Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የመንገዶች ባለሥልጣንና የየመኑ ተቋራጭ ፍጥጫ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በ2008 በጀት ዓመት ግንባታቸው አልቆ ለትራፊክ ክፍት ይሆናሉ ከተባሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በደቡብ ክልል፣ ከጩኮ – ይርጋጨፌ የሚዘልቀው መንገድ ይገኝበታል፡፡

  60 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና በ786.7 ሚሊዮን ብር በጀት እንዲገነባ ውለታ የተገባለት የጩኮ – ይርጋጨፌ መንገድ ፕሮጀክት፣ እንደታሰበው የተያዘለትን ጊዜ ጠብቆ ሊጠናቀቅ ግን አልቻለም፡፡ የግንባታ ሥራውን ለማከናወን ጨረታውን ማሸነፉ ከተረጋገጠው የየመኑ ሐዋክ ኢንተርናሽናል ፋይናንስና ኮንስትራክሽን ሊሚትድ የተባለ ኩባንያ ጋር የኮንትራት ውል የተፈረመው በሚያዝያ ወር 2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኮንትራት ውሉ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ በሚሰላ የጊዜ ገደብ መሠረት፣ በሦስት ዓመት ውስጥ መጠናቀቅ የነበረበት ይህ የመንገድ ግንባታ፣ ሥራው ተጠናቅቆ ርክክብ ይፈፀምበታል በተባለበት ሦስተኛ ዓመት ላይ ግን ከጠቅላላው ሥራ 60 በመቶ አካባቢ ብቻ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ በዚሁ ወቅት ነበር የግንባታ ሥራው እንደቆመ ይፋ መውጣት የጀመረው፡፡

  በሐምሌ ወር 2008 አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ገልጾ እንደነበረው፣ ከኮንትራክተሩ ጋር የነበረው ውል ስለመቋረጡና የተቋረጠውን ፕሮጀክት ለማስቀጠል አዲስ ኮንትራክተር እንደሚቀጠር የሚጠቁም ነው፡፡ ከየመኑ ኩባንያ ጋር የነበረው ውለታ ሊቋረጥ የቻለበት ዋነኛው ምክንያት በኮንትራት ውሉ መሠረት ግንባታውን ባለማከናወኑ የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ ባለሥልጣኑ አስታውቆ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ግን ከዚህ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በኮንትራክተሩ ላይ ተወሰደ የተባለው ዕርምጃና ኮንትራክተሩ ሥራ እንዲያቋርጥ የተደረገበት ምክንያት እንዲሁም በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ባለሥልጣኑ ያሰራጨው መረጃ ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑን ሐዋክ ለሪፖርተር የላከው መረጃ ያስረዳል፡፡ እንደ ኮንትራክተሩ ማብራሪያ ከሆነ፣ ለሥራው መስተጓጐል ዋናው ተጠያቂ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ነው፡፡

  በዚህ አኳኋን በፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት ከሁለቱ ወገኖች የሚሰነዘረው እሰጣ ገባ፣ ጉዳዩን አነጋጋሪ እያደረገው መጥቷል፡፡ የመንገድ ግንባታ ውሉ የተቋረጠበትና የፕሮጀክቱ ሥራ የተስተጓጐለበት ምክንያት በሁለቱም ወገኖች የተለያየ መልክ እየተሰጠው በመገለጽ ላይ ነው፡ 

  አጋጅ ታጋጅ

  በፕሮጀክቱ መስተጓጐል ዙሪያ ኮንትራክተሩ ሊታገድ የቻለው በአግባቡ ሥራውን ማከናወን ባለመቻሉ ነው ተብሏል፡፡ ኮንትራክተሩ መባረሩን ባለሥልጣኑ ሲያስታውቅ፣  ስለፕሮጀክት ግንባታው መቋረጥና ስለኮንትራክተሩ መባረር የተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያም ለፕሮጀክቱ መጓተት የኮንትራክተሩ ጥፋት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ግንባታውን ጨርሶ እንዲያስረክብ የተደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ የተወሰደ ዕርምጃ ነው ተብሏል፡፡ ኮንትራክተሩ በበኩሉ የመንገድ ግንባታ ሥራው የተቋረጠው ባለሥልጣኑ በኮንትራት ውሉ ላይ በተቀመጠው መሠረት ግዴታና ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ምክንያት መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻል፡፡ ‹‹ሥራዬን በአግባቡ ለመወጣት ከባለሥልጣኑ ሊደረግልኝ ይገባ የነበረው እገዛ ስላልተደረገልኝ ነው፤›› በማለት ለሥራው መስተጓጐል ባለሥልጣኑን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡

  ኮንትራክተሩ አልተፈጸሙም የሚላቸው ጉዳዮች

  የመንገድ ፕሮጀክቱ ውል በባለሥልጣኑ ተጥሶ ሥራው እንዲታጐል አድርጓል የሚለው የየመኑ ኮንትራክተር፣ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሠራ እንቅፋቶች ነበሩ ያላቸውን ጉዳዮች ለሪፖርተር በላከው ደብዳቤ ጠቅሷል፡፡ በተለይም ባለሥልጣኑ ቀድም ብሎ ሊከውናቸው ይገባው ነበር የተባሉ ሥራዎች ባለመሠራታቸው የተፈጠረ ችግር መሆኑንም ገልጿል፡፡ ከወሰን ማስከበር ጋር በተገናኘ ለሥራው እንቅፋት የሆኑትና ባለሥልጣኑ ካሣ ከፍሎባቸው ያልተነሡ እንደ ኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮች፣ የውኃ ቧንቧዎች፣ መሬት ሥር የተቀበሩ ገመዶች፣ የድንጋይ አጥሮች፣ የሸንኮራ ማሳዎች፣ ዛፎችና ሌሎችም ከመንገድ ግንባታ ማካሄጃው አካባቢ ባለመነሳታቸው ምክንያት ሥራው ሊታጐልበት እንደቻለ ኮንትራክተሩ አመልክቷል፡፡

   ከዚህ በተጨማሪ ለግንባታ ሥራው መጓተት ምክንያት ነበር ብሎ ኮንትራክተሩ የጠቀሰው ሌላው ችግር ተፈቅዶለት መረከብ የነበረበት የድንጋይ ማውጫ (ካባ) ሥፍራዎችን ለማስረከብ ባለሥልጣኑ ማዘግየቱ ነው፡፡ የካባ ቦታው ርክክብ የዘገየውም ድንጋይ ማውጫ ባለበት አካባቢ የሚኖሩ የመሬት ባለይዞታዎች ካሣ ሊከፈላቸው ባለመቻሉ ነው፡፡ የካሣ ክፍያውን ጥያቄ በወቅቱ ለመፍታት ባለሥልጣኑ ጥረት ባለማድረጉና በቶሎ እልባት እንዲሰጥበት ኮንትራክተሩ በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ለፕሮጀክቱ መጓተት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተቋራጩ አጣቅሷል፡፡ የካባ ቦታውን ካሣ ከፍሎ ባለሥልጣኑ ሊያስረክበኝ አልቻለም በሚለው የኮንትራክተሩ ክስ ግን ባለሥልጣኑ አይስማማም፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንደገለጹት፣ ኮንትራክተሩ ሁለት የካባ ቦታዎችን በወቅቱ ተረክቧል፡፡

  በካባ ሥፍራው ለመጠቀም ወይም የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ወደ ፕሮጀክቱ ሥፍራ ለመውሰድ በአካባቢው የሚገኘውን የገጠር መንገድ ለመጠቀም ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሳምሶን፣ ካባው የሚገኝበት ወረዳ አስተዳደር መንገዱ ይበላሽብኛል ብሎ ጥያቄ ማንሳቱን አስታውሰዋል፡፡ የወረዳውን ሥጋት በመንተራስ ባለሥልጣኑ በጉዳዩ ገብቶ መንገዱን ኮንትራክተሩ ከተጠቀመበት በኋላ እንዲጠግንና ወረዳውም እንዲፈቅድ ስምምነት ተደርሶ ነበር ብለዋል፡፡ ሆኖም ኮንትራክተሩ ሥራውን በማቋረጡ እንጂ ለድንጋይ ማውጫ ወይም ለግንባታ ግብዓት አቅርቦት ጥያቄው አወንታዊ መልስ ተሰጥቶ ነበር ይላሉ፡፡

  ‹‹አንድ ኮንትራክተር መንገድ የሚገነባበት ቦታ ለካባ ወይም ለግንባታ የሚሆኑ ተቆፋሪ መሬቶችና የግንባታ ግብዓቶችን የሚያገኝበት ቦታዎችን ከመረጠ በኋላ ተከልሎ ይሰጠዋል፡፡ ኮንትራክተሩ የወሰን ማስከበር ችግርን እንደሰበብ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም፤›› በማለት ባለሥልጣኑ የቀረበበትን ቅሬታ ውድቅ ያደርገዋል፡፡ ንብረቶች ባይነሱ እንኳ ግንባታውን ለማካሄድ በሚያስችሉ ቦታዎች ላይ ሊሠራ የሚችልበት ሰፊ ዕድል እንደነበረው አቶ ሳምሶን ይገልጻሉ፡፡

  ‹‹ኮንትራክተሩ ይህንን ዕድል ሊጠቀምበት አልቻለም፡፡ የራሱን ውስጣዊ ችግር ውጫዊ ለማድረግ እየሞከረም ነው፤›› በማለት ይነቅፉታል፡፡

  ውሉ እንደምን ተቋረጠ

  በኮንትራት ውሉ መቋረጥ ዙሪያ ከሁለቱም ወገኖች የተሰጠው ምክንያት የተለያየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለኮንትራክተሩ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በኋላ የተወሰደ ዕርምጃ ነው ቢልም ኮንትራክተሩ ግን በዚህ አይስማማም፡፡ ለሥራ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በገባበት ወቅት እንኳ የግንባታ ሥራው 45 በመቶ ገደማ ተዳርሶ፣ ለአጠቃላይ ግንባታው የተሰጠው የሦስት ዓመት ጊዜ ሲቃረብም ግንባታውን ለማጠናቀቅ የጊዜ ማራዘሚያ ፈቃድ እንዲሰጠው መጠየቁን ሐዋክ ይገልጻል፡፡ ሥራውን ለማጠናቀቅ እንቅፋት የነበሩ ጉዳዮችን በመጥቀስ የጊዜ ማራዘሚያ ያስፈልገኛል በማለት ያቀረበውን ጥያቄ ባሥልጣኑ ይሁንታ ሳይሰጠው በመቅረቱ ኮንትራክተሩ መታገስ የማይችልበት ደረጃ በመድረሱ፣ በኮንትራት ውሉ መሠረት ቀድሞ ውሉን ስለመቋረጡ የሚገልጽ ደብዳቤ ኮንትራክተሩ ያስገባ ስለመሆኑም ያመለክታል፡፡

  ለግንባታው እንቅፋት የሆኑት ጉዳዮች አሳማኝና ተቋራጩ የውል ግዴታውን እንዳይፈጽም ያስገደዱት በመሆናቸው፣ መጋቢት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. የውል ማቋረጥ ማሳወቂያ ኮንትራክተሩ ለባለሥልጣኑ መስጠቱን፣ ከባለሥልጣኑም በፊት ተቋራጩ ውሉን ማቋረጡን ይገልጻል፡፡ ይህ ዕርምጃውም ከሚያዝያ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በውሉ ድንጋጌዎች መሠረት የተፈጸመ ነው ይላል፡፡

  ባለሥልጣኑ የመንገድ ግንባታ ውሉ የተቋረጠበት ምክንያት ተቀባይነት የሌለው አድርጐ በመቁጠሩ፣ የተፈጠረ ግጭት መሆኑንም ተቋራጩ ይገልጻል፡፡ የፕሮጀክቱ ሥራ ከቆመና ፕሮጀክቱም ከተቋረጠ በኋላ ባለሥልጣኑ በተቋረጠው ውል ላይ ባለሥልጣኑ የማቋረጫ ማስታወቂያ ለተቋራጭ ለመስጠት የተወሰነ መሆኑንም በመግለጽ፣ ኮንትራክተሩ ይህ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሎ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲታይ መደረጉንም ይገልጻል፡፡

  ለሁለቱም ተዋዋዮች ትክክለኛው የማጠናቀቂያ ጊዜና ውጤታማ የሆነ የሥራ መርሐ ግብርን ለመገምገም እንዲችሉ የሚያደርጋቸው አስገዳጅ ግዴታ ነበር የሚለውንና ኮንትራክተሩ ስለውሉ መቋረጥ ከባለሥልጣኑ የተሰጠውን ምክንያት አልተቀበለውም፡፡

  ኮንትራክተሩ ለግንባታ ሥራው እክል ሆኑብኝ የሚላቸው ችግሮች ሊፈጠሩ የቻሉት ባለሥልጣኑ መሥራት ያለበትን ሥራ ባለመሥራቱ ነው፤ በዚህም የተነሳ  ለደረሰብኝ ያልተገባ ወጪ (ኪሣራ) ማካካሻ ይከፈለኝ በማለት ጥያቄ አቅርቦ እንደነበርም አስታውሷል፡፡ ከዚህ ጥያቄው ጐን ለጐን የጊዜ ማራዘሚያ እንዲሰጠው ያቀረበው ጥያቄም በባለሥልጣኑ ውድቅ እንደተደረገበት ገልጿል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖና ችግሩንም እያወቀ ባለሥልጣኑ ኮንትራክተሩን ተጠያቂ ማድረግ አልነበረበትም የሚለው ሐዋክ፣ ከባለሥልጣኑ ሥራውን ለማጠናቀቅ እገዛ ተደርጐለታል የሚለውንም ሐሳብ የሌለና ያልነበረ ነው ይለዋል፡፡

  ባለሥልጣኑ ኮንትራክተሩ ውል አቋርጫለሁ በማለት ማመልከቻቸውን ቀድሞ ማስገባቱን አላስተባበለም፡፡ ‹‹ውል አቋርጠናል የሚለው ማመልከቻቸው ግን ሕጋዊ አካሄዱን ተከትሎ የቀረበ ባለመሆኑ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሥራውን እንዲሠራ ዕድሎች ተሰጥተውት ሳለ በዕድሉ ባለመጠቀሙ ባለሥልጣኑ ሐምሌ 2008 ዓ.ም. የኮንትራት ውሉን ቅደም ተከተል መሠረት አድርጐ ከኮንትራክተሩ ጋር የነበረው ውለታ እንዲቋረጥ አድርጓል፤›› ይላል፡፡

  ተቋራጩ ውል ወደ ማቋረጥ ከመሄዱ በፊት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠውና ተጨማሪ ክፍያ እንዲለቀቅለት የሚጠይቅበት አሠራር አለ የሚሉት አቶ ሳምሶን፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ሥራውን እየሠራ ወደ ግልግል አካል መሄድ ይችል እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ኮንትራክተሩ ግን ይህንን ሒደት ሳይጠብቅ ውል አቋርጫለሁ ማለቱ ባለሥልጣኑንም ሆነ አማካሪ ድርጅቱን አላሳመነም፡፡ ይህም ሆኖ ባለሥልጣኑ የጊዜ ማራዘሚያና የተጨማሪ ክፍያውን ጉዳይ እየተመለከተ ባለበት ወቅት ኮንትራክተሩ ውሌን አቋርጫለሁ በማለቱ ሥራውን ለመሥራት እንዳልፈለገ ስለሚያመለክት፣ ዕርምጃው ሊወሰድበት ችሏል እንጂ አቅርቦ የነበረው ጥያቄ ምላሽ ተነፍጎት አይደለም በማለት አቶ ሳምሶን ስለተፈጠረው አለመግባባት አብራርተዋል፡፡  

  የግንባታው መስተጓጎል ያስከተለው ከፍተኛ ወጪ

  እንዲህ ባለው ምክንያት የመንገድ ግንባታዎች ሲቋረጡና ሥራውን ከቆመበት ለማስቀጠል የሚወስደው ጊዜና ገንዘብ ቀላል እንዳልሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ግንባታው ለሌላ ኮንትራክተር ሲሰጥ ቀደም ብሎ ለፕሮጀክቱ ከተመደበው ወጪ በላይ መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡ ባለሥልጣኑም በዚህ ይስማማል፡፡ የየመኑ ኮንትራክተርም ይህንን ሐሳብ ይቀበላል፡፡ ነገር ግን እነርሱ ተረክበውት በነበረው ፕሮጀክት ላይ ባለሥልጣኑ ግዴታውን ቢፈጽምና ኃላፊነቱን በመወጣት ተገቢውን የጊዜ ማራዘሚያ ሰጥቶ ቢሆን ኑሮ፣ ኮንትራክተሩ ሥራውን ስለሚቀጥል ቀሪውን የመንገድ ሥራ ለሌላ ኮንትራክተር መስጠት የሚያስከትለውን ከፍተኛ ወጪ ወይም የዋጋ ጭማሪ ላይፈጠር ይችል እንደነበር በመጥቀስ ባለሥልጣኑን ይኮንናል፡፡

  ቀጣዩ ዕርምጃና አደራዳሪው ቦርድ

  እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ገለጻ የየመኑ ኮንትራክተር ውል ማቋረጡን ካሳወቀ በኋላ ቀሪውን ወይም ያልተጠናቀቀውን መንገድ ለማስጨረስ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ከተቋረጠ ከአምስት ወራት በላይ የሆነውንና በጅምር የቀረውን መንገድ ለማጠናቀቅ ባለሥልጣኑ የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ የደረሰበት ድምዳሜ የዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በተሠሩ መንገዶች የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸውን ኮንትራክተሮች ጋብዞ የተሻለ ዋጋ ለሚያቀርበው ሥራውን መስጠት ነው፡፡ ይህንንም ሥራ እየሠራ ነው፡፡ በቅርቡም ጨረታው ይወጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

  ከዚህ ሒደት ጐን ለጐን ግን በባለሥልጣኑና በየመኑ ኮንትራክተር መካከል የተፈጠረውን ያለመግባባት ለመዳኘት አደራዳሪ ቦርድ ተቋቁሞ ጉዳዩ እየታየ ነው፡፡ የድርድሩ ውጤት ምን እንደሚሆን ባይታወቅም ባለሥልጣኑ ሥራውን ለሌላ ኮንትራክተር እሰጣለሁ ማለቱ በየመኑ ኮንትራክተር ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ የበርዱ ውሳኔ መታወቅ አለበት የሚል አቋም ይዟል፡፡

  በየመኑ ኩባንያ የቦርዱን ውሳኔ እጠብቃለሁ ቢልም፣  የድርድር ውጤቱ ገና ሳይገለጽ ከደንብ ውጭ በመሆን ባለሥልጣኑ የባንክ ዋስትናውን በመጠየቅና ማምረቻና የግንባታ መሣሪያዎቹን ከፕሮጀክት ሥፍራው እንዲያነሳ የማድረግ ዕርምጃ መውሰዱን ኮንትራክተሩ ገልጿል፡፡         

  ባለሥልጣኑ ግን አንድ የሥራ ተቋራጭ ውሉ ሲቋረጥ ሥራው የተቋረጠበት መንገድ እስኪረጋገጥ ንብረቱን ማንቀሳቀስ እንደማይችል በኮንትራት ውሉ ላይ በግልጽ ተቀምጧል በማለት፣ የወሰደው ዕርምጃ ሕጋዊ እንደሆነ ገልጾ ተከራክሯል፡፡ ‹‹እንዲያውም እንዲህ ባለው መንገድ የተቋረጠ ውል ሲኖር በግንባታ ሥፍራው ላይ የሚገኙ የቀድሞው ኮንትራክተር ንብረቶችን አዲሱ ኮንትራክተር እንዲጠቀምባቸው የሚደረግበት አሠራር አለ›፤› ይላል፡፡ ስለዚህ ከኮንትራት ውጭ የተፈጸመ ነገር ስላልሆነ የግልግል ቦርዱ እስኪወስን ንብረቱ ይያዛል በማለት ባለሥልጣኑ አቋሙን አጽንቷል፡፡

  ከሐዋክ ክፍያ የሚጠብቁ ድርጅቶች

  የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ መስተጓጐል ከኮንትራክተሩና ከባለሥልጣኑ ውጭ ያሉትንም አካላት የነካካ ነበር፡፡ የግንባታ ሥራው መቆሙ ከታወቀ በኋላ ለኮንትራክተሩ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችና መገልገያዎችን ያከራዩ አካላት ሊከፈለን የሚገባ  ዕዳ ተቋራጩ ላይ አለን ብለዋል፡፡ ሠራተኞችም ኮንትራክተሩ ክፍያችንን አልከፈለም፣ የላባችንን ዋጋ መና አስቀርቷል በማለት ጥያቄ አንስተውበታል፡፡

  ኮንትራክተሩ ግን የኪራይም ዕዳም ሆነ ደመወዝ ሳልከፍል አልቀረሁም ወይም አላዘገየሁም ይላል፡፡ ሁሉም አገልግሎት አቅራቢዎች፣ ተቀጣሪዎችና አከራዮች በሐዋክ አማካይነት እንደሚገባቸው ተከፍሏቸዋል በማለት ተከራክሯል፡፡ ሆኖም ለአገልግሎት አቅራቢዎች የሚፈጸሙ የቅርብ ጊዜ ክፍያዎች ባለሥልጣኑ ከየካቲት 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የሐዋክን ደረሰኞችና መጠየቂያዎች ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ አልተከፈሉም ብሏል፡፡

  በዚህ ፕሮጀክት ዙሪያ ከሁለቱም ወገኖች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ምላሽ የሚሹ ናቸው፡፡ ለዚህም ሲባል ጉዳዩን በድርድር ለመቋጨት የያዘው የግልግል ቦርድ ውሳኔ ይጠበቃል፡፡ ባለሥልጣኑና ተቋራጩ ግን ችግሩን አንዱ በሌላው እያላከኩ የመንገድ ሥራው ለወራት ተቋርጦ ሕዝብ እየተቸገረ ይገኛል፡፡   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች