Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ‹‹23 ሰዎች›› መሞታቸውን መንግሥት ገለጸ

  በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ‹‹23 ሰዎች›› መሞታቸውን መንግሥት ገለጸ

  ቀን:

  – የሟቾች ቁጥር መንግሥት ከሚለው እንደሚበልጥ እየተገለጸ ነው

  – ማረሚያ ቤቱ እስካሁን በአድማ በታኝ ፖሊሶች ተከቧል

  – የሟቾች ዝርዝር ሐሙስ ይፋ ይደረጋል ተብሏል

  ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ፣ አዲስ አበባ በሚገኘው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በተነሳ የእሳት አደጋ ‹‹የ23 ሰዎች›› ሕይወት ማለፉን መንግሥት ይፋ አደረገ፡፡

  በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ግን የሟቾች ቁጥር ከዚህ እንደሚበልጥ እየገለጹ ነው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች እንደሚገልጹት ከ30 በላይ የወደቁ ሰዎችን ማየታቸውን፣ በወቅቱ የነበረው የአምቡላንስ ምልልስም መንግሥት ከገለጸው የሟቾች ቁጥር ጋር እንደማይገናኝ ገልጸዋል፡፡ ሟቾቹ በሙሉ እስረኞች ናቸው ለማለት እንደሚከብድ የሚናገሩት የሪፖርተር ምንጮች፣ አብዛኞቹ ግን እስረኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ 

  ለዚህ ጥርጣሬያቸው መነሻ እሳቱ በተነሳበት ወቅት ግቢው ውስጥ ገብተው የነበሩ የእስረኞች ቤተሰቦች መኖራቸውን ነው፡፡ አንዳንዶቹም በፀጥታ ኃይሎች እንደ እስረኛ ተቆጥረው ከሁለት ቀናት እስር በኋላ መፈታታቸውን ገልጸዋል፡፡

  አብዛኞቹ የማረሚያ ቤቱ ሕንፃዎች በእሳት ተለብልበው ይታያሉ፡፡ አንዳንዶቹ ክፍሎች የተሠሩት ከላሜራ መሆኑን ለመመልከት የተቻለ ሲሆን፣ በእሳት የተለበለቡ የጐን የላሜራ ግድግዳዎችና ጣሪያዎችም ተገነጣጥለዋል፡፡

  የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በዕለቱ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በሕግ ከለላ ሥር የሚገኙ ታራሚዎች በቀሰቀሱት ግርግር የእሳት ቃጠሎ ተነስቷል፤›› ይላል፡፡

  የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በድጋሚ ባወጣው መግለጫ በማረሚያ ቤቱ በተነሳው የእሳት አደጋ የ23 ሰዎች ማለፉን፣ ከዚህ ውስጥም 21 ሰዎች በአደጋው ወቅት በመረጋገጥ፣ በጭስ በመታፈንና በቃጠሎ መሞታቸውን ገልጿል፡፡ እነዚህ ሰዎች እስረኞች ይሁኑ አይሁኑ ግን የተናገረው ነገር የለም፡፡

  ነገር ግን የተቀሩት ሁለቱ ታራሚዎች መሆናቸውንና የማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ መገደላቸውን ገልጿል፡፡

  አዲስ ስታንዳርድ መጽሔት በአደጋው ወቅት በቦታው የነበረ አንድ የማረሚያ ቤቱ ባልደረባ ገልጾልኛል በማለት እንደዘገበው ከሆነ ግን፣ የማረሚያ ቤቱ ጥበቃዎች ከማማው ላይ ሆነው እንዲሁም ወደ ግቢው የዘለቁ የፖሊስ አባላት በቀጥታ እስረኞች ላይ ሲተኩሱ እንደነበር በፌስቡክ ገጹ አስነብቧል፡፡

  መንግሥት በሰጠው መግለጫ ግን በእሳት አደጋው ወቅት ታራሚዎችን ከቃጠሎና ከጭስ መታፈን ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጿል፡፡

  በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ዘጠኝ ታራሚዎችና የፖሊስ አባላት የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ፣ የሟቾችን አስከሬን ፖሊስ ተቀብሎ አስፈላጊውን ምርመራ እያከናወነ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

  አደጋው በደረሰ ማግሥት በርካታ የእስረኞች ቤተሰቦች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ የተገኙ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ይገልጻሉ፡፡

  ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መገንጠያ ከሆነው የአቃቂ ወንዝ ድልድይ አንስቶ እስከ ማረሚያ ቤቱ የሚወስደው መንገድ በእስረኛ ቤተሰቦች ተሞልቶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ‹‹ሁሉም የየራሱን ጩኸትና ብሶት እያሰማ ነበር፡፡ ነገር ግን በሥፍራው የነበሩ ፖሊሶች ለጠላት እንዲህ እያላችሁ ነው የምትሰጡን እያሉ ሲያዋክቡን ነበር፤›› ብለዋል አንድ ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ የእስረኛ ቤተሰብ፡፡

  ፖሊሶቹ ሁሉንም እያስወጡና ሞባይሎችን እየፈተሹ ከሥፍራው እንዳራቋቸው እኝሁ ግለሰብ ተናግረዋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙ እስረኞች ከ500 እንደማይበልጡና አብዛኞቹ እስረኞች ወደ ሸዋ ሮቢትና ዝዋይ ማረሚያ ቤቶች መዘዋወራቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

  ሪፖርተር አካባቢውን በጐበኘበት ወቅት የእግር መከላከያ የለበሱ በርካታ አድማ በታኝ ፖሊሶች ከማረሚያ ቤቱ ፊት ለፊት በሚገኙ የቂሊንጦ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥና ግቢ ውስጥ ሲዘዋወሩ ታይተዋል፡፡

  የሟቾች ማንነት የፊታችን ሐሙስ ጳጉሜን 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ማረሚያ ቤቱ በር ላይ እንደሚለጠፍ በሥፍራው ተገኝተው ለነበሩ ቤተሰቦች መገለጹን ለማወቅ ተችሏል፡፡

    

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...