Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየ2008 አክራሞት

  የ2008 አክራሞት

  ቀን:

  የ2007 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ፤ 2008 ዓ.ም. የሰላም፣ የደስታ የፍቅርና የብልፅግና እንዲሆን ብዙዎች ተመኝተዋል፡፡ 2008 ዓ.ም. ብሩህ ተስፋ ይዞ እንዲመጣ በመመኘትም፣ የሃይማኖት አባቶች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ መንግሥትም እንዲሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ 2009 ዓ.ም.ን ተቀብለናል፡፡ 2008 ዓ.ም. እንዴት ከረመ? መንግሥት በጤናው፣ በትምህርቱና በኢኮኖሚው አስመዝግቤዋለሁ ከሚለው ዕድገት ጎን ለጎን፣ በ2008 ሕዝቡ ምን ዓይነት ማኅበራዊ ቀውሶችን አስተናገደ?

  2008 ዓ.ም. ገና በመባቱ የተከሰተውና በማኅበረሰቡ የወተት አጠቃቀም ብሎም በወተት አምራቾች ላይ ብዥታን የፈጠረው፣ በወተት ውስጥ የሚገኝ አፍላቶክሲን መጠን 0.41 ሆኖ መገኘት የጉበት ካንሰርን ያስከትላል መባሉ ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ኢልሪ) በአዲስ አበባና በውስን የአዲስ አበባ ሥፍራዎች ከሚገኙ 100 የወተት ላም አርቢዎች፣ አሥር ወተት ሰብሳቢዎች ብሎም 156 የመኖ ናሙናዎችን ከአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ሰበታ፣ ሰንዳፋና ሱሉልታ በመውሰድ በወተት ናሙናዎች፣ በድብልቅ መኖዎች ላይ ያካሄደው ምርምር ውጤት፣ በተለያዩ ሚዲያዎች መገለጹ፣ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ሰዎች ወተት ከመጠጣት እንዲቆጠቡ ሲያደርግ፣ አምራቾች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የአፍላቶክሲን መብዛት ለጉበት ካንሰር ስለሚያጋልጥ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ጤና ክብካቤ ባለሥልጣን ወተት አምራቾችና መኖ አቅራቢዎች ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ፣ ባስታወቀው መሠረት ቁጥጥሩን አጠናክሯል፣ ወተት አምራቾች በምን መልኩ ሊያቀርቡ እንደሚገባ አሳውቋል፡፡

  አሥር ዓመታትን እየተሻገረ ኢትዮጵያን የሚያጠቃው ድርቅም በ2008 ዓ.ም. አሻራውን አሳርፏል፡፡ ለድርቁ ኤሊኖን ተከትሎ የሚመጣ የዝናብ እጥረት እንዲሁም ሌሊኖ ያስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት መሆናቸውን መንግሥት ገልፆ ነበር፡፡ ድርቁ እንደተከሰተ 2.9 ሚሊዮን ሰዎች ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም፣ የተረጂዎች ቁጥር ወደ 10.2 ሚሊዮን የደረሰው ድርቁ በተከሰተ በወራት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ መንግሥት የድርቁን ተፅዕኖ ‹‹በራሴ›› አቅም እቋቋማለሁ ብሎ በተደጋጋሚ የገለጸ ቢሆንም፣ ድርቁ በነበረበት ወራት ከሚያስፈልገው 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 54 በመቶው እንኳን መገኘት አለመቻሉ ሌላ ራስ ምታት ነበር፡፡

  ድርቁ ያስከተለውን ቀውስ ለመዘገብ በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ድጋፍ የተንቀሳቀሱ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ድርቁ በተለይ በምሥራቅ ሐረርጌ ጠባሳ ማሳረፉን ዘግበዋል፡፡ በምሥራቅ ሐረርጌ በድርቁ ምክንያት የተረጂዎች ቁጥር ከነበረበት 500 ሺሕ ወደ 900 ሺሕ እንደሚደርስ ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በአርሲ ዶዶታ ደግሞ፣ የተረጂዎች ቁጥር ከ14,404 ተነስቶ ከ51 ሺሕ በላይ ሆኗል፡፡ መንግሥት ለድርቅ ተጎጂዎች ይሰጥ የነበረው ዕርዳታ በቂ እንዳልነበረ፣ የውኃ ችግሩ ደግሞ ከምንም በላይ እየጎዳቸው እንደበር የድርቁ ተጎጂዎች በወቅቱ ተናግረዋል፡፡

  በድርቁ በተለይ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በጣም የተመቱ ሲሆን፣ በምዕራብ ሐረርጌ ብቻ ከ2,200 ከብቶች በላይ መሞታቸው ታውቋል፡፡ ሐሩሩ ጋብ ብሎ ከሚያዝያ 2008 ዓ.ም. በኋላ ዝናብ መጣል ቢጀምርም፣ ሌሊኖ ያስከተለው ጎርፍ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች ማሳዎችን አውድሟል፡፡ የመሬት መንሸራተት አስከትሎም የሰው ሕይወት ቀጥፏል፡፡

  በሐዋሳ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶም ሰዎች መኖሪያቸውን ለቀናት ለቀው ሲሰነብቱ፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲም ለ15 ቀናት ያህል ትምህርት ዘግቶ ነበር፡፡

  የድርቁ ጥላ ሳያልፍ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንን ተከትሎ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የተከሰተው አመፅ 2008 ዓ.ም.ን ፈትኖታል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ይዘት አለው የተባለው ማስተር ፕላን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውስን አስከትሏል፡፡ ኅዳር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በአምቦ፣ በጊንጪና በምዕራብ ወለጋ የተጀመረው ተቃውሞ፣ በክልሉ በርካታ ከተሞች ተስፋፍቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና አልፎ አልፎም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲካሄድ የነበረው ተቃውሞ፣ ኋላ ላይ ነዋሪዎችን አካቷል፡፡ የተቃውሞው ዋነኛ ጥያቄ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ይሰረዝ የሚል ነበር፡፡ ማስተር ፕላኑ ይፋ መሆኑን ተከትሎ በግንቦት 2006 ዓ.ም. በተጠሩ ሰልፎች፣ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች ታስረዋል፣ ተጎድተዋል፣ ንብረትም ወድሟል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው አመፅ በ2008 ዓ.ም. ሲቀሰቀስ፣ አንዱ አጀንዳ ማስተር ፕላኑ ሲሆን፣ የሕዝቡን ጥያቄ ተከትሎ መንግሥት ማስተር ፕላኑ እንደተሰረዘ አሳውቋል፡፡ ሆኖም አመፁ አላባራም፡፡ ብቅ ጥልቅ በሚለው አመፅም ሰዎች እየሞቱ፣ ንብረት እየወደመ ትምህርት እየተስተጓጎለ ንግድ እየተሰናከለ ከርሟል፡፡

  በኦሮሚያ ክልል መስከረም 2008 ዓ.ም. ከገባ መንፈቅ እንኳን ሳይቆይ የተቀሰቀሰው ዓመፅ እንዲሁም ውጥረት ዓመቱ እስኪያልቅ መላ አላገኘም፡፡ ይልቁንም በአማራ ክልል፣ በተለይ በጎንደርና ጎጃም ከወልቃይት የማንነት ጥያቄና ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ዓመፅ ውጥረትን፣ ሥጋትን አንግሷል፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ለሚነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ ያለመሰጠቱ ተጠራቅሞም ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ 2008 ላይ ፈንድቷል፡፡ ሰዎች እንዲሞቱ፣ እንዲታሰሩና እንዲንገላቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአማራ ክልል በተለይ ጎንደርና ባህርዳር ግብይት በመቀዛቀዙ የከተሞቹ ነዋሪዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ መንግሥት መከላከያ ሠራዊት በሥፍራው እንዲገባም በይፋ አዟል፡፡ ይሁን እንጂ በሁለቱ ክልሎች ሕዝቡ በተለያየ መንገድ ተቃውሞውን ከመግለጽ አላባራም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩም በሪዮ በተካሄደው 31ኛው ኦሊምፒያድ በማራቶን የብር ሜዳልያ ተሸላሚው ፈይሳ ሌሊሳ እጁን በማጣመር ተቃውሞውን አሳይቷል፡፡  

  የኢንፍሎዌንዛ ቫይረስም 32 ሰዎችን አጥቅቶ ከእነዚህ ውስጥ ተጓዳኝ በሽታ የነበረባቸው አራት ሰዎች መሞታቸውን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የገለጸው በዚሁ ዓመት ነው፡፡ ኢንፉሉዌንዛ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ያሳወቀ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ገብቶ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ በይፋ የተገለጸው አምና ነው፡፡

  በአዲስ አበባ የታክሲ አሽከርካሪዎች አድማ የመቱትም በዚሁ ዓመት ነው፡፡ በዕለቱ ተማሪዎች፣ ከትምህርታቸው፣ ሠራተኞች ከሥራቸው ተስተጓጉለው ውለዋል፡፡ የታክሲ አሽከርካሪዎች የሥራ ማቆም አድማውን የመቱት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 208/2003 ተግባራዊ መሆንን ተቃውመው ነው፡፡ በዕለቱ መንግሥት ፐብሊክ ሰርቪስ አውቶቡሶች ከመንግሥት ሠራተኞች ውጭ ላሉትም አገልግሎት እንዲሰጡ ሲያደርግ፣ ግለሰብ አሸከርካሪዎችም እግረኞችን በማጓጓዝ አግዘዋል፡፡ ዕድል ያልቀናቸው ደግሞ በእግራቸው ለመጓዝ ተገደዋል፡፡

  የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንቡ፣ በተለያዩ እርከኖች የተቀመጡትን ጥፋቶች የፈጸመ እንደጥፋቱ ዓይነት ቅጣት እንዲጣል የሚያዝ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አንድ አሽከርካሪ 14 ነጥብ የሚደርስ ጥፋት ካጠፋ፣ የመንጃ ፈቃዱ ለስድስት ወር እንደሚታገድና የተሃድሶ ሥልጠና እንደሚወስድ መደንገጉን ነበር 13 የታክሲ ማኅበራት፣ ሦስት የሃይገር ሚዲ ባስ ማኅበራትና የታክሲ አሽከርካሪዎች የተቃወሙት፡፡ ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ከታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ጋር ባደረገው ድርድር፣ ለተወሰነ ጊዜ ደንቡን ተግባራዊ ከማድረግ ተቆጥቧል፡፡

  የቃና ቲቪ አየር ላይ መዋል የማኅበረሰቡን እሴትና የአገር ውስጥ የጥበብ ሥራን ያጠፋል በሚል የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተቃውሟቸውን የገለጹትም ባሳለፍነው ዓመት ነው፡፡ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትም ቃና ቲቪን መመልከት ሐጢያት መሆኑ ለምዕመናን ሲነገር ተሰምቷል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ናቸው የተባሉ ቤቶች በመፍረሳቸውም በሺሕ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች የተበተኑት ባሳለፍነው ግንቦት 2008 ዓ.ም. ውስጥ ነው፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ ወረገኑ ከሚባል ስፍራ በሕገወጥ የመሬት ወረራ ተገንብተዋል የተባሉ ከሁለት ሺሕ በላይ ቤቶች በአፍራሽ ግብረ ኃይል የፈረሱ ሲሆን፣ በዚህም በአፍራሽ ግብረ ኃይሉና በነዋሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት ከ50 በማያንሱ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

  በሰኔ ወር ማብቂያ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃና ማርያም በተባለው አካባቢ፣ ሕገወጥ ናቸው የተባሉ ቤቶችን ከማፍረስ ጋር በተያያዘ፣ በነዋሪዎችና በፖሊስ መካከል በተነሳ ግጭት፣ የሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በዚህ ዓመት ካስተቹት ዋና ጉዳዮች አንዱም፣ ከሰባትና ስምንት ዓመታት በፊት የተገነቡ ቤቶችን በዚህ ዓመት ሕገወጥ ናችሁ ብሎ ማፍረሱ ነው፡፡

  አስተዳደሩ፣ በክረምት በሺሕ የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን አውጥቶ ሲበትን፣ 500 የሚደርሱ ጊዜያዊ ቤቶችን ሠርቶ በጣም ለተቸገሩት እንደሚሰጥም ገልፆ ነበር፡፡ ከሥፍራዎቹ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች አዲስ አበባ ዙሪያ ርካሽ ቤት ኪራይ ፍለጋ ሲንከራተቱ፣ ይህንን ማድረግ ያልቻሉትም ላስቲክ ቀልሰው ከጅብ እየተሳደዱ እንደሚኖሩ መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡

  የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የሆነው የ12ኛ ክፍል ፈተና በመሰረቁ ከግንቦት 22 እስከ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊሰጥ የታቀደው ፈተና የተሰረዘውም በዚሁ ዓመት ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተነሳውን ዓመፅ ተከትሎ፣ ትምህርት በመስተጓጎሉ ሳቢያ ተማሪዎች መፈተን የለባቸውም ከሚል አመለካከት ፈተናውን ማሰረቃቸውን፣ በውጭ የሚገኙ አካላት መግለጻቸው፣ ለእማኝም የእንግሊዝኛ ፈተናንና ሌሎችንም ፈተናው ከመሰጠቱ ጥቂት ቀናት ቀድሞ በማኅበራዊ ድረ ገጽ መለጠፋቸው፣ በተፈታኝ ተማሪዎችና ቤተሰቦች እንዲሁም በመንግሥት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ አልፏል፡፡  መንግሥት የውስጥ ፖለቲካውን እንዲፈትሽ የተለያዩ አካላት ሲገልጹም ከርመዋል፡፡

  ፈተናው መሰረቁ ቀድሞ በማኅበራዊ ድረገጾች ቢለቀቅም፣ ትምህርት ሚኒስቴር ፈተናውን የሰረዘው ተማሪዎች ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት የእንግሊዝኛ ፈተናን እየወሰዱ ነው፡፡ ‹‹ፈተናውን ቀድሜ ያልሰረዝኩት ፈተናው ምን እንደሆነ ስለማላቅና ፈተናው ሲጀመር ማረጋገጥ ስለነበረብኝ ነው›› የሚል ምላሽ የሰጠው ሚኒስቴሩ፣ የትችት ሰለባም ሆኗል፡፡ 253 ሺሕ 424 ተማሪዎች ለመፈተን የተመዘገቡበት፣ ለዝግጅቱ 215 ሚሊዮን ብር የወጣበት ፈተና ተሰርዞ፣ ፈተናው ከሐምሌ 4 እስከ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

  8,874 ፈታኞች፣ የፈተና ተቆጣጠሪዎችና ጣቢያ ኃላፊዎች በፈተና ጣቢያዎች ተመድበው የፈተኑ ሲሆን ፈተናውም ያለስርቆት ተጠናቋል፡፡ ፈተናው በድጋሚ በሚሰጥበት ወቅት ማኅበራዊ ድረገጾች እንዲዘጉ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም መንግሥትን ለሰላ ትችት ዳርጎታል፡፡

  አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ከሰኔ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለህትመት እስከገባንበት ጳጉሜን 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ አዲስ አበባን እንደተጠናወታት ቀጥሏል፡፡ ሆስፒታል የሚሄዱ ሕሙማን ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም፣ ከተማዋ አተትን መቆጣጠር አልቻለችም፡፡ አተት በትግራይና አማራ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎችም ተከስቷል፡፡ የተጠቂዎችን ቁጥር ለመግለጽ ግን መንግሥት ዳተኝነቱን አሳይቷል፡፡

  ከአዲስ አበባ የሚመነጭ ቆሻሻ ሰንዳፋ በተሠራው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሥፍራ እንዳይጣል የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውመዋል በሚልም፣ ከጥር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ጎዳናዎችና ጥጋጥጎች የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆነዋል፡፡ ከተማዋ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ዲፕሎማቶች መቀመጫ ብትሆንም፣ በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ ጎዳናዎቿም የቆሻሻ ማስተናገጃ ሆነዋል፡፡

  አዲስ አበባ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ካለው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ሥጋትና ውጥረት የነገሠባት ብትሆንም፣ በከተማዋ የተሞከረ ሰላማዊ ሠልፍ በፀጥታ ኃይሎች ቢከሽፍም ጥላው አጥልቶባታል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ባሉ ዋና ዋና በሚባሉና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ያለው አለመረጋጋት አዲስ አበባን እየነዘራት ነው፡፡

  በአንዳንድ ሥፍራ እንደተመለከትነውም ነዋሪው እህልና ጥራጥሬ በተለይ ጤፍ ከቀድሞ አስቤዛው አስበልጦ ገዝቷል፡፡ አንዳንድ ወፍጮ ቤቶችም ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ልማድ በተለየ መልኩ፣ ለአንድ ግለሰብ እስከ ሁለት ኩንታል ጤፍ መፍጨታቸውን ተናግረዋል፡፡

  በኦሮሚያ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ፣ በተለያዩ ከተሞች የሚታየው አለመረጋጋት አሳሳቢ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመቱ አጋማሽ አሳውቆ፣ በአገሪቱ አንዳንድ ሥፍራዎች የተከሰተው ግጭት በአስቸኳይ እልባት እንዲያገኝ፣ መንግሥት የጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክርም አሳስቦ ነበር፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ችግርና ሰላማዊ ጥያቄ በመገንዘብ መፍትሔ እንዲሰጥ፣ ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን የዕለት ከዕለት ጥረት እንዲቀጥልም ያሳሰበው በዚሁ ዓመት ነው፡፡

  በ2008 ዓ.ም. በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተለያዩ ከተሞች የተነሱ ግጭቶች የራሳቸውን ጠባሳ ጥለው አልፈዋል፡፡ ሰዎች ሞተዋል፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ተሰደዋል፣ ታስረዋል፡፡ ሲንከባለል የመጣውንና በ2008 ዓ.ም. የፈነዳውን የነዋሪውን ብሶት፣ መንግሥት ከመልካም አስተዳደር እጦት የመጣ ነው በማለት፣ ችግሩን ለማቃለል እየሠራሁ ነው፣ የውስጥ አሠራር ለውጥም አደርጋለሁ ብሎ ቢገልጽም ዓመቱ ያለቀው የሕዝብን ብሶት ሳያብስ ነው፡፡ ችግሮችና ብሶቶች አፈትልከው ወጥተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ፣ እህልና ሸቀጥ ከክልል ክልል እንዳይገባ የሚል የቤት ውስጥ አመፅ መሰማቱም፣ አገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶቡሶች አንዳንድ ሥፍራዎች እንዳይገቡ መደረጋቸው፣ የገቡትም ደግሞ የጥቃት ሰለባ መሆናቸው የፖለቲካው አለመረጋጋት ያስከተላቸው ማኅበራዊ ቀውሶች ናቸው፡፡  በሌላ በኩልም በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ከሚገኙት ማረሚያ ቤቶች መካከል የእሳት ቃጠሎ መድረስና በሕግ ጥላ ሥር ላይ ባሉ ወገኖች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ መድረሱ አንዱ አስከፊ ገጽታ ሆኖ አልፏል፡፡

  የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገሪቱ የሚታየው አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪውን ያስተላለፈውም በ2008 መገባደጃ ነው፡፡ 2008 ዓ.ም. የሰላም ይሁን ብለን ብንቀበለውም፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩት 25 ዓመታት በተለየ መልኩ በውጥረቶች አልፈነዋል፡፡ ይህ ውጥረት በ2009 ዓ.ም. ይቀጥል ይሆን?

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...