያልፍባቸው እንደ ጠገዴና ካሳ ሁመራ ካሉ ወረዳዎች አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር የወሰን ማስከበር ሥራው በቶሎ እንዲጠናቀቅ በማደረግ ጭምር ግንባታው እንዲፋጠን ለማደረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ካሳ ያልተከፈላቸው ባለይዞታዎች ክፍያ አላገኘንም ሳይሉ ንብረት ለማንሳት ያደረጉት ትብብር ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረግ ለዕቅዱ መሳካት እንደረዳ አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡

   

    

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች