Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  በብርድ ላይ ናፍቆት?

  እነሆ ጉዞ! ከሜክሲኮ ወደ ፒያሳ። ማልዶ የጀመረው ግርግር ጨለማ በዋጠው ጎዳና ሊጠናቀቅ የጥቂት ሰዓታት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። ብርዱ ከታክሲ አለመገኘት ጋር ሲደመር ሆድን ባር ባር ይላል። ብሶት ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን ስለታመነ ይመስላል፣ በዚያ ግርግር የሚሰማው ጨዋታና ስላቅ ብሎም የትዕይንቱ መብዛት አንዳች አስደሳች ስሜት ያጭራል። ቆነጃጅት ንፋስን ከነመፈጠሩ በዘነጋ አለባበሳቸው በቅዝቃዜ እየተርገፈገፉ ይንቀጠቀጣሉ። ታክሲ እስኪመጣ የፍቅር አጋር ማደን የጀመሩ ወንዶች፣ ‘የሰው ልጅ መቼም ልብስ፣ ምግብ መጠለያ ግድ ይለዋል ብለሽ እንደምታምኝ አልጠራጠርም፣ ተሳሳትኩ?’ እያሉ ይጠጋጋሉ። ድፍረት ከልባቸው ሞልቶ በዓይናቸው የፈሰሰ ዓይናውጣዎችን እያየ ጎልማሳው ይስቃል፣ የፈራው ትምህርት ይወስዳል። ‹‹አልተሳሳትክም›› ትለዋለች አንዷ ስለሦስቱ መሠረታዊ ነገሮች የተጠና ቃሉን እንዳነበነበ።

  የመንገድ ጨዋታና ሐሜት መቼ ያልቅና! ‹‹ይኼውልሽ እዚህ አገር የአርባ ቀን ዕድል ሆነና የምትጠጋጊው በቁጠባና በልመና ነው። ቁጠባውም ገንዘብ ሲኖር ልመናውም ሰው ከተገኘ ማለቴ ነው። ያውም ዶላር ጠፍቶ ብርድ? አስቢው እስኪ? ‘ሜሪ ክሪስማስ ብያለሁ’ ግን፤›› እያለ የጨዋታውን ዳር ለማስፋት ይታገላል። ከሁለቱ ማዶ መንገድ ላይ ሳር ቤት ለመሄድ ሰው ታክሲ ይሻማል። ተራ አስከባሪዎች የቤት መኪና እንዲተባበር ይለምናሉ። ብርድና ግርግር ለፕሮፓጋንዳ ያመቻል ይመስላል። አጠገቤ አንድ ወጣት እጅግ በብርድ እየተንዘፈዘፈ፣ ‹‹እኔን የማይገባኝ እኮ ቆዳቸው ከምን የተሠራ ቢሆን ነው እንዲህ የሚለብሱት በዚህ ብርድ?›› እያለ ሲጠይቅ ይሰማኛል። ወደሚያይበት ስመለከት ሦስት ልጃገረዶች በአጭር ቀሚስ ልብስ ይታዩኛል። ትችትና ማጉረምረም፣ ሳቅና ነቆራ፣ ብሶትና ትዕግሥት ማጣት ጥንድ ጥንድ ሆነው የገነኑበት ምሽት!

  ጃጉዋር ታክሲያችንን ገብተን ሞላናት። ብናይ አንሄድም። በሰው ላይ ሰው ይደረባል። ‹‹ሾፌር አይበቃም? እንጓዝ እንጂ!›› መጨረሻ ወንበር ላይ ከተሰየምነው ተሳፋሪዎች አንዱ ተናገረ። ‹‹ይሰማኛል ብለህ ነው የምትደርቀው? ወይስ በሜዳችን የመናገር ነፃነትን እንለማመድ ብለህ ነው?›› ስትለው አጠገቡ የተቀመጠች ጎምላላ ዞሮ ዓይቷት አቀለጠው። ይተዋወቁ ኑሯል። ‹‹አፌ ቁርጥ ይበልልሽ! ባንቺ ቤት አያይዘሽኝ ሞተሻል እ? ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ እንዲህ አፍ የፈታሽልኝ?›› ጎልማሳው ዓይን ዓይኗን እያየ ልጅትን በኃፍረት አንገት አስደፋት። ‹‹ቢናገሩ አፈኛ ዝም ቢሉ ሞኝ! ታዲያ መሀል መስፈሪያ አማራጭ ከሌለ ካለው ላይ አንዱን መምረጥ የለብኝም? ጊዜው እኮ የቴሌግራምም ጭምር ነው። አማራጩን ለቻለበት ቢናገር ምን ገዶህ?›› አለችው። ‹‹አደራ እንዲህ እያልሽ ቆመሽ እንዳትቀሪ። ሰው ዘንድሮ ካገኘው ላይሻል አማራጭ እንዳለው ሁሉ የያዘውን እያቃለለ፣ ምርጫ ምርጫ ሲል ነው መላ ቅጡ የጠፋበት። ደህና ነሽ ግን?›› እያላት ወደ ግል ጨዋታቸው አዘነበሉ።

  ‹‹ኧረ እናንተ ሰዎች ስለጉልበታችሁ እምላክ እንሂድ?›› ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ቆፍጣና ቁጣ ጀመረች። ትዕቢተኛው ወያላችን ብቅ ብሎ ገላምጧት ሲያበቃ፣ ‹‹የት ለመድረስ ነው አሁን አንቺ እንዲህ የምትመናቀሪው? መሬት በነፃ እየጠበቀሽ ነው የተባለች አትመስልም? ላራሹ ለራሱ ብለው ቸብችበውት አልቋል ስልሽ እመኚኝ። ካሬ ሚሊዮን ገብቷል አርፈሽ ቁጭ በይ በሏት…” ብሎን እየተጎማለለ ራቅ አለ። ቆፍጣኒት ለካ ቀላል አይደለችም። (ማጣት ሲያቀለው እንጂ ድሮስ የሰው ቀላል አለው እንዴ?) ወርዳ ሸሚዙን ጨምድዳ ይዛ ካልደበደብኩ አለች። ደህና ተጠጋግቶ የተሟሟቀው ተሳፋሪ ሊገላግል ወረደ። ትርምሱ በገላጋዮች ብርታት ቢበርድም አፍላፊው ሊቆም አልቻለም። ይኼን የታዘበ መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ ‹‹አንቺ አትሻይም ከእሱ? ዝም በይ በቃ!›› ብሎ ተቆጣና፣ ‹‹በጭንቅ የምንሞላት ሆዳችን በየመንገዱ በምንሰረዝረው ቦክስ እየጎደለችማ በምግብ ራስን መቻል አይታሰብም…›› ብሎ በምፀት ፈገግታው ቃኛት። ከእሱ በላይ ያሳቀን ግን ጎልማሳው፣ ‹‹በቀለበት መንገድ ምትክ መንግሥት መቧቀሻ ‘ሪንግ’ ቢያሠራልን ነበር ጥሩ…›› ማለቱ ነው። ፌዴራሉ ያልሰማው ጉድ አሉ ክልሎች!

  - Advertisement -

   አንዱ ባንዱ ተነባብሮ፣ ጢም ብላ ሞልታ በታጨቀችው ታክሲያችን ትንፋሻችን መስታወቶቹ ላይ ጉም ይገነባል። ‹‹ኧረ መስኮት! ቢያንስ መስኮት ይከፈት! የዘመኑ ሰው እኮ ብዙ ነገር እየሳበ አስቸግሯል፤›› ይላል ከወደኋላ በጩኸት። ‹‹አቦ አትጩህብና! ገና ለገና ተቃዋሚ ይነሳብኛል ብለህ በጩኸት ታደነቁረናለህ እንዴ?›› ይመልሳል መሀል መቀመጫ ቡዝዝ ያሉ ዓይኖቹ በመጠጥ መዳከማቸው የሚታወቅበት ሽበታም። መጠጥ የሚያኮላትፈው ልሳኑ ከአዕምሮው ሆኖ እንደማይናገር የተገነዘበው ሁሉም ተሳፋሪ ስለነበር መልስ የሚያቀነባብርለት አልነበረም። እሱ ግን ቀጥሏል። ‹‹ጩኸት አይበቃም እንዴ? አገር ማልማት ውለታ አድርጎት የተቃዋሚ ነገር ባስበረገገው ቁጥር የሚጮህብን አይበቃንም ወይ? መስኮት አይከፈትም ብሎ የሚቃወመኝ ሰው ይኖራል ብለህ ፈርተህ ገና ለገና ምንድነው እንዲህ ሰው ማደንቆር?›› እያለ ሲናገር አባባሉ ከማበሰጫት ይልቅ ፈገግ ያሰኛል። ‹‹አዲስ ነገር ፈርተን፣ አዲስ ሐሳብ ፈርተን መጨረሻችን ምን እንደሚሆን የሚነግረን ቢገኝ እንዲያው?›› ቀጥሏል ሽበታሙ በሞቅታ። ‘ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል’ ሆነና መስኮት ይከፈት ማለት ሰበብ ሆኖ ተገኝቶ ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን ታክሲያችን የተቃዋሚና የገዥውን ፖለቲካ ማዳመጥ ግድ አላት!

  ወያላችን ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። ‹‹በይ ነገርኩሽ ዝም ብለሽ ትሄጂ እንደሆን ሂጂ ነገር አታምጪ›› ሙሉ ቀሚሷን እስኪሸፍን ነጥላ ያጣፋችውን ነጠላ ደጋግማ የምትጎትት ወይዘሮ። ባልንጀሮች ይመስላሉ። ‹‹አንቺ ደግሞ ገንዘብን ገንዘብ ብለሽው። እንካማ ጫኝ አውራጅ የእሷን ሒሳብ፤›› ትላለች ወዳጇ። ሲያዩዋቸው መንትዮች ይመስላሉ። ወያላው ‘ጫኝ አውራጅ’ መባሉ አስከፍቶታል። እናም ነገር ጎንጉኖ፣ ‹‹እኔን ነው?›› አላት። ዝርዝር ብሮች ይዘው ወደ እሱ የተዘረጉትን እጆች በጥርጣሬ እየተመለከተ። ‹‹ታዲያ ሌላ ‘ጫኝ አውራጅ’ አለ?›› ደገመችለት ሞንዳሊት። ‹‹ምነው እናንተ መርካቶ ያላችሁ መሰላችሁ?›› አጉረመረመ ወያላው። ‹‹ምን አልክ? አየነው መርካቶን ከእግር እስከ ራሱ አለ የፒያሳ ሰው። አንቺዬ አንዲህ እንደ ቀበሮ ሥር ለሥር እያነፈነፉ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታችን ተገደበ ብለው መንግሥትን ሲያሙ ግን አይገርሙሽም?›› ተባብለው ሲያበቁ ከፋይ መልሷን ተቀብላው ፊቷን አዞረች።

  ወያላው ዓይኑ እንደ ቀላ፣ ‹‹መቁጠሪያ በመያዣቸውና በመቁረቢያቸው ዘመን እየተላከፉ ልበ ደንዳናነታችንን ያባብሳሉ፤” ብሎ በሩን ሲዘጋ ሾፌሩ፣ ‹‹ባልሰማ ባላየ ማለፍ ነው። አለበዘሊያ አንተም እንደ አምባገነን መሪዎች የንስሐ ዕድሜ ሳይተርፍህ መሞትህ ነው፤›› ይለዋል። ሒሳብ ከተከፈለላት ወይዘሮ ተደርበው የተቀመጡ አዛውንት አስነጠሱ። ደገሙ። ሦስተኛ ማሳረጊያ እንጥሻቸውን እንዳገባደዱ ቀና ብለው ወደኋላና ወደፊት አማተሩ። ጥቂት ሲያስቡ ቆዩ። እንባ እንባ እንዳላቸው ያስታውቃሉ። ‹‹ማነህ ሾፌር አውርደኝ፤›› ኮስተር ብለው ቃል ካንደበታቸው እንደ ወጣ፣ ‹‹ወያላው ለምን ገቡ? አስነጥሰውብን ሊወርዱ ነው የተሳፈሩት?›› አላቸው። ‹‹እና ላንተ ብዬ ይማርህ ማለት ከረሳ መንገደኛ ጋር ልጓዝ?›› በጣም ተቆጡ። ወይዘሮዋ ጣልቃ ገባች። ‹‹አይ እርስዎ። ሰው እኮ ወደ ውስጥ እያስነጠሰና እየሳለ የሌላ ሰው ማድመጥ ትቷል። ወይ የፌስቡክ አካውንትዎን ይናገሩና እየገባን ኮሜንት ሳጥን ላይ እንጻፍልዎ እንጂ፣ ፊት ለፊት ሰው መማማር ትቷል፤›› አለቻቸው። ካልወረድኩ ብለው ያገነገኑት አዛውንት ወይዘሮዋ እንዳለቻቸው አርፈው ተቀመጡ። ድጋሚም አላስነጠሱብንም። ምናልባት ወደ ጅጊው፣ ወደ ደቦው ተቀላቅለው ንጥሻቸውን ‘ሳይለንት’ አድርገውት ይሆን? የሚያኖርና የሚምር ሰው የጠፋበት ዘመን ሆነ እኮ ዘመኑ እባካችሁ! 

  ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። በዚያ ጨለማ ዩኒፎርም የለበሱ ልጆች እያሽካኩ ከመጠጥ ቤት ሲወጡ ድንገት ዓይናችን ገባ። ‹‹ተመልከት እንዲህም አልሆን ብሎናል ሰው ይወልደዋል፤›› ይለዋል ከኋላችን ከተቀመጡት ባልሰማ ያሳለፈው። ‹‹እና አንተ ምን አገባህ? ውለድ አልተባልክ። ምናለበት ሰው ዓይኑን በዓይኑ ዓይቶ ቢያልፍ? እዚህ አገር አንድ የእርካታ ምንጭ ልጅ ብቻ መሆኑን አጥተኸው ነው?›› እያለ መዓት ወረደበት። ‹‹ወይ የዘንድሮ ዩኒቨርሲቲ? አሁን አንተ በድህነት በምትማቅቅ አገር የሕዝብ ቁጥር መጨመር ስለሚያስከትለው ጉዳት ሳታውቅ ነው አምና ዲግሪ ያዝኩ ብለህ የደገስከው?›› ብሎ ሊያሳፍረው ሲሞክር፣ ‹‹ዲግሪ ሌላ ኑሮ ሌላ። እዚህ አገር አንተስ ከመቼ ወዲህ ነው ሰዎች እንደተማሩት ሲያስቡ፣ ሲኖሩና ሲሠሩ ያየኸው? ደግሞስ ዲግሪ ምንድነው? የጫት ዲግሪ፣ የመጠጥ ዲግሪ፣ የሐሽሽ ዲግሪ በዝምታ ጭብጨባ በደቦ እያደልን እያያችሁ ዲግሪ ዲግሪ የምትሉት ለመሆኑ ትርጉሙ እየገባችሁ ነው?›› ቢለው ዝም ዝም ሆነ።

  መውለድን የኮነነው ወጣት ዝም እንዳለ ጓደኛው የሚያነበንበውን ያዳምጣል። ‹‹ወልደን በዚህ ኑሮ ላይ ቅመም ካልጨመርንበት እያዛጋን እስከ መቼ? እንዴ! አስተውለሃል ለመሆኑ? ለዛ ያለው ነገር እኮ እልም ብሎ ጠፋ። ጣዕም የሚባል ነገር… ተወው ሌላውን ከዘፈን አቅም እንኳ የድሮ እየጎረጎርን ስናደምጥ አይደል እንዴ የምንውለው? ባይሆን ‘ሶሊውሽኑ’ ምንድነው ብሎ ጉዳዩን ‘ኢሹ’ ማድረግ መቻል አለብን፤›› እያለ መውለድን ያበረታታል። ‹‹አይ እናንተ? አጨራረሱን እያያችሁ በአጀማማሩ ትሟገታላችሁ? ውልደት ውልደት ነው። ከደሃ ተወለድን ከሀብታም፣ ከንጉሥ ተወለድን ከአገልጋይ፣ በበረት ተወለድን በቤተ መቅደስ ለውጥ የለውም። ዋናው አጨራረሱ ነው። ብቻ የሚገርመኝና የማይገባኝ በስንፍና፣ በሙስና፣ በቸልተኝነት እግራቸውን ሰቅለው ከቤት እስከ አደባባይ ሸክም የሆኑብንን ለምን ሥራቸው እንደማያስጠይቃቸውና እንደማያስገኛቸው ብቻ ነው፡፡ ትውልድን በሱስ ማፍዘዝም እኮ ከባድ ሙስና ነው። ብቻ የምንጠያየቅበት ቀን ናፈቀኝ፤›› ስትል ከአጠገቤ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። አንድ በአንድ እየወረድን ወደ ጉዳያችን ስንበታተን በብርድ ላይ ናፍቆት ሲደረብ እያሰብን ያንዘፈዝፈን ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!  

   

   

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት