Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየከተማ አስተዳደሩ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ባለዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ ካርታ ማምከኑ ተቃውሞ አስነሳ

  የከተማ አስተዳደሩ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ባለዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ ካርታ ማምከኑ ተቃውሞ አስነሳ

  ቀን:

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በልደታ ክፍለ ከተማ ልደታ መልሶ ማልማት ቦታ ላይ፣ ዊዝደም የገበያ ማዕከል አክሲዮን ማኅበር የሚያስገነባውን በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ባለዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲመክን ማድረጉ ተቃውሞ አስነሳ፡፡

  የሊዝ ውሉን በማቋረጥ የይዞታ ማረጋገጫው ካርታ እንዲፈርስ የተደረገው በልደታ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ቀበሌ 07/14 የሚገኘውና በመልሶ ማልማት ተነሺ የነበሩ የቀበሌና የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲና የንግድ ቤቶችን ተከራይተው ይሠሩ የነበሩ 55 ግለሰቦች፣ በአክሲዮን ማኅበር ተደራጅተው በሊዝ ውል በወሰዱት 1,425 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ ያለ ሕንፃ መሆኑን የማኅበሩ አባላት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

  የአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዊዝደም የገበያ ማዕከል እያስገነባው የሚገኘው ሕንፃ እንዲመክን ያደረገው በካቢኔ ውሳኔ፣ በአስተዳደሩ ፍትሕ ቢሮ አስተያየትና በከንቲባው ጽሕፈት ቤት ውሳኔ አራት ግለሰቦች (በመልሶ ማልማት ተነሺ ናቸው የተባሉ) በአክሲዮን ማኅበሩ እንዲካተቱ ያስተላለፉትን ውሳኔ፣ አክሲዮን ማኅበሩ ተግባራዊ ባለማድረጉ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ገልጿል፡፡

  ቢሮው የገለጸውን ወይም አስተላልፌያለሁ የሚለውን ‹‹አራቱ ግለሰቦች በአክሲዮን ማኅበሩ ውስጥ መካተት አለባቸው የሚል ውሳኔ›› የሚቃወሙት የአክሲዮን ማኅበሩ ባለድርሻዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአስተዳደሩ የመሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን ጋር ሚያዝያ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ለ50 ዓመታት የሚቆይ የሊዝ ውል ፈጽመዋል፡፡ ቅድሚያ የሊዝ ግምት በመክፈል ቀሪ የሊዝ ዋጋ በ20 ዓመታት ለመክፈልም ተስማምተዋል፡፡ በወቅቱ የማኅበሩ አባላት 54 የነበሩ ሲሆን፣ በአክሲዮን ማኅበሩ መካተት እንዳለባቸው በመግለጽ ከአስተዳደሩ ጋር የሚከራከሩ አንድ አባል ስለነበሩ፣ አስተዳደሩ የጠየቃቸውን መሥፈርት የሚያሟሉ ከሆነ በማኅበሩ እንዲካተቱ የሚል በውሉ ላይ ተጠቅሶ ስለነበር ተከራካሪው ግለሰብ አሟልተው በመቅረባቸው መካተታቸውን አስረድተዋል፡፡ ቁጥራቸውም 55 መድረሱን አክለዋል፡፡

  አክሲዮን ማኅበሩ ውሉን ፈጽሞና ቦታውን ተረክቦ ወደ ግንባታ መግባቱን የሚናገሩት የማኅበሩ አባላት፣ ሕንፃው መሠረቱ ወጥቶና የፎቆች ግንባታ በመካሄድ ላይ እያለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጥር 26 ቀን 2005 ዓ.ም. አራት ግለሰቦች በመልሶ ማልማቱ የተነሱ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ በአክሲዮን ማኅበሩ ውስጥ እንዲካተቱ ለልደታ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ማሳወቁን ተናግረዋል፡፡

  የክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት የሰጠውን ምላሽ የማኅበሩ አባላት ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በአክሲዮን ሊካተቱ የሚችሉት ግለሰቦች የተከራዩትን የመንግሥት ቤት በሕጋዊ መንገድ በስማቸው የተዋዋሉና የተከራዩ መሆን አለባቸው፡፡ ግለሰቦቹ ከቀበሌውም ሆነ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በቂ ማስረጃ (ኦርጂናልና ኮፒ) ባይኖራቸውም እንኳን፣ በአክሲዮኑ ይካተቱ የሚለው ከመመርያ አንፃር ሲታይ ለአሠራር ክፍተት የሚፈጥር ነው በማለት ካቢኔው ውሳኔውን በድጋሚ እንዲመለከተው ጽሕፈት ቤቱ ምላሽ መስጠቱን አስረድተዋል፡፡

  የክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የካቢኔው ውሳኔ ከመመርያ ውጪ መሆኑንና ምንም ሕጋዊ ማስረጃ የሌላቸውን ግለሰቦች እንደማያካትት ገልጾ ለቢሮው ምላሽ የሰጠ ቢሆንም፣ የአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይለ፣ የክፍለ ከተማው ጽሕፈት ቤት የታዘዘውን እንዲፈጽም የማሳሰቢያ ደብዳቤ መጻፋቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

  የቢሮ ኃላፊው ጽሕፈት ቤቱ አራቱን ግለሰቦች በአክሲዮኑ ውስጥ እንዲያካትት የትዕዛዝ ደብዳቤ የጻፉት፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው፣ የፍትሕ ቢሮው በካቢኔው ውሳኔ ላይ የሰጠውን አስተያየት መሠረት አድርጐ ቢሮው እንዲያስፈጽም የትዕዛዝ ደብዳቤ ከጻፉ በኋላ መሆኑን፣ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ይገልጻሉ፡፡ የፍትሕ ቢሮው በሰጠው የሕግ አስተያየት፣ በማኅበሩና በአስተዳደሩ መካከል የተፈጸመው ውል ሕግ መሆኑን ጠቅሶ፣ ማኅበሩ ግዴታውን በውሉ መሠረት የማይፈጽም ከሆነ የሊዝ ውሉ ሊቋረጥና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው መክኖ የመንግሥት መሬት እንዲመለስ ማድረግ የሚችል መሆኑን ለካቢኔው አስተያየቱን መግለጹን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

  የፍትሕ ቢሮው የሰጠውን አስተያየት ተከትሎ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የማኅበሩ የሊዝ ውልና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከኅዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲቋረጥና እንዲመክን ያደረገ ቢሆንም፣ የአስተዳደሩ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ድርጊቱን ተቃውሟል፡፡

  የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አልይ በጻፉት የመቃወሚያ ደብዳቤ ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ተጨማሪ ሰዎችን ባለማካተቱ በተፈጠረ አለመግባባት፣ በውል ተቀባይ (ማኅበሩ) እና በውል ሰጪ (ልደታ ክፍለ ከተማ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት)፣ እንዲሁም ሥልጣን ባላቸው በየደረጃው በሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ክርክር ተደርጐበት ፍርድ አለመሰጠቱን ሥራ አስኪያጁ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡ መሠረታዊ ክፍተት እያለ የሕግ አስተያየትን (ፍትሕ ቢሮ በሰጠው) ብቻ መነሻ በማድረግ የሊዝ ውልን ማቋረጥና የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታን ማምከን ተገቢ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጣቸውን አስገዳጅ ውሳኔዎችንም ያለመመልከት ችግር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78(1) እና 79 (1 እና 4) ሥር የተረጋገጠውን ነፃ ፍርድ ቤት መኖርንና የዳኝነትን ሥልጣን ትርጉም አልባ የሚያደርግ ዕርምጃ በቢሮው መወሰዱንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

  ውሳኔው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 የተረጋገጠውን የዜጐችን ፍትሕ የማግኘት መብት፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 (1 እና 2) መሠረት የንብረት ባለቤት የመሆንን ዋጋ የሚያሳጣ መሆኑን አስረድተው፣ ቢሮው የሊዝ ውል ለማቋረጥም ሆነ የይዞታ ማረጋገጫን ካርታ ለማምከን ሕጋዊም ሆነ የአሠራር መሠረት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡ ድርጊቱ የማይተካ ከፍተኛ የፍትሐ ብሔር ኃላፊነትና በግለሰብ ደረጃም ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን አቶ ጀማል አስገንዝበዋል፡፡

  የማኅበሩ አባላት እንደሚናገሩት፣ ቅድሚያ የሊዝ ክፍያ የፈጸሙት ልጆቻቸውን ዓረብ አገር ልከው ነው፡፡ ሕንፃው ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት የቻሉትን ሁሉ እያደረጉ የቀጠሉ ቢሆንም፣ ሕንፃው ሰባተኛ ፎቅ ላይ ሲደርስ ግንባታው ታግዶ ካርታው እንዲመክን መደረጉ እንዳስደነገጣቸውና እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ በሕጋዊ መንገድ የተደራጀና አስፈላጊውን መሥፈርት አሟልቶ ወደ ሥራ የገባን ማኅበር፣ ያለምንም ምክንያት በሕገወጥ መንገድ ግለሰቦችን በግድ ካላካተታችሁ ተብሎ ሕጋዊ ሰነድ ማምከን ሕገወጥነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በነጋ በጠባ ልማትን የሚሰብክ መንግሥት እንደዚህ ያለ ሕዝብንና አገርን የሚጐዳ ተግባር ይፈጽማል የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚናገሩት የማኅበሩ አባላት፣ ድርጊቱን እየፈጸሙ የሚገኙት ሕዝብን በአግባቡና በሕጉ መሠረት ያገለግላሉ ተብሎ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

  ግንባታው ሰባተኛ ፎቅ ላይ ሲደርስ ውል በማቋረጥና ካርታ በማምከን የሕንፃው መሠረት በውኃ እንዲሞላ በመደረጉ፣ በአጭር ጊዜ ሕንፃውን ሊያፈርሰው እንደሚችል ጠቁመው፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስተካክልላቸውና ችግሩን በፈጠሩትም ላይ ዕርምጃ ወስዶ ወደ ግንባታቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል፡፡    

         

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...