Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ባንኮች በተጠናቀቀውና በመጪው ዘመን

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የተሸኘው በጀት ዓመት በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አዳዲስ ክስተቶች የታዩበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ለኢንዱስትሪው እንግዳ የሆኑ አዳዲስ አገልግሎቶች ይፋ የተደረጉበትም ነበር፡፡

  በምሳሌነት ሊጠቀሱ ከሚጠቀሱት አንዱ ሁሉም የአገሪቱ የአገሪቱ ባንኮች አንድ ዓይነት ወይም ወጥ የቼክ ክፍያ ማስተናገደጃ ሥርዓት ተግባራዊ ያደረጉበት ዓመት ነው፡፡ ነባሩን ቼክ ይተካል የተባለው አዲሱ ቼክ ከነባሩ ጋር ጎን ለጎን እንዲሠራ ተደርጎ ከሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በኋላ ግን አዲሱ ቼክ ሙሉ ለሙሉ ተግባር ላይ በመዋል የቀረውን ተክቶ ይሠራል ተብሎ ነበር፡፡ ይሁንና አዲሱን ቼክ በተገቢው መንገድ ማሰራጨት ባለመቻሉ ነባሩና አዲሱ ቼክ መሳ ለመሳ አገልግሎት የሚሰጡበት ጊዜ ለስድስት ወራት ተራዝሟል፡፡

  በፋይናንስ ኢንዱስትሪው አዲስ የሆነው ሌላው የአገልግሎት ዘርፍ የሁሉም ባንኮች የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ማሽኖች (ኤቲኤም) ለሁሉም ባንኮች ደንበኞች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ነው፡፡ ይህም ማለት የየትኛውም ባንክ የኤቲኤም ማሽን፣ የሚጎርሰውን ካርድ በአግባቡ ተቀብሎ ደንበኞችን ማስተናገድ ይችላል ማለት ነው፡፡ በሁሉም ባንኮች የባለቤትነት ድርሻ በተመሠረተውና ኢትስዊች በተባለው ኩባንያ በኩል ተግባራዊ የተደረገው ይህ አገልግሎት ለፋይናንስ ዘርፉ አዲስና እንግዳ ነበር፡፡ እርግጥ እውን ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ በርካታ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ በ2008 ወደ ተግባር የገባ አዲስ አሠራር ነበር፡፡

  በ2008 ዓ.ም. በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንግዳ የተባለው ሌላው ክስተት ደግሞ   የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስተላለፈው አዲስ ሰርኩላር ነበር፡፡ ይህም በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ግምት ያላቸው ንብረቶች በባንክ ዕዳ የተያዘባቸው የደቡብ ቡና አቅራቢ ነጋዴዎችን ለመታደግ ሲባል የወጣው ሰርኩላር ነው፡፡ ከብድር አሰጣጥና አሠራር ሕግጋት ውጪ ቡና አቅራቢዎቹ እንዲስተናገዱበት የሚስችል ውሳኔ በማሳለፍ ለባንኮች የተሰራጨው ሰርኩላር፣ የብድር ዕዳቸውን በጊዜ ሰሌዳው መሠረት መክፈል ባለመቻላቸው፣ አቅራቢዎች ሐራጅ ተብለው ንብረቶቻቸው እንዳይሸጥ የሚከላከል ሲሆን፣ በዘርፉ አነጋጋሪ የተባለ ጉዳይ ሆኖ ማለፉም ይታወሳል፡፡

  የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ቀድሞ ከአንድ በላይ በሆኑ ባንኮች ማመልከቻ በማቅረብ በአማራጭ ይጠቀሙበት የነበረው አሠራር የቀረውም በተሰናባቹ ዓመት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊ ሊስተናገድ የሚችለው በአንድ ባንክ ብቻ እንዲሆን ሲደረግ፣ ማመልከቻውን ለሌላ ባንክ ካቀረበ የማይስተናገድና እንደውም የሚያስጠይቅ አሠራር ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቁ ውጤት የተገኘበት፣ ብሔራዊ ባንክም ክትትል እያደረገ ስኬት ያሳየበት ነው ተብሎ የሚጠቀሰው የቴክኖሎጂ ዝርጋታ፣ ሁሉንም የአገሪቱ ባንኮች በኮር ባንኪንግ ማስተሳሰር መቻሉ ነው፡፡ የመጨረሻዎቹ ሦስት ባንኮች በኮር ባንኪንግ የሚያስተሳስራቸውን ሥራ በማጠናቀቅ ለዘመናዊ አገልግሎት መዘጋጀታቸው በባንክ ኢንዲስትሪው ትልቅ እመርታ ተደርጓል፡፡

  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ መገንባት የጀመረበት ዓመት ሆኖም ይጠቀሳል፡፡ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ከመጀመርና ከማስተዋወቅ አኳያም እንደ ኤጀንት ባንክ ያሉ አገልግሎቶች የተጀመሩትም በአብዛኛው በተሰናበትነው ዓመት ነው፡፡

  በአገሪቱ የኩባንያዎች ጥምረት ትልቁና ያልተጠበቀ ሆኖ የተስተናገደው የሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች ቅልቅል በይፋ የተከናወነው በ2008 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮንስትራክሽን ቢዝነስ ባንክን በመጠቅለል በተወሰነ መልኩ ይበልጠ ገዝፎ እንዲወጣ ያስቻለው ሲሆን፣ የግል ባንኮችም የወደፊት አቅጣጫቸው ውህደት አለያም አንዱ በሌላው መጠቅለል ሊሆን እንደሚችል አመላካች ስለመሆኑ በሰፊው የተነገረበትና የተመከረበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡

  አንዳንድ ባንኮች የፕሬዚዳንቶቻቸውን ወርኃዊ የደመወዝ መጠን ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ማድረስ መጀመራቸውም ከተጠናቀው በጀት ዓመት ስለባንክ ከተወሩ ወሬዎች ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አኳያም የተፈጠረው እጥረት ባንኮችን የፈተነበት ዓመት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲሰጠው በመደረጉ፣ የግል ባንኮች ደንበኞችም የውጭ ምንዛሪ በተናጠል እንዲያገኝ ወደተደረገው ንግድ ባንክ እንዲጎርፉ አስገድዷል ተብሎ ገዥው ብሔራዊ ባንክ ሲሞገት የነበረበት ዓመትም ነበር፡፡

  የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንትና ጥቂት የቦርድ አባላት እንዲሁም የዘመን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ዕርምጃም ከብዙ በጥቂቱ በኢንዱስትሪው የተከሰቱ ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገርም የአገሪቱ ባንኮች አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከወትሮው ሻል ያለ ውጤት ያሳዩበት ዓመት ስለመሆኑ የሚያመለክቱ መረጃዎችም እየወጡ ነው፡፡

  ባንኮችና የተቀማጭ ገንዘባቸው ዕድገት

  በአገሪቱ ውስጥ ያሉት 18ቱም የግልና የመንግሥት ባንኮች በ2008 በጀት ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው ከ435 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ይህ ከ2007 በጀት አኳያ ሲታይ ዓመት ብልጫ ያስመዘገበ ውጤት ሲሆን፣ በቀደመው ዓመት መገባደጃ ወቅት የሁሉም ባንኮች ተቀማጭ ገንዝብ 367.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2006 ደግሞ 292.8 ቢሊዮን ብር እንደነበር የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያስረዳል፡፡

   የአገሪቱ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው ባንኮቹ የተቀማጭ ገንዘባቸውን ለማሳደግ ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ አንዱና ዋነኛው መንገድ የነበረው ቅርንጫፎችን ማስፋፋት በመሆኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከፈቱት ቅርንጫፎች ብዛት እንዳላቸው የባንኩ መረጃ ያሳያል፡፡ እንደ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ጥንቅር ከሆነ፣ በ2006 መጨረሻ ላይ የሁሉም ባንኮች ቅርንጫፎች ቁጥር 2,208 ነበር፡፡ በ2007 ደግሞ 2,693 ደርሷል፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በነበረው መረጃ መሠረት የቅርንጫፎቹ ቁጥር 3,153 ደርሶ ነበር፡፡

  16ቱ የግል ባንኮች ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 147 ቢሊዮን ብር አሻቅቧል፡፡ 2008 በጀት ዓመት የግል ባንኮች ለመጀመርያ ጊዜ ተቀማጭ ገንዘባቸውን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻሉበት ዓመት ነው፡፡ በታኅሳስ ወር፣ 16ቱ የግል ባንኮች የነበራቸው ተቀማጭ ገንዘብ 100 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡

  በ2007 መጨረሻ ላይ የግል ባንኮች የነበራቸው ተቀማጭ ገንዘብ 97 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የደረሱበት የተባለው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በንጽጽር ሲቀመጥ ልዩነቱ እንደሰፋ ያሳያል፡፡

  በ2008 በጀት ዓመት 18ቱም ባንኮች ካሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን 288.4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይኽም በኢንዱስትሪው ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ብልጫ ይዞ መጓዙን ያመለክታል፡፡

  የብድር ክምችት

  የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ እያደገ በመጣ ቁጥር የሚሰጡትም የብድር መጠን ያድጋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ባንኮቹ የሰጡት የብድር መጠን ዕድገት እየታየበት ቢሆንም፣ ባንኮች ከሚቀርብላቸው የብድር ጥያቄ አንፃር ፍላጎትን የሚያሟላ ምላሽ እየሰጡ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህም ሆኖ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 18ቱም ባንኮች በአጠቃላይ የሰጡት የብድር ክምችታቸው ከ232.1 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ደግሞ የብድር መጠኑ 217.3 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 75.6 ቢሊዮን ብሩ የግል ባንኮች ያበደሩት ሲሆን፣ ሦስቱ (አሁን ሁለቱ) የመንግሥት ባንኮች ደግሞ በጥቅል 141.7 ቢሊዮን ብር አበድረው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለብቻው የብድር ክምችቱ 111.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

  በሌሎች የባንኮች አገልግሎቶች እንደታየው ሁሉ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛውን ብድር በመስጠት ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ባንኩ በ2008 በጀት ዓመት ያሳየው የብድር ክምችት መጠን 138.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ 92 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ሰጥቷል፡፡ ይህም በበጀት ዓመቱ በኢንዱስትሪው ለብድር ከዋለው ገንዘብ ውስጥ ንግድ ባንክ የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ 16ቱ የግል ባንኮች ደግሞ በበጀት ዓመቱ የሰጡት የብድር መጠን በድምር ከ93.3 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተመልክቷል፡፡ ቀሪው 11.84 ቢሊዮን ብር ብድር የሰጠው ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነው፡፡

  ከግርድፍ መረጃው መረዳት እንደተቻለው ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ) በጥቅል ያበደሩት ገንዘብ የግል ባንኮች በድምር ከሰጡት ብድር ጋር ሲተያይ የመንግሥት ባንኮች የብድር መጠን ዕድገት ከፍተኛ ነው፡፡

  በበጀት ዓመቱ ውስጥ ከ16ቱ የግል ባንኮች ከፍተኛውን ብድር የሰጡ አዋሽ፣ ዳሸን፣ አቢሲኒያ፣ ወጋገን፣ ኅብረት፣ ንብና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንኮች ናቸው፡፡ እነዚህ ባንኮች በበጀት ዓመቱ የሰጡት ብድር ከአምስት እስከ 15.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

  ባንኮችና የተበላሸ የብድር መጠን

  እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ትንታኔ የአንድ ባንክ ጥንካሬ ከሚለካባቸው መመዘኛዎች አንዱ የሰጡትን ብድር በአግባቡ ማስመለሳቸውና ከተመላሽ ብድሩ ያገኙትን ትርፍ በአግባቡ ማጣጣም መቻላቸው ነው፡፡ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ የተመለሰ ብድር ጤነኛ በመሆኑ ተበዳሪውም ሆነ አበዳሪውን ባንክ ጤናማ አሠራር እንዳላቸው ይመሰክራል፡፡ የተበላሸ የብድር መጠን እያደገ በመጣ ቁጥር ለባንኩም ሆነ ለአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፍ አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ባለሙያዎች ገለጻ በአንድ አገር የአንድ ባንክ አደጋ ለሌሎችም ስለሚተርፍ ጥብቅ ክትትል ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል የተበላሸ ብድር መጠን መገደብ ያለበት መሆኑ ነው፡፡

  ብሔራዊ ባንክም የባንኮች የተበላሸ የብድር መጠን ከአምስት በመቶ በላይ መሆን እንደሌለበት በሕግ አስቀምጧል፡፡ የባንኮች የሙቀት መለኪያ እንደሆነ የሚነገርለት የተባለ የተበላሸ ብድር መጠን ከአምስት በመቶ በታች ከሆነም ጤናማነታቸው ይረጋገጣል፡፡ በእርግጥ የተበላሸ የብድር መጠናቸው ከአምስት በመቶ በላይ ቢሆን ግን በዚያው ልክ የመጠባበቂያ መጠን ይቀመጣል፡፡ ሆኖም የተበላሸ የብድር መጠኑ ከፍ እያለ ሲሄድ ግን ዓመታዊው የባንኮች የሥራ ውጤት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ምክንያቱም ማስመለስ ያልቻሉት ገንዘብ እንደኪሳራ ስለሚቆጠር ዓመታዊ ትርፋቸው እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሌሎች ተፅዕኖዎችንም ያሳርፋል፡፡

  ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ባንኮች ጤንነት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ብሔራዊ ባንክ ያምናል፡፡ የ2008 በጀት ዓመት የባንኮች የተበላሸ ብድር መጠን በአማካይ አምስት በመቶ አካባቢ ነው፡፡ ይህ መልካም ቢሆንም በተናጠል የአንዳንድ ባንኮች የተበላሸ የብድር መጠን ግን ከፍ ማለቱ፣ የጥቂቶቹም በዝቅተኛው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ታይቷል፡፡

  ከአንዳንድ ባንኮች የተገኘው የመጀመርያ ደረጃ የተበላሸ የብድር መጠን ውስጥ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ የተበላሸ ብድር ያላቸው ባንኮች ውስጥ አንዱ 7.9 በመቶ ደርሶበታል፡፡ ከ16ቱ የግል ባንኮች ውስጥ የተበላሸ የብድር መጠኑ ከአምስት በመቶ በላይ የሆነው አንድ ባንክ ነው፡፡ 4.7 በመቶ የደረሰበትም ባንክ አለ፡፡

  ባንኮችና እየጨመረ የመጣው ትርፍ

  የአገሪቱ ባንኮች አሁንም አትራፊ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ የ2008 በጀት ዓመት የትርፍ ሪፖርታቸው እንደሚያመለክቱም 18ቱም የግልና የመንግሥት ባንኮች በጥቅሉ ከታክስ በፊት ከ21.5 ቢሊዮን ብር በላይ አትርፈዋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከቀዳሚው በጀት ዓመት ብልጫ ያለው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 13.4 ቢሊዮን ብር በማትረፍ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ የተጣራ 413.9 ሚሊዮን ብር ሊያተርፍ ችሏል፡፡ 16ቱ የግል ባንኮች በጥቅል 6.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት 5.35 ቢሊዮን ብር አትርፈው ስለነበር የትርፍ ዕድገታቸው ወደ አንድ ቢሊዮን ብር እየደረሰ መሆኑን ያሳያል፡፡

  እንደ ግርድፍ መረጃው በጀት ዓመቱ ከግል ባንኮች ለመጀመርያ ጊዜ ከታክስ በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማትረፍ የበጀት ዓመቱ ከግል ባንኮች ከፍተኛውን ትርፍ ያተረፈው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ነው፡፡ ይኽም ለዓመታት በከፍተኛ የትርፍ መጠን ከግል ባንኮች የመጀመርያ ደረጃውን ይዞ ከነበረው ዳሸን ባንክ ተረክቧል፡፡

  ዳሸን በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 990 ሚሊዮን ብር በማትረፍ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ 471 ሚሊዮን ብር ወጋገን ባንክ 472 ሚሊዮን ብር፣ ኅብረት ባንክ 447 ሚሊዮን ብር፣ ንብ ባንክ ደግሞ 482 ሚሊዮን ብር በማትረፍ እስከ አምስተኛ ደረጃ ያለውን ቦታ ይዘዋል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ከባንኮች የትርፍ መጠን ጋር በተያያዘ በተለየ የታየው ክስተት ከግል ባንኮች በተከታታይ ሦስት ዓመታት ከአዋሽና ከዳሸን ባንክ ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የነበረው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የትርፍ መጠን ባልታሰበ ሁኔታ መቀነስ ነው፡፡ ባንኩ ከ2008 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት አግኝቶት ከነበረው ትርፍ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ ማሳየቱ ነው፡፡ ብርሃን ባንክ ደግሞ የ2008 በጀት ዓመት በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡

  የባንኮች የ2009 በጀት ዓመት ውጥን

  ከአንዳንድ ባንኮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2008 በጀት ዓመት ያገኙትን ውጤት እስከ 30 በመቶ ለማሳደግ ውጥን ይዘዋል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት 88 ሚሊዮን ብር ያተረፈው ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ በቀጣዩ ዓመት ትርፉን 150 ሚሊዮን ብር የማድረስ ዕቅድ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም 18 ቢሊዮን ብር ለማበደር ተዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡ ኅብረት ባንክ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ካፒታሉን ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ይሠራል፡፡

  በ2009 በጀት ዓመት የአገሪቱ ሁሉም ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖች ተክለው ለአገልግሎት የሚያበቁበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የባንኮች ኃላፊዎች እንደሚገልጹት ከሆነም በ2009 በጀት ዓመት ኤቲኤም የማይኖረው አንድም ባንክ አይኖርም፡፡ ሁሉም ባንኮች የኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ በ2009 በጀት ዓመት 18.8 ቢሊዮን ብር በመፍቀድ 14.08 ቢሊዮን ብር ለመልቀቅ አቅዷል፡፡ 654.04 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ መወጠኑን ያሰበው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ የብድር መጠኑንም ወደ ስምንት በመቶ አወርዳለሁ ብሏል፡፡

  በተናጠል እንደርስበታለን ብለው ከያዙት ዕቅድ ሌላ ግን ሁሉም ባንኮች ሊደርሱበት ይገባል የተባለ መመርያ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባመጣው የአምስት ዓመት ዕቅድ ክንውን ማንኛውም የቅርንጫፍ ቁጥሩን 30 በመቶ፣ የተቀማጭ ገንዘቡን መጠን ደግሞ 30 በመቶ የኤቲኤማቸውንም ቁጥር በ25 በመቶ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል የሚለው መመርያ የሚፈተሽበት ዓመት ይሆናል፡፡ ባንኮች 2009 በተለየ የሚተገብሩት ደግሞ በሚቀጥሉት ሦስት ተከታታይ ወራት የሚያደርጉባቸው ጠቅላላ ጉባዔዎችና ምርጫ በአዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚተገበሩበት ነው፡፡

  በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይ የግል ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ላይ 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያዘው መመርያ በዚህ ዓመት ይሻሻል ተብሎ ሲጠበቅ ሳይሻሻል ቀርቷል፡፡ ሆኖም በበጀት ዓመት ለቦንድ ግዥ ከዋለው ገንዘብ አምስት ዓመት የሞላው እየታሰበ መመለስ ተጀምሯል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች