Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዓለምየደቡብ ሱዳን አማፅያን መሪ የጦርነት አዋጅ

  የደቡብ ሱዳን አማፅያን መሪ የጦርነት አዋጅ

  ቀን:

  ደቡብ ሱዳን ቀድሞውንም በመንጨላጨል ላይ የነበረው የሰላም ተስፋዋ ተዳፍኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ነፃነቷን ከሱዳን ካርቱም ከተቀዳጀች ወዲህ፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2013 ሰላም የነበራት ደቡብ ሱዳን፣ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትላቸው በነበሩት ዶ/ር ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች፣ ወደ ሕዝቡ ብሎም የመከላከያ ኃይሉ ድረስ ዘልቆ አገሪቷን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከከተታት ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ሁለቱን መሪዎች ለማደራደር፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግና በአገሪቷ ሰላም ለማስፈን በኢትዮጵያ በኋላም በኬንያና በኢጋድ አደራዳሪነት የተሠሩ ሥራዎች ከሽፈዋል፡፡

  ዲንካ እና ኑዌር በተሰኙ ብሔሮች ፕሬዚዳንቱ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ጦሩና ሌሎች ተከፋፍለው የሚያደርጉትን ጦርነት እንዲያቆሙ፣ በነሐሴ 2007 ዓ.ም. ፕሬዚዳንቱና ምክትሉ የሰላም ስምምነት ያደረጉ ቢሆንም፣ ይህም አልዘለቀም፡፡ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በ2008 ዓ.ም. አጋማሽ ጁባ ገብተው ከሳልቫ ኪር ጋር ሥራ የጀመሩት ማቻር፣ በሰኔ 2008 ዓ.ም. በጁባ በተቀሰቀሰ ግጭት አገሪቷን ለቀው ካርቱም ሲገቡ፣ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የሁለቱ ስምምነትና የአገሪቷ የወደፊት የሰላም ተስፋ ተመናምኗል፡፡

  ይልቁንም በካርቱም ሕክምና ሲያደርጉ ሰንብተዋል የተባሉት ማቻር፣ የሳልቫ ኪርን መንግሥት በመኮነን ሕዝቡ በሳልቫ ኪር መንግሥት ላይ ጦሩን እንዲያነሳ፣ ካሉበት ካርቱም ሆነው ጥሪ ማስተላለፋቸው በአገሪቷ የነበረውን የሰላም ጭላንጭል አጥፍቶ፣ ችግሮችን በጦር ብቻ ወደ መፍታት አሸጋግሯል፡፡ ይህም ለደቡብ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው አገሮች በተለይም ቀድሞውንም በደቡብ ሱዳን ስደተኞች ለተጨናነቀችው ኢትዮጵያ ፈተና ነው፡፡

  የተደረጉ ጥረቶች ሁሉ መክነው አገሪቷ አሁን ያለችበት ሁኔታ ከፍቷል፡፡ የደቡብ ሱዳን ሰላም ካልተረጋገጠም ቀጣናውን በኢኮኖሚ በማስተሳሰር፣ የአካባቢውን አገሮች መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ለማሸጋገር የተጀመረው ሥራ ቀርቶ መደበኛ ሕይወት አሥጊ ሆኗል፡፡ ለዚህ በሶማሊያም ሰላም ማስፈን ሌላው ፈተና ነው፡፡

  የደቡብ ሱዳን የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአማፅያን መሪ ዶ/ር ማቻር በደቡብ ሱዳን መንግሥት ላይ አዲስ ጦርነት ያወጁት ባሳለፍነው ሳምንት ማብቂያ መሆኑን፣ ይህም ሁለቱንም ወገኖች ለማግባባት ሲካሄድ የቆየውን ዓለም አቀፍ የሰላም ድርድር ውጤት አልባ እንደሚያደርገው ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡

  ማቻር፤ ‹‹ፋሽስታዊ መንግሥት›› የሚሉትን የፕሬዚዳንት ኪርን ሥርዓት በጦርነት በማስወገድ በምትኩ በመላው አገሪቱ ሰላም፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የጦርነት ጥሪ ሲያቀርቡ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የደቡብ ሱዳን መንግሥት መጥፎ፣ ፀረ ሰላም፣ ለቀጣናውና ለዓለም አቀፉ ሰላምና ፀጥታ አሥጊ መሆኑን መግለጽ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

  የደቡብ ሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይ ማይክል ማኩይ በበኩላቸው ማቻርን ‹‹የጦርነት ሰው›› ሲሉ፣ ያስተላለፉትን የጦርነት አዋጅ ኮንነውታል፡፡ አዲሱንና አስደንጋጩን የጦርነት ጥሪ ገታ አድርገው በፖለቲካው ለመቀጠል ፈቃደኛ ከሆኑ፣ በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው ምርጫ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  ‹‹በማቻር ምክንያት ወደ ሰላም መድረስ ተስኖናል፡፡ ማቻር እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2016 ጁባ በመጣበት ጊዜ ፍላጐቱ ሁሉ በኃይል መምራት ነው፤›› ሲሉም ማኩይ ተናግረዋል፡፡

  ማቻር ካርቱም ከገቡ በኋላ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ታባን ዴንግን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጐ የሾመ ሲሆን፣ ይህም ችግሩን ያወሳስበዋል የሚል ሥጋት አስከትሏል፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ግን የማቻር መሰናበት ለአገሪቱ ሰላም ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሆኖም ጁባ ሰላሟን አላገኘችም፡፡

  በሁለቱም ወገኖች በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሪክ ማቻር ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወደ ጁባ ተመልሰው የምክትል ፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸውን ቢረከቡም፣ ሐምሌ አጋማሽ ላይ ግጭቱ እንደገና በማገርሸቱ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው በአሁኑ ጊዜ ለሕክምና ካርቱም ሱዳን ይገኛሉ፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት የደቡብ ሱዳንን ዜጎች ከእርስ በርስ ጦርነት ለመታደግና የአካባቢውንም ሰላም ለማረጋጋት በማሰብ 4,000 ተጨማሪ የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ሥፍራው ለመላክ ወስኖ ነበር፡፡ ይኼም በሥፍራው የሚገኙትን የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ቁጥር ወደ 17 ሺሕ ከፍ ሊያደርገው ይችል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተጨማሪ ኃይሎችን ለመላክ የተላለፈውን ውሳኔ ፍጹም እንደማይቀበለው በወቅቱ አስታውቋል፡፡

  ከዚህም በተጨማሪ የቅርብ ጎረቤቷ የሆነችው ኡጋንዳ ለሰላም አስከባሪው ኃይል ወታደራዊ አስተዋጽኦ እንደማታደርግ ገልጻለች፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች የስደተኞች ኤጀንሲ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ባለፉት አምስት ሳምንታት ብቻ 82 ሺሕ የሚሆኑ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ድንበር ተሻግረው ወደ ኡጋንዳ ገብተዋል፡፡

  የእርስ በርስ ግጭቱ ከተቀጣጠለበት ጊዜ ጀምሮ 200 ሺሕ ያህል ዜጎች በደቡብ ሱዳን ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች በሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጠለያ ካምፖች ገብተዋል፡፡

  የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ኃይል ያልተቀበለው ውሳኔው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ መርህ ጋር የሚጋጭና የደቡብ ሱዳንን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ስላስገባ መሆኑን ገልጿል፡፡

  ደቡብ ሱዳን ለውሳኔው ተገዥ ካልሆነች የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ሊደረግባት እንደሚችል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ሚስተር ዴቪድ ፕሬስማን ቢናገሩም፣ ደቡብ ሱዳን ለዚህ ቦታ አልሰጠችም፡፡

  ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን በ2003 ዓ.ም. ተቀዳጅታ ወደ እርስ በርስ ግጭት ከገባችው ከ2005 ዓ.ም. ወዲህ 50 ሺሕ የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት፣ ሌሎች ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል፡፡

  የእርስ በርስ ግጭቱ የተከሰተው ፕሬዚዳንቱ ሳልቫ ኪር ምክትላቸውን ሪክ ማቻር የመንግሥት ግልበጣ ዶልቶብኛል በማለታቸው ሲሆን፣ በግጭቱም ዜጎች ሰለባ ሆነዋል፡፡

  የአማፂያኑ መሪ ያቀረቡት የጦርነት ጥሪ ተግባር ላይ ከዋለ የእርስ በርስ ግጭቱ እንደማያባራ፣ ይህም የቀጣናውን ሰላም እንደሚያደፈርሰው የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል፡፡

  የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ኬንያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱም ወገኖች ለስምምነቱ ተገዥ እንዲሆኑ፣ አለበለዚያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡     

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ‹‹ምዕራባውያን አፍሪካውያንን ለማዘዝ የሚያሳዩት ፍላጎት ተቀባይነት የለውም››

  የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንደር የአሜሪካ የውጭ...

  ዕውቅና ቤት ለቤት ልብስ ለሚያጥቡ ሴቶች

  ሴቶች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን፣ መላው...

  በኮሎምቢያ ካሊ በወጣት አትሌቶች በሜዳሊያ የተንበሸበሸው ብሔራዊ ቡድን ዓርብ አቀባበል ይደረግለታል

  በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች...

  የፌዴሬሽኑ ቀጣይ ምርጫና የሊጉ አክሲዮን ማኅበር መግለጫ

  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ...