Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የሕግ ጥያቄ ያስነሳው የንብ ባንክ ሕንፃ ግንባታ ኮንትራት ውል

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ባንክ ለማቋቋም እንደ ዛሬው 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማይጠየቅበት፣ ይልቁንም 20 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በቂ በነበረበት ወቅት ከተቋቋሙት የግል ንግድ ባንኮች አንዱ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ነው፡፡ ግንቦት 1991 ዓ.ም. ተመሥርቶ ጥቅምት 18 ቀን 1992 ዓ.ም. በይፋ ሥራ ሲጀምር 27.6 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና 27 ሠራተኞችን ይዞ ነበር፡፡

  ከተመሠረተ 16 ዓመታት ያስቆጠረው ይህ ባንክ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃውን ለመገንባት መስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የጨረታ አሸናፊ መሆኑን ይፋ ካደረገው ተቋራጭ ድርጅት ጋር ሲፈራረም እንደተገለጸው፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 1.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የሠራተኞቹ ቁጥር ከ3,900 በላይ እንደደረሰ፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ፎንጃ ገልጸዋል፡፡

  እንደ አቶ ክብሩ ገለጻ፣ ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ431 ሺሕ በላይ ደንበኞች ማፍራት መቻሉን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም 12.6 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት 7.8 ቢሊዮን ብር ብድር ስለመስጠቱ ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ የባንኩ ሀብትም ከ15.7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ ባንኩ አቅሙን እያጐለበተ በመምጣቱም ሌሎች የግል የንግድ ባንኮች እንደሚያደርጉት ሁሉ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ባንኩ ከአሥራ ስድስት ዓመታት በፊት ሾላ አካባቢ በሚገኝ ሕንፃ ቀጥሎም በጆሞ ኬንያታ መንገድ ፐርፕል ካፌ ከሚገኝበት፣ መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኝ የኪራይ ቤቶች ሕንፃ ላይ ቢሮውን ከፍቶና ዋና መሥሪያ ቤቱን በዚያው በማድረግ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ካለፉት 12 ዓመታት ወዲህም ዋና መሥሪያ ቤቱን ወደ ደንበል ሕንፃ በማዞር እየሠራ ይገኛል፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ የግል ባንኮች ንብ ባንክም ከዓመታዊ ወጪው ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን ለቤት ኪራይ ያውላል፡፡ በ12 ዓመታት የደንበል ሕንፃ ቆይታው ለዋና መሥሪያ ቤትነት የሚጠቀምበት ቢሮ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለኪራይ ወጥቶበታል፡፡   አቶ ክብሩ ለዋና መሥሪያ ቤት የኪራይ እስካሁን ምን ያህል ወጪ እንደወጣ ባይገልጹም፣ የባንኩም ሆነ የሌሎች ባንኮች ከፍተኛ ወጪ ኪራይ ስለመሆኑ ግን ጠቅሰዋል፡፡ በየጊዜው ዋጋው እየናረ መምጣቱም ለዋና መሥሪያ ቤትም ሆነ ለቅርንጫፎች የሚጠቀሙባቸውን ሕንፃዎች በመተው የራሳቸውን ሕንፃ እንዲገቡ እያስገደዳቸው ይገኛል፡፡

  ንብ ባንክ ከመሬት በታች አራት፣ ከመሬት በላይ ደግሞ 33 ወለሎች ያሉት ባለ 37 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ከአራት ዓመታት በኋላ ተጠናቆ እንደሚረከብ በግንባታ ስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

  ሕንፃ ለማስገንባት ባንኩ በድጋሚ ባወጣው ጨረታ አሸናፊ ከተባለው የቻይናው ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክና ቴክኒካል ኮርፖሬሽን ሊሚትድ ኩባንያ ጋር የግንባታ ውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ይሁን እንጂ በስምምነታቸው ወቅት ባንኩም ሆነ ኮንትራክተሩ የግንባታ ዋጋው ምን ያህል እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡  

  የባንኩ ኃላፊዎች ኮንትራክተሩ ያሸነፈበትን ዋጋ እንዲገልጹ ሲጠየቁም፣ በዕለቱ ዋጋውን መናገር እንደማይችሉ ይህም ተጨማሪ ድርድሮች ስለሚደረጉ ነው በማለት አልፈውታል፡፡ ኮንትራት የተፈረመበት ውልና የዋጋ መጠን እንዴት አይገለጽም የሚል መከራከሪያ ቢቀርብላቸውም፣ ‹‹ኮንትራክተሩ ያሸነፈበትን ዋጋ ለሚመለከታቸው አሳውቀናል፡፡ ስለዚህ አሁን ለመግለጽ አንችልም፤›› ማለታቸው ያልተለመደ ነበር፡፡ የቻይናው ኩባንያ የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስተር ዡ ጁን ለሪፖርተር እንደገለጹት ግን፣ ኩባንያው ለግንባታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 1.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

  ከቀረቡት ኮንትራክተሮች ውስጥ አነስተኛ ዋጋ ማቅረብ በመቻላቸው አሸናፊ ሆነዋል ቢባልም፣ የጨረታው ሒደት ግን ከውሉም በፊት ጥያቄ ሲያስነሳ መቆየቱ  ታውቋል፡፡ የኮንትራት ውሉ ከተፈረመ በኋላ ከሌሎች ተጫራች ኮንትራክተሮች የሚደመጠው  ቅሬታ የኮንትራት ውሉን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡  

  የዘገየው ስምምነት

  ንብ ባንክ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ከወጠነ ከ10 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ግንባታውን እውን ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ከተገለጸ ደግሞ ከስድስት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የግንባታ ቦታ ከተረከበም ዓመታት ቢያልፉም ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ በወጠነው አልተጓዘም፡፡ ዘግይቷል፡፡

  ንብ  ኢንተርናሽናል ባንክ እንደ አዋሽ ባንክ መንትያ ሕንፃዎች ዓይነት ለመገንባት ተነሥቶ የነበረው ከእህት ኩባንያው ንብ ኢንሹራንስ ጋር በመሆን ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት ንብ ባንክና ንብ ኢንሹራንስ በጋራ ሕንፃውን ለመገንባት በመስማማታቸው፣ የጋራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁመው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እህትማማቾቹ ኩባንያዎች የዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ሕንፃ ባሰቡት ጊዜ ውስጥ መገንባት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት፣ የሕንፃ ግንባታው ሒደቶች መሰናከል የጀመሩትን በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ባንኩ ለብቻው ከኢንሹራንስ ኩባንያው ተነጥሎ ሕንፃውን ለመገንባት በመወሰኑና ኢንሹራንስ ኩባንያውም በራሱ መንገድ መጓዝ በመፈለጉ በጋራ የመገንባት ህልማቸው ሳይሳካ ይቀራል፡፡

  የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወልደትንሳይ ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹት፣ ንብ ባንክና ንብ ኢንሹራንስ በጋራ ለመገንባት የጀመሩት ሥራ ሊቋረጥ የቻለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ በጋራ መገንባቱ ባንኩን ከፍተኛ ወጪ ያስወጣዋል የሚል ምክንያት ይቀርብ እንደነበርም፣ ጥያቄ እያስነሳ በሚገኘው የግንባታ ስምምነት ወቅት ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው መመርዎች አኳያ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎቹ ስላልፈቀዱ፣ በተያዙት ቦታዎች በተናጠል መገንባት እንደሚገባ በመታመኑ ኩባንያዎቹ ለየብቻ ለመገንባት መነሳታቸውን የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ የሁለቱም እህትማማች ኩባንያዎች ቦርዶች አምነውበት ለየራሳቸው ባለአክሲዮኖች አሳውቀው በተደረሰ ስምምነት መሠረት፣ በተናጠል እንዲሠሩ ለማድረግ ሲሞከር ጊዜ እንደፈጀ አስረድተዋል፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በጋራ ይሠራ ስለነበርም በተናጠል የባንኩን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ማቋቋምና አስፈላጊ የፖሊሲ ፕሮጀክት ማንዋል መቅረጽና ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን የወሰዱት ጊዜ ተደማምሮ፣ ሕንፃው ሳይገነባ ለመቆየቱ ምክንያት እንደነበርም አብራርተዋል፡፡ ለሕንፃ ግንባታ ተሰይሞ የነበረው አማካሪ ድርጅት በሌላ እንዲቀር መደረጉም ለፕሮጀክቱ መዘግየት ሌላኛው ምክንያት ነበር፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት የግንባታ ውል በመፈረሙ በውሉ መሠረት በጊዜ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡

  አቶ ወልደትንሳይ ‹‹ይህ ፕሮጀክት ረዥም ጊዜ የወሰደና የዘገየ መሆኑ ሁላችንም ሲያስጨንቀን ነበር፤›› በማለት በፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ አሁን ወደ ተግባር መገባቱ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል፡፡

  ባንኩና የጨረታ ሒደቱና አነጋጋሪው የጨረታ ውጤት

  ባንኩ ለዚህ ሕንፃ ግንባታ ሁለት ጊዜ ጨረታ አውጥቶ ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ጨረታ ሰርዞ ለሁለተኛ ጊዜ ባወጣው ጨረታ ስድስት የቻይናና ሁለት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተሳታፊ ሆነው ነበር፡፡ ከእነዚህ ተጫራቾች ውስጥ የቴክኒክ መመዘኛውን አልፈዋል ተብለው ሲጠባበቁ ከነበሩት ኮንትራክተሮች ውስጥ ሦስቱ በጨረታ ሒደቱ ችግር ያለበት ስለመሆኑ ሲከራከሩ የቆዩ ሲሆን፣ ባንኩ አሸናፊውን መርጫለሁ ካለም በኋላ ጉዳዩን እየሞገቱ ሲሆን፣ ባንኩ ከጨረታ መመርያ ውጭ በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ሕግ የወሰዱም አሉ፡፡ ከቻይናው ኮንትራክተር ጋር ውል ከተፈረመ በኋላም ባንኩ የፈጸመው ውል ግን ፈጽሞ ሊፈጸም እንደማይገባ የሚጠቁሙ መረጃዎች ከየአቅጣጫው መሰንዘር ጀምሯል፡፡ በጨረታው ላይ ከተሳተፉ ኮንትራክተሮች መካከል አንዳንዶቹ ግን የጨረታ ሒደቱ ትክክል አልነበረም በሚል የባንኩን ውሳኔ በመቃወም ብቻ ሳይመለሱ ጉዳዩን ወደ ሕግ አካላት ወስደዋል፡፡ ባንኩ ከጨረታ አሠራር ውጪ ከቻይናው ኮንትራክተር ጋር መዋዋሉን ያስረዱልኛል ያላቸውንም መረጃዎች እያቀረቡ ነው፡፡

  በተለይ ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ታኮን) የባንኩ የጨረታ አካሄድ ትክክል እንዳልነበር፣ በሒደቱ ላይ የታዩት ግድፈቶች ይታረሙ በማለት ያቀረበው ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ምላሽ ባለማግኘቱ ጉዳዩን ወደ ሕግ ወስጃለሁ ብሏል፡፡ ለዓቃቤ ሕግ ደብዳቤ ጽፏል፡፡

  ታኮን የጨረታ ሒደቱ ትክክል አልነበረም ብሎ የሚሞግተው አሁን አሸናፊ ተብሎ የኮንትራት ውል የፈጸመው የቻይናው ኮንትራክተር በጨረታ መመርያው መሠረት ያቀረበው የጨረታ ማስከበሪያ (Bid security) መመርያው ከሚያዘው ውጭ መሆኑ ስለተጠቆመ፣ ባንኩ ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ታኮን ጠይቋል፡፡ ሌሎቹም ቅሬታ አለን ያሉት ኮንትራክተሮች በተመሳሳይ ባንኩን ጠየቀዋል፡፡ ነገር ግን ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡

  እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ አሸናፊ የተባለው ኮንትራክተር በጨረታ መመርያው መሠረት የመጫረቻ ሰነዱ ሳይከፈት ከጨረታ ውጭ መሆን ነበረበት ይላሉ፡፡ ምክንያቱም በጨረታ መመርያው ላይ አንድ ተጫራች ለጨረታ ማስከበሪያው ማስያዝ ያለበት ገንዘብ ማረጋገጫ ለ178 ቀናት መሆን በግልጽ የሚያስቀምጥ ቢሆንም፣ አሸናፊ የተባለው ኮንትራክተር ያቀረበው ለ150 ቀናት ማስያዣ ነው፡፡ ስለዚህ በጨረታው መመርያ መሠረት ይህንን ካላሟላ ወዲያው ከውድድር ውጭ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን ባንኩ ይህንን ወሳኝ ጉዳይ ወደኋላ በመተው ሕገወጥ ተግባር እንደፈጸመ ይናገራሉ፡፡

  ታኮን የጨረታ ሒደቱን የተመለከቱ አቤቱታዎችን ያቀረበባቸው ተከታታይ ደብዳቤዎች ጥያቄያቸው መልስ ባለማግኘታቸው እንደገና መስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በጨረታ ሒደቱ ላይ አሉ ያላቸውን ግድፈቶች እርምት እንዲሰጥበት ማሳሰቢያ መስጠቱንም ታኮን ይገልጻል፡፡ በግንባር ቅሬታቸውንም ያቀረቡ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ታኮን በጻፈው ደብዳቤ በጨረታ ሰነዱ ላይ የተመለከተው የተጫራቾች መመርያ በባንኩ በኩል በአግባቡ ተፈጻሚ ባለመሆኑ ታኮን ቅሬታ ያደረበት መሆኑን በድጋሚ በመግለጽ ይጀምራል፡፡ አያይዞም የጨረታው አሸናፊ በመመርያው በተቀመጠው መሠረት ለተጫራቾች በሙሉ በይፋ ያላሳወቁ መሆኑም፣ ጨረታው የሚመራበት መመርያ ላይ የተመለከተውን መመዘኛና መሥፈርት መጣሱን በግልጽ ያመለከተ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡

  የጨረታ ሒደቱ ላይ ተፈጥሯል ላለው ጥሰት በተከታታይ ለጻፈው ደብዳቤዎች ከባንኩ ምንም ዓይነት መልስ ሳያገኝ በመቅረቱ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ መገደዱን አመልክቷል፡፡ ታኮን ለዓቃቤ ሕግ በጻፈው ደብዳቤም በጨረታ ሰነዱ ውስጥ የሰፈረው አስገዳጅ የሆነው የመንግሥት ግዥ የተጫራቾች መመርያ መሠረት በጨረታ አመራር ላይ ያለ ቅሬታ መስተናገድ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህ ቅሬታ ሳይስተናገድ ባንኩ አሸናፊ ነው ከተባለው ኮንትራክተር ጋር ውል ለማሰር የሚያስችል አንዳችም የሕግ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በማስታወስ፣ ባንኩ ተገቢውን የእርምት ዕርምጃ እንዲወስድ፤ ካልሆነም ከሕግ ምክንያታዊነት አንፃር ተፈጻሚነት የሚያገኝ ከሆነ ጉዳዩን ሥልጣን ባለው አካል ፊት ለማቅረብ እንደሚገደድ በማሳወቅ ወደ ክስ ገብቷል፡፡

  ባንኩ የፌዴራል የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር መመርያ 2011 በመተላለፉ በጨረታ ተሳታፊዎች ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ሚዛናዊነት ባልጠበቀ ሁኔታ ጨረታው እንዲመራ በማድረጉና የቻይናው ኩባንያ የጨረታው አሸናፊ እንዲሆን መደረጉ ከሕግም ሆነ ከሞራል የሚጻረር ነውም ብሏል፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የጨረታው አፈጻጸም እንዲቆይና ሁኔታውንም እንዲመረምር ጠይቋል፡፡ ከታኮን ሌላ ቅሬታ አላቸው የተባሉ ሁለት ተጫራቾችም በተመሳሳይ ጉዳዩን ወደ ሕግ የወሰዱት ሲሆን፣ የፋይናንስ ተቋማትን ለሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቤት ስለማለታቸውም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ አቶ ክብሩ በበኩላቸው በክሱ አይስማሙም፡፡ ቅሬታቸውን በአምስት ቀን ማቅረብ ነበረባቸው ሲሆን፣ ይህንንም አላደረጉም ብለዋል፡፡

  ለአገር በቀል ኮንትራክተር የተሰጠው ዕድል ተሰርዟል

  እንደ ቅሬታ አቅራቢ ተጫራቾቹ የጨረታ ሒደቱ ሌላም ግድፈት ነበረው ይላሉ፡፡ በአገሪቱ የጨረታ ሒደት የአገር በቀል ኮንትራክተሮች የሚጠቅመው አሠራር በባንክ የጨረታ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ ይህ አገር በቀል ኮንትራክተር ካሸነፈ የተወሰነ ፐርሰንት ዕድል ያገኛል፡፡ ይህንኑ በማሰብ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ዋጋቸውን በማስላት የጨረታ ሰነዳቸውን አስገብተዋል፡፡

  በጨረታው መመርያ ውስጥ ሁሌም እንደሚደረገው በአንድ ጨረታ የአገር ውስጥና የውጭ ኮንትራክተሮች ተወዳድረው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሩ ያቀረበው መወዳደሪያ ዋጋ ከውጭ ኮንትራክተሮቹ ዋጋ በ7.5 በመቶ ከፍ ካለ አሸናፊ የሚሆነው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሩ ይሆናል የሚል ነው፡፡

  በንብ ባንክ ጨረታ መመርያ ላይም ይህ ተቀምጦ ነበር የሚሉት ቅርታ አቅራቢዎቹ ተጫራቾች፣ የመወዳደሪያ ዋጋቸውን ካቀረቡ በኋላ ይህ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ይደግፋል የተባለው አንቀጽ መቅረቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን ይላሉ፡፡ ይህም ራሱ ግድፈት ነው የሚሉት እነዚሁ ኮንትራክተሮች፣ ዋጋ የገባውም በ7.5 በመቶ የሚገኘውን ዕድል ታሳቢ በማድረግ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡   

  ይሁን እንጂ የመወዳደሪያ ዋጋው ከገባ በኋላ ባንኩ ይህንን አገር በቀል ኮንትራክተሮች ይጠቅማል የተባለውን የጨረታ መመርያው አካል መሰረዙን አሳውቋል፡፡

  የቅሬታ አቅራቢዎቹ ቢያንስ ዋጋ ከማስገባታችን በፊት ሊገለጽ ይገባ ነበር ይላሉ፡፡ ይህም ጉዳይ የጨረታ አካሄዱ እንደ ግድፈት ነው ይላሉ፡፡ አቶ ክብሩ በዚህ ጉዳይ በሰጡት ሐሳብ 7.5 በመቶውን ዋጋ በተመለከተ ደብዳቤ መጻፉን አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ይህ ማካካሻ ለመንግሥት ተቋማት እንጂ ለግል ድርጅት አይደለም በማለት ሞግተዋል፡፡

  ምላሽ ያጡት ደብዳቤዎችና የድርድር ጥያቄ

  የጨረታ ሒደቱን በተመለከተ ታኮን ከጻፋቸው ደብዳቤዎች መገንዘብ እንደተቻለው፣ የቻይናው ኩባንያ ያቀረበው የጨረታ ማስከበሪያ ሕጉ ከሚያገባው ውጭ መሆኑ ተጣርቶ ውሳኔ እንዲሰጠው ካቀረበው ጥያቄ ጐን ለጐን ለድርድር ዝግጁ መሆኑንም የሚገልጽ ነበር፡፡

  በተለይ መስከረም 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ‹‹በቻይናው ኩባንያ ላይ የቀረበው ጥቆማ ትክክል ሆኖ የጨረታውን ውጤት የሚቀይረው ከሆነ የቴክኒካል ማጣሪያውን ካለፉት ኩባንያዎች መካከል የላቀ ውጤት ያገኘው ታኮን ቢሆንም፣ ያቀረበውን ዋጋ በድጋሚ ማሻሻል የሚችል መሆኑንና ለዚህም የመደራደሪያ ሐሳቡን አቅርቧል፤›› በማለት ገልጿል፡፡

  ከመደራደሪያ ሐሳቦቹ መካከል ለመላው ተወዳዳሪዎች ከቀረበው ዝቅተኛ ዋጋ በታች የግንባታ ዋጋውን ቀንሶ ለመሥራት ፍቃደኛ መሆኑን የሚገልጽ ጭምር ነበር፡፡ በቴክኒካል ምዘናውም 100 በመቶ ያገኘ በመሆኑ፣ በሌሎች ተመሳሳይ ግንባታዎች ላይ ያሳየው አፈጻጸም ሆነ ያደረገው ዝግጅት ከፍተኛ በመሆኑ አራት ዓመት የተሰጠው የግንባታ ጊዜ በሦስት ዓመት እጨርሳለሁም በማለት በዚሁ የመደራደሪያ ሐሳቡን በገለጸበት በደብዳቤው አስታውቋል፡፡ ለዚህም ደብዳቤ ምላሽ በማጣቱ መስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም. የቻይናው ኩባንያ የጨረታ ማስከበሪያው በማያሟላ ሁኔታ የቀረበ መሆኑና በመመርያው መሠረት ይህንን ካላቀረበ ውድቅ በመሆኑ፣ መመርያው ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቆ ነበር፡፡

  ከተደጋጋሚ ጥያቄው በኋላ

  ታኮን በተከታታይ የቀረበው ጥያቄና በደብዳቤ ይመለስልኝ በማለት ያቀረበው ጥያቄና መደራደሪያ ሐሳቡ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቶ፣ ባንኩ አሸናፊ ካለው ኮንትራክተር ጋር መስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የኮንትራት ውል ፈርሟል፡፡

  ከዚህ የኮንትራት ውል አንድ ቀን ቀደም ብሎ የተጻፈ ስለመሆኑ በሚጠቅሰው የንብ ባንክ ደብዳቤ ታኮን የደረሰው መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡ ባንኩ ምላሽ የሰጠው ዘግይቶም መሆን ጉዳዩን የበለጠ አነጋጋሪ ያደገው ሲሆን፣ የአሸናፊው ኮንትራክተር ማንነት የሚገለጽ ደብዳቤም የኮንትራት ውሉ ከተፈረመ በኋላ መድረሱም በተለይ ከመጀመሪያው ጀምሮ ቅሬታ አለን ያሉትን ተጫራቾች የጨረታ ሒደቱ ግልጽነት የጐደለው እንደነበር ያረጋግጥልናል ብለዋል፡፡ የጨረታ አሸናፊውን ከማሳወቅ አኳያ ቀድሞ መፈጸም የነበረበት ቢሆንም ባንኩ አሸናፊውን ድርጅት መምረጡን፣ ያሸነፈበትን ዋጋ ያሳወቀውና በተለይ በተከታታይ ደብዳቤዎቹ ምላሽ የተሰጠውም ባንኩ ኮንትራት ውሉን መፈረሙ ከተገለጸ በኋላ ነው በማለትም የጨረታ ሒደቱንም ሆነ የባንኩን አሠራር ይኮንናል፡፡

  የዘገየ ነው የተባለውና መስከረም 20 ተጽፎ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ደረሰ የተባለው የባንኩ ምላሽ ላይ እንደተጠቀሰው ደግሞ፣ ከሕግ ውጭ የተሠራ ነገር የሌለ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ በተለይ ለታኮን በላከው ደብዳቤ ‹‹መስከረም 18 እና 20 ቀን ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ ደብዳቤ የቻይናው ኮንትራክተር ላይ የቀረበው የጨረታ ማስከበሪያ ቦንድ በማስታወቂያው የተመለከተውን አያሟላም የሚለውን ጉዳይ ተመልክቶ ውሳኔ የሰጠበትም ነው፡፡ ‹‹ጉዳዩን እንዲያየው፤ በዚህ ነጥብ ላይ ቅሬታ ካላችሁ ጨረታው እ.ኤ.አ. ኦገስት 10 ቀን 2016 ተወካዮች በተገኙበት ሲከፈት ማቅረብ ትችሉ የነበረ ከመሆኑም በላይ፣ በቴክኒካል ምዘና ግምገማ ማለፋችሁ ሴፕቴምበር 8 ቀን 2016 ሲገለጽላችሁ በሒደቱ ያላችሁ ቅሬታ ቢኖር በአምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት እንድታሳውቁ ይጠበቅ ነበር፤›› በማለት ባንኩ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ ደብዳቤ ላይ አክሎ እንዳመለከተውም ‹‹ታኮን ቅሬታውን በአምስት ቀን ባለማቅረቡ ሴፕቴምበር 21 ቀን 2016 ተወካያችሁ በተገኙበት ከተከፈተና ባቀረባችሁት ከፍተኛ ዋጋ ምክንያት ባለመመረጣችሁ ባንኩ ዝቅተኛ ዋጋ ካቀረበው ተጫራች ጋር ተገቢውን ድርድር አጠናቅቆ መጨረሻ ላይ ከደረሰ በኋላ፣ በደብዳቤ ያቀረባችሁዋቸው ተከታታይ ቅሬታዎች ተቀባይነት ያላቸው አይደሉም፤›› በማለት የታኮን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

  ባንኩ በጨረታ ሰነዱ ከተመለከተው ውጭ የፈጸመው ምንም ጉዳይ ስለሌለ ቅሬታቸውን መሠረት በማድረግ ካሸናፊው ኮንትራክተር ጋር የጀመረውን ሕጋዊ ሒደት የሚያስቆም ሕጋዊ መሠረት ያላገኘ መሆኑን በመግለጽም፣ አሸናፊ ከሆነው ኮንትራክተር ጋር ተፈራርሟል፡፡

  ይህ የባንኩ ምላሽ ግን ቅሬታ ባላቸው ኮንትራክተሮች ዘንድ ከሕግ ተጠያቂነት የማያድን ነው ተብሏል፡፡ የጨረታ መመርያዎች ተጥሰው እየታዩ ለዚህም በአግባቡ ምላሽ መስጠት ሲገባው አለመሰጠቱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ግድፈቶችም የሕግ ጥሰት አለባቸው በማለት ክስ መሥርተዋል፡፡ የቻይናው ኩባንያ አሸነፈ ተብሎ ደብዳቤ የደረሳቸውም ከኮንትራት ስምምነቱ በኋላ መሆኑ በራሱ አንድ ክፍተት ሲሆን፣ የጨረታ ሒደቱ በመንግሥት ግዥ እንደሚካሄድ ተገልጾና ይህም ተቀምጦ፣ ከዚህ አሠራር ውጭ ሲከናወን የሕግ ተጠያቂ የሚያደርስ ስለሆነ የጨረታ ውጤቱ በሕግ አግባብ ሊታገድ እንደሚገባ ያመለከቱበትን ክስም ለዓቃቤ ሕግ አስገብተዋል፡፡

  ከኮንትራት ውሉ በኋላ የደረሳቸው መረጃ ላይ የቻይናው ኩባንያ አሸናፊ ተብሎ የተገለጸው 1.61 ቢሊዮን ብር ጉዳይም ቢሆን ጨረታው ሲከፈት ያልነበረ የተምታቱ ነገሮች ያሉባቸው ናቸው በማለትም ጉዳዩ ግራ ያጋባ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

  በዚህ ጨረታ ሒደት ዙሪያ አሉ የተባሉ ችግሮች ስለመኖራቸው የሚገልጹ የባንኩ ባለአክሲዮኖችም ጨረታ ሒደቱ ብዙ ችግሮች ያሉበት ስለመሆኑ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ ኮንትራቱን በቶሎ ለመፈረም የተደረገው ጥረትም አጠራጣሪ ነገሮች እንደጫሩባቸው በመግለጽ ለባንኩ ባለአክሲዮኖችም እየተዘጋጁ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ አቶ ክብሩ እንዳመለከቱት ደግሞ በየትኛውም መንገድ ለቀረበው ክስ መልስ አለን የሚል ነው፡፡

  የቅሬታ አቅራቢዎቹን ክስ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የባንኩ የሥራ ኃላፊ እንደገለጹት ደግሞ፣ የጨረታ ሒደቱን በጥንቃቄ የተሠራ ነው፡፡ ሕግ አልጣስንም ብለዋል፡፡ ቀረበ የተባለው የድርድር ጥያቄም ቢሆን ከጨረታ አሠራር ውጭ በመሆኑ አልተቀበልነውም ይላሉ፡፡ በጨረታው ስለተሸነፉ ነው ይህንን ያደረጉት የሚሉት እኒሁ የሥራ ኃላፊ፣ የቻይናው ኩባንያ ጨረታ ማስከበሪያ ያቀረበው ማስያዣ ለ150 ቀንም ይሁን ለ200 ቀን ይህ የእኛ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡ ቢሆንም ሠነዱን መርምረን ያገኘነው ነገር የለም በማለት አስረድተዋል፡፡

  የቻይናው ኩባንያና ሁለተኛው ባንክ ሕንፃ ግንባታ

  እንደ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ የግል ባንኮች ሁሉ ንብ ባንክ ግዙፉን ሕንፃ እገነባበታለሁ ብሎ ከአዲስ አበባ አስተዳደር በሊዝ የተረከበው ቦታ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋም መንደር ተብሎ እየተጣራ በሚገኘው ሠንጋ ተራ አካባቢ ነው፡፡

  ከአዲስ አበባ ንግድ ኮሌጅ ፊት ለፊት ከንብ ባንክ የሕንፃ መገንቢያ አጠገብ ኅብረት ባንክና ዘመን ባንኮች በተመሳሳይ የዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ሕንፃዎች እየገነቡ ነው፡፡ ንብ ባንክም የሹሪንግ ሥራውን በማከናወን ከመሬት በላይ ወደ ላይ 33 ወለል ያለውን ሕንፃ ግንባታውን ለማከናወን ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ የሆነው የቻይና ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክና ቴክኒካል ኮኦፕሬሽን ሊሚትድ፣ በዚህ አካባቢ ከሚገነቡት የባንክ ሕንፃዎች ሁለተኛውን ለመገንባት ዕድል ያገኘበት ሆኗል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠየቀውን የኅብረት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ በመሆን ግንባታውን እያካሄደ ይገኛል፡፡ እንደ ቻይና ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል አይሆን እንጂ ከሠንጋ ተራ አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ የዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ሕንፃ ለማስገንባት ባወጡት ዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ እየሆኑ ያሉትም የቻይና ኩባንያዎች ሆነዋል፡፡ ይህም በዚያ የፋይናንስ ተቋማት ሕንፃ ግንባታዎችን የቻይና ኮንትራክተሮች እየወሰዱ መቀጠላቸውን ያሳያል፡፡

  እስካሁን የዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ሕንፃ ለማስገንባት ባወጡት ጨረታ የቻይና ኮንትራክተሮች እየገነቡዋቸው ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የወጋገን ባንክ፣ የሕብረት ባንክና ዘመን ባንክ ናቸው፡፡ የፋይናንስ ተቋማትን ሕንፃ ለመገንባት በቅርቡ በተከታይ በወጡ ጨረታዎች ላይ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ቢሳተፉም አሸናፊ መሆን አልቻሉም፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገነቡ የፋይናንስ ተቋማት ሕንፃዎች ውስጥ የሁለቱን ባንኮች ሕንፃ ግንባታ የተረከበው ይህ የቻይና ኩባንያ፣ በቻይና መንግሥት ባለቤትነት የተመዘገበ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከ20 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ በዚህ ቆይታው በተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ላይ ስለመሰማራቱ ሚኒስትር ዡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከከወናቸው መካከል በባህር ዳር ከሰማዕታት ሐውልት አጠገብ የሚገኘውን የባህር ዳር የስብሰባ አዳራሽ፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ይጠቀሳሉ፡፡ ሜድሮክ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካና ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ግንባታዎችም በዚሁ የቻይና ኮንትራክተር የተሠሩ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ዡ ገልጸዋል፡፡

   

   

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች