Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአገር አቀፉ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አወዛጋቢ ጉዞ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት የግሉ ዘርፍ ሚና ወሳኝ መሆኑ ይታመናል፡፡ ያለ ግሉ ዘርፉ የአገር ዕድገትና የኢኮኖሚ ምጥቀት አይታሰብም፡፡  መንግሥትም የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው፣ በማኅበዊራውና በፖለቲካው መስክ የሚጫወተው ሚና ትልቅ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በዚህ ዕይታ የግል ዘርፉን የሚወክሉ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ሚና የዚያኑ ያህል ጠቃሚ ድርሻ ይይዛል፡፡

   በበርካታ አገሮች የሚገኙ ንግድ ምክር ቤቶች የሚወክሉትን የንግድ ኅብረተሰብ መብት ከማስከበር በላይ የአገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ ብዙ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የአባሎቻቸው ምርታማነት እንዲያድግ፣ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲያገኙ፣ አላሠራ ያሏቸውን ሕግጋት እየተከታተሉ እንዲሻሻሉ በማድረግ ትርጉም ያለው ሥራ እንደሚሠሩም ይታወቃል፡፡ የራሳቸውን ሥራ በመሥራት ሒደትም ቢሆን ጎን ለጎን ለአገር ጠቃሚ ሥራ ይሠራሉ፡፡ 

  የአገራቸው ምቹና የኢንቨስትመንት አመራጮች በማስተዋወቅ፣ የወጪ ንግድ እንዲያድግ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትም እንዲገባ በማድረግ በኩል የንግድ ምክር ቤቶች አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ የንግድ ምክር ቤቶች የግሉን ዘርፍ ከመደገፍና ከማሳደግ ጋር የተያያዙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያም እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት እንዲችሉ ታስቦ የንግድ ምክር ቤቶች ምሥረታ ዕውን የሆነው ከ70 ዓመታት በፊት ነው፡፡

  በወቅቱ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ተብሎ የተቋቋመው ንግድ ምክር ቤት የቅድመ ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የግሉን ዘርፍ በማስተባበር ከመንግሥት የበለጠ ይሠራ እንደነበር ነው፡፡ ወቅታዊና መጪው የኢኮኖሚ ገጽታ ምን ሊሆን እንደሚችል በመተንይ፣ የአገራዊ ገበያ ሁኔታን በማጥናት ነገን የሚተነብዩ ትንታኔዎች የሚያቀርበው ይኸው ንግድ ምክር ቤት ነበር፡፡ ትንታኔዎቹን የሚያመላክትበት የራሱን ጆርናል እያሳተመ ያሰራጭ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

  በአሁኑ ወቅት ግን የአገር አቀፉን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጨምሮ በክልል፣ በወረዳና በከተማ ደረጃ ነጋዴዎችን የሚወክሉ የንግድ ምክር ቤቶች ተደራጅተዋል፡፡ እነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታዩ እንዲሁም ቀድሞ ይታወቁበት ከነበረው መገለጫቸው አኳያ ሲቃኙ በተቃራኒው የሚታዩ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የንግድና የዘርፍ ምክር ቤቶች አባላት ይህንኑ ይገልጻሉ፡፡ በአጠቃላይ ክንውናቸው ሲታዩም ከቀደመው እንቅስቃሴያቸው ይልቅ በአሁኑ ወቅት እየተዳከሙ መምጣታቸው መነገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ሞቅ ያሉ ክርክሮችና ጥናታዊ ጽሑፎች እየወጡ መንግሥትን የሚሞግቱባቸው መድረኮች እየተቀዛቀዙ መምጣታቸው እየታየ ነው፡፡

  በተለይ የንግድ ምክር ቤቶች በአዲስ እንዲደራጁ የሚያስገድደው አዋጅ ቁጥር 341/95 ከወጣ ወዲህ ያለው ሒደት ንግድ ምክር ቤቶች በስያሜያቸው ወይም በወከሉት የንግድ ኅብረተሰብ ፍላጎት ልክ እየሠሩ ባለመሆናቸውም ትችቶች ይቀርብባቸዋል፡፡

   እየተለወጠ ከሚመጣው ኢኮኖሚ ጋር የተጣጣመ እንቅስቃሴ አያደርጉም፣ ፈዘዋል በማለት የሚተቿቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ በአንፃራዊ ደረጃ የተሻለ አቋም አላቸው ከሚባሉት መካከል የአዲስ አበባ የንግድ ምክር ቤትን ጨምሮ ከጥቂቶች በቀር አብዛኖቹ ምክር ቤቶች እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ማምጣት የተሳናቸው ሆነዋል እየተባሉ ይታማሉ፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ጉዟቸው ከሚሠሩት ይልቅ ሰዎችን ወደ አመራር ለማምጣት የሚያደርጉት ፉክቻ ገዝፎ የሚታይባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው፡፡

  በተለይ ኢንዱስትሪ ቀመስ የሆኑ ተቋማትንና ኩባንያዎችን በማሰባሰብ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተብለው ለብቻቸው የሚንቀሳቀሱ፣ እስከ አገር አቀፍ ደረጃም ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጋር ተጣምረው የሚሠሩ የዘርፍ ምክር ቤቶች ለራሳቸውም ሆነ ለንግድ ምክር ቤቶች መልፈስፈስ ምክንያት ሆነዋል የሚሉ ስሞታዎች ይቀርቡባቸዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የዘርፍ ምክር ቤቶች ለማደግ ሲጥሩ ተፅዕኖ አለባቸው የሚሉም አሉ፡፡ ኢንዱስትሪ ቀመስ ተቋማትን ያሰባሰቡት የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ያለፉት አሥር ዓመታት ጉዟቸው ሲታይም ከነበሩበት ደረጃ ሻል ብለው ለመገኘት ፈቅ ለማለት እንዳልቻሉ ይጠቀሳል፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በተሰጣቸው ዕድል መጠቀም እንዳልቻሉም ይታማሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በዘርፍ ምክር ቤቶች የተሰባሰቡ አባላትም በዘርፍ ምክር ቤት ውስጥ መካተት ያለባቸውን ወሳኝ ኢንዱስትሪ ቀመስ ተቋማትን የዘነጉ፣ ያላካተቱ ሆነው መዝለቃቸውና የዘርፍ ምክር ቤቶችን የሙጥኝ ብለው በአመራርነት የያዙ ግለሰቦችም እንደታሰበው የአምራች ኢንዱስትሪው ጠንካራ ተወካይ እንዳይኖረው፣ በአጠቃላይም ለንግድና ለዘርፍ ማኅበራት መዳከም ምክንያት ናቸው እየተባሉ መተቸታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱ አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠንካራ እየሆነ መጥቷል ይላሉ፡፡ ከ21 አቻ ማኅበራት ጋር ትስስር መፍጠሩን፣ ቀድሞ የ870 ብር የነበረው የካፒታል አቅሙን አሁን ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለማካበት የቻለበት ደረጃ የደረሰ መሆኑን በመግለጽ፣ ዘርፍ ማኅበሩ እየተዳከመ ነው የሚለውን አስተያየት አይቀበሉትም፡፡

  የዘርፍ ምክር ቤቶች አነሳስና የቁልቁሊት ጉዞ

  አምራች ኢንዱስትሪዎች ራሳቸውን ችለው በዘርፍ ምክር ቤትና በንግድ ምክር ቤት በኩል እንዲደራጁ የተፈቀደው፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማጎልበትና ወደ ኢንዱስትሪ ተኮር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ነው፡፡

  በዚህ መነሻነት የመጀመርያው አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተመሠረተው በ1999 ዓ.ም. ነበር፡፡ የዘርፍ ምክር ቤቶች ከወረዳ እስከ ላይ ባለው መዋቅር እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡ በ1999 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲመሠረት መሥራች የነበሩ አባላትም የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የመድኃኒትና ሕክምና መገልገያዎች የዘርፍ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ጎማና ፕላስቲክ አምራቾች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የወተት ተዋጽኦ አምራቾች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዕቃዎች አምራቾች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የጤናና የውበት መጠበቂያ አምራቾች ማኅበርና የኢትዮጵያ ማርና ሰም ላኪዎች ማኅበር ነበሩ፡፡

  እነዚህን አምራች ድርጅቶች የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤትን መሥርተው ከንግድና አገልግሎት ዘርፍ ጋር ተቀላቅለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ፈጥረዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ትላልቅ ማኅበራት በአሁኑ ወቅት ውክልናቸው በዘርፍ ማኅበራት ውስጥ አይታይም፡፡ በወረዳ፣ በክልልና በከተማ ደረጃ አዋጁን ተንተርሰው የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ተቋቁመዋል፡፡ ከአዋጁ መንፈስ ለመረዳት እንደሚቻለው በክልል፣ በወረዳና በከተማ ደረጃ መቋቋም ያለባቸው የዘርፍ ምክር ቤቶች ብዛት 52 መሆኑ ይታያል፡፡

  ይሁንና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አቋም ደካማ ስለመሆኑ የሚገልጹ ወገኖች፣ በሚያከናውኗቸው ተግባራት ውስጥ በተለይ በፋይናንስና በአገልግሎት አሰጣጣቸው የደከሙ ስለመሆናቸው ዓመታዊ ሪፖርታቸውን መጥቀስ ይበቃል፡፡ ሆኖም የዘርፍ ማኅበራቱ ያቀፏቸው አባላት ቁጥር ከንግዱና ከአገልግሎት ዘርፎቹ የበለጡ ሆነው ቢገኙም አሉን ባሏቸው አባላት ልክ አቅማቸውን አላጎለበቱም፡፡

  ከ52 በላይ የአምራች ዘርፎችን በተለያየ መንገድ ለአባልነት ማቀፍ የሚገባው የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የስሙን ያህል የገዘፈ ላለመሆኑ አንዱ መገለጫው፣ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ምክር ቤቱን የሚመሩ የቦርድ አባላት ውክልና እንዲሁም ሊካተቱ የሚገባቸውን ዘርፎች ያላካተተ ሆኖ መቆየቱ ብቻ ሳይሆን፣ የአመራር ቅብብሎሽም የሌለው ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡

  እሑድ ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ስምንተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በ2008 በጀት ዓመት አከናወንኳቸው ስላላቸው ጉዳዮች ያቀረበው ሪፖርት ይጠቀሳል፡፡

  የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱና የ2008 በጀት ዓመት ሪፖርቱ

  በአገሪቱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳለው የሚነገርለት ይህ የዘርፍ ምክር ቤት፣ የ2008 በጀት ዓመት ሪፖርት በአሥር የተከፋፈሉ አንቀጾችን አካቷል፡፡ የሪፖርቱ መንደርደሪያም በ2008 ዓ.ም. የምክር ቤቱ ዳይሬክተሮች ቦርድ ስምንት ጊዜ መደበኛና ሁለት ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባዎችን ማካሄዱን በማተት ይጀምራል፡፡ የሰባት አገሮች የንግድ ልዑካንን ተቀብሎ ማነጋገሩን፣ ከካናዳ፣ ከቱርክና ከጣልያን አቻ ማኅበራት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስለመፈራረሙም ይገልጻል፡፡  የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ በቋሚ አባልነት የተወከለባቸው የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች መኖራቸውን በመግለጽ ይቀጥልና ምክር ቤቱ ከተረከባቸው ተቋማት መካከል አንዱ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር መሆኑን ያሳያል፡፡

  በኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ምክር ቤት አባልነት፣ በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የፀረ ሙስና ጥምረት በምክትል ሰብሳቢነት፣ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪነት ብሔራዊ ምክር ቤትና የትምህርት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ተቋምም የቦርድ አባል በመሆን እየሠራ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

  ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት አኳያ የተገበራቸውን ሥራዎች በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት፣ ከተለያዩ አገሮች የመጡ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንዲሁም የንግድ ትርዒቶችን እንዲጠቀሙባቸው ለአባላት በየጊዜው መረጃ እየተላለፈ ይገኛል ይላል፡፡ ለምሳሌ ወደ ህንድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በተደረገ ጉዞ ሦስት የምክር ቤቶች አባላት በዕድሉ ተጠቅመዋል፡፡ አንዱ የንግድ ትርዒት ማዘጋጀቱንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

  በውጭ አገር የተደረጉ የቢዝነስ የአቻ ለአቻ ግንኙነትን በተመለከተም ወደ አራት አገሮች ሰባት ጉዞዎች ተደርገዋል፡፡ ከ85 በላይ ሰዎችም በዘርፍ ማኅበሩ አማካይነት በኤግዚቢሽንና በጉዞ ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን ያስረዳል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ከሪፖርቱ ውጭ ስለተከናወኑ ሥራዎች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ገብረ ሕይወት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ገልጸዋል፡፡

  ኦዲት ሪፖርት

  በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት የዘርፉ ምክር ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በፕሬዚዳንት መቅረብ ሲኖርበት፣ በዋና ጸሐፊው ከቀረበ በኋላ በምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በውጭ ኦዲተር የበጀት ዓመቱ የሒሳብ ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባዔው መቅረብ ይጠበቅበት ነበር፡፡ በየትኛውም ማኅበር ከሕግ አኳያም እንደሚደረገው በውጭ ኦዲተር የተረጋገጠ የኦዲት ሪፖርት የሚቀርበውና ስላጠናቀረው ኦዲት ማብራሪያ የሚሰጠው ኦዲቱን የሠራው ኦዲተር ድርጅት ተወካይ ቢሆንም፣ በዕለቱ ኦዲተሩ ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ ታትሞ ለጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊዎች የተሰጠ ቢሆንም፣ የኦዲተሩ ሐሳብ አልተንፀባረቀም፡፡ ዋና ጸሐፊም ‹‹ኦዲተሩ እስካሁን ጉባዔው ውስጥ ነበር፡፡ አስቸኳይ ጉዳይ ስላለው በመሄዱ ነው፤›› የሚል ምክንያት አቅርበው ታልፏል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውም ሪፖርቱን በጭብጨባ አጽድቋል፡፡

  በዕለቱ የታየው አንዱ ክፍተት ይህ ሲሆን፣ የሒሳብ ሪፖርቱ የሚያሳየውም አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ የፋይናንስ እንቅስቃሴ፣ ሀብቱና አጠቃላይ የወጪና ገቢው ይዘት ሲታይ ደካማ መሆኑን ነው፡፡

  በሪፖርቱ መሠረት የዘርፍ ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ 2.5 ሚሊዮን ብር ገቢ አሰባስቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2.1 ሚሊዮን ብሩን ወጪ ማድረጉንም ይገልጻል፡፡ የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቋሚ ሀብት ነው ተብሎ የተገለጸው 110 ሺሕ ብር ነው፡፡ ዘጠኝ ዓመታት የቆየ፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ዋና ተወካይ ያካበተው የሀብት መጠን 110 ሺሕ ብር ብቻ መሆኑ አስገራሚ ቢሆንም፣ ከቢሮ ቁሳቁስ ውጭ ምንም ሀብት ያላፈራ ስለመሆኑ በፋይናንስ ሪፖርቱ ሰፍሯል፡፡ ወጪ ተብሎ በተጠቀሰው ሰንጠረዥ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ለሰባት አባላት ለቪዛ ማስፈጸሚያና ለመሳሰሉት የዋለ ነው፡፡  አብዛኛው ወጪም ለውጭ ጉዞ፣ ለክልልና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አቶ ገብረ ሕይወት ግን አሁን የደረሰበት የፋይናንስ አቅም ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

  ጠቅላላ ጉባዔውና ታይተዋል የተባሉ የሕግ ጥሰቶች

  እንዲህ ባለው መንገድ የተካሄው ጠቅላላ ጉባዔ፣ የኦዲት ሪፖርቱን ያፀደቀ ሲሆን፣ ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ወገኖች ግን ምርጫውና ጠቅላላ ጉባዔው አካሄድ የሕግ ጥሰት የታየበት ስለመሆኑ ከጠቅላላ ጉባዔው በፊትም ጀምሮ ሲገልጹ ነበር፡፡

  በተለይ ውክልናን በተመለከተ የሚደመጡ ቅሬታዎች በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የጣሰ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ የአማራ ክልል ዘርፍ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ከጠቅላላ ጉባዔ ዕውቅና ውጭ በጥቂት ቦርድ አባላት ውሳኔ ምክንያት በአገር አቀፍ ስብሰባ ላይ እንዳይወከሉ ሲደረግ ዝም መባሉ አንዱ የሕግ ጥሰት ነው ተብሏል፡፡

  ከአማራ ዘርፍ ምክር ቤት የተወከሉት ተወካዮች ሕጉን ጠብቀው በጉባዔው እንዳልተወከሉ የአገር አቀፉ ዘርፍ ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል አቶ ዳንኤል ካሳሁን አሳውቀው ነበር፡፡ በመሆኑም ምክር ቤቱ ለጥያቄያቸው ምላሽ ሳይሰጥ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄዱ ትክክል እንዳልነበር ተገልጿል፡፡

  ጠቅላላ ጉባዔው ሊያሟላቸው የሚገቡ ሌሎች ሕጋዊ ጉዳዮችንም አላገናዘበም ተብሎ ተተችቷል፡፡  የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ከስብሰባው መካሄድ ቀደም ብሎ ሥጋቱን በደብዳቤ ገልጿል፡፡ አገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባዔ የሚካሄደው ሁሉም አባል ዘርፍ ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ካካሄዱ በኋላ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ሳያካሂዱ አገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባዔ መካሄዱ አግባብ ያለመሆኑን ደብዳቤው ጠቁሟል፡፡

  የተወሰኑ የክልልና የከተማ ዘርፍ ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ሳያካሂዱና ምርጫ ሳያከናውኑ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዲወከሉ ተደርጓል፡፡ መወከል ብቻ ሳይሆን፣ ብሔራዊ ዘርፍ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት እንዲመሩ ጭምር መመረጣቸው ትልቁ ስህተት ስለመሆኑ በጠቅላላ ጉባዔው የተሳተፉ አባላት ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ ዘርፍ ምክር ቤቶች የራሳቸውን ምርጫ ሳያካሂዱ ለጠቅላላ ጉባዔ መጠራታቸው በምሳሌት ተጠቅሷል፡፡

  እንደ ተሳታፊዎች ገለጻ፣ ጠቅላላ ጉባዔው 13 ትላልቅ የዘርፍ ማኅበራት ያልተከወሉበት ነበር፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው በምን ያህል ተወካዮች እንደሚወከል ግልጽ አሠራር አልነበረም፡፡ የደቡብ ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ፈለቀ፣ የጠቅላላ ጉባዔው የውክልና ቁጥር በጠቅላላ ጉባዔ የሚፀድቅ ቢሆንም፣ በእሑዱ ጠቅላላ ጉባዔ የጉባዔተኛው ውክልና በ120 ወንበር የተወሰነ ነው መባሉ ከጠቅላላ ጉባዔው ዕውቅና ውጭ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ በጠቅላላ ጉባዔው የፀደቀ  አይደለም፡፡ የውክልና ድልድሉም ቢሆን ግልጽ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ የአገር አቀፍ ዘርፍ ማኅበራት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን በማተናገዱ ሕጋዊ ነው ለማለት አስቸጋሪ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

  በዕለቱ የተደረገው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ የገለጹት አቶ ገብረ ሕይወት፣ ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት ያልተፈጸመበት እንደሆነም ተከራክረዋል፡፡ የውክልና ቀመሩም ቢሆን በፊት 70 የነበረው ዘንድሮ 120 ደርሷል ይህም በቦርድ የተወሰነ ነው ብለዋል፡፡

  ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ በአመራርነት ከተመረጡት ውስጥ አንዳንዶቹ በትክክል ከታች የዘርፍ ምክር ቤቶች ስለመወከላቸው እርግጠኛ መሆን ያለመቻሉ ነበር፡፡ ለአራተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡ አቶ ገብረ ሕይወት የውክልናቸው ጉዳይ ያጠራጥራል ከተባሉት ተመራጮች መካከል ናቸው፡፡ ቀደም ብሎ የትግራይ ክልልና የመGለ ከተማ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ስለነበሩ ተወክለው  ተመርጠዋል፡፡ አሁን ግን ሁለቱም ምክር ቤቶች በአመራር ላይ የሌሉ በመሆኑ እንዴት ተወከሉ? የሚለው ጥያቄ ተሰዝሯል፡፡ በትግራይ ክልል ለዘርፍ ምክር ቤት በአባልነት ሊያሳትፋቸው የሚያስችላቸው ድርጅት ወይም ኩባንያ የላቸውም ተብለው ይብጠለጠላሉ፡፡ እንዲህ ያለውን የከረረ ትችት አቶ ገብረ ሕይወት ምላሽ የሚሰጡበት የክልሉን ዘርፍ ምክር ቤት ወሳኔ ወይም ሉዓላዊነት የሚፃረር ነው በማለት ነው፡፡ ‹‹ለፕሬዚዳንትነት እንድወዳደርና የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ተወካይ እንድሆን የላከኝ የትግራይ ዘርፍ ምክር ቤት በመሆኑ የተሰጠው አስተያየት ተቀባይነት እንደሌለው ያመለክታል፤›› ብለዋል፡፡  

  ጠቅላላ ጉባዔው ሕግን ተጋፍቷል የተባለበት ሌላው ምክንያት፣ የከተማ ወይም የክልል ዘርፍ ምክር ቤቶችን እንዲመሩ ስለመወከላቸው ሳያረጋግጡ በቀጥታ መምጣታቸው የሕግ ጥሰት የታየበት ነው መባሉ ነው፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የእሑዱ ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት የጻፈው ደብዳቤም ይህንኑ የሚያመላክት ነበር፡፡

  በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት የተጻፈው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ የሚያሳስበው መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞውን ይጀመራል፡፡

  ጠቅላላ ጉባዔውና የምርጫው ሒደት በሁለት ዓበይት ጉዳዮች ምክንያት አሳሳቢ ያለው ምክር ቤቱ፣ ጠቅላላ ጉባዔውና የምርጫው ሒደት ያሳስበኛል ያለበት አንዱ ምክንያት የአማራ ክልል የዘርፉ ምክር ቤት ውስጥ የተወከለበት አግባብ ከአዋጅ ውጭ የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡

  በዚህ ምክንያት የሚታየው ውዝግብ እልባት ያላገኘ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትንም ሆነ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን የወደፊት ሥራዎች የሚያውኩ ስለመሆናቸውም የፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

  ከዚህም ባሻገር በአዋጁና በመመርያው መሠረት የዳይሬክተሮች ቦርድ የሥራ ዘመን ሁለት ዓመት መሆኑ እየተጠቀሰ፣ ለሚቀጥለው እርከን የሥራ አመራር ቦርድ ምርጫ የሚቀርቡ አባላት በየዘርፍ ምክር ቤቶቻቸው በኩል ምርጫ ያካሄዱና በጠቅላላ ጉባዔ በአባልነት የሚወከሉ መሆን እንዳለባቸው በማያሻማ ሁኔታ ስለመደንገጉ ደብዳቤው ይገልጻል፡፡

  ይህ ሆኖ ሳለ የተወሰኑ የከተሞችና የክልሎች ማኅበራት ይህንን ሒደት ያልጠበቁ፣ ለማጠናቀቅም በሒደት ላይ መሆናቸው እየታወቀ አገር አቀፉ የዘርፍ ምክር ቤት ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድና ትክክለኛ ያልሆኑ ተወካዮችን በምርጫ ማሳተፍ አዋጅና ደንብ መጣስ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት አስገንዝቧል፡፡  

  ይህን ጥሰት ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እንዲሠራ ፕሬዚዳንቱ አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፣ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ ገልጸው ነበር፡፡ ይሁንና የዘርፍ ምክር ቤቱ ይህንን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በማለት ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ በተደረገው ምርጫም የጠቅላላ ጉባዔ ሳይጠሩ በቀድሞ ውክልናቸው ብቻ የቦርድ አባላት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ይህ ግልጽ  የሕግ ጥሰት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትም ዕርምጃ ሊወስድ ይችላል እየተባለ ነው፡፡ ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሄዱ አባል የዘርፍ ምክር ቤቶች መወከል አልነበረባቸውም የሚለውን ጉዳይ ያልተቀበሉት አቶ ገብረ ሕይወት፣ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከንግዱ ጋር ተዋህዶ ጠቅላላ ጉባዔውን የሚያካሂድ በመሆኑ ባያካሂድም ተወካዩን ልኳል በማለት ሞግተዋል፡፡

  የጋምቤላ ዘርፍ ምክር ቤት ገና በመደራጀት ላይ ነው፡፡ የድሬዳዋም በራሳቸው ችግር ያልተወከሉ ናቸው ብለዋል፡፡ የአፋርም ቢሆን ባለው አቅም ጉባዔውን አድርገው የመጡ ናቸው በማለት የተሰነዘረውን ወቀሳ አልቀበልም ብለዋል፡፡ በተደጋጋሚ መመረጡ አግባብ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ሲገልጹም፣ የመራጩ ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡

  መምረጥና መመረጥ ዴሞክራሲያዊ መብት እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ገብረ ሕይወት፣ በብቸኝነት የተወዳደሩት ሌሎች ዕጩዎች መቅረብ ባለመቻላቸው እንደሆነ፣ እሳቸውም ዕጩ ሆነው በመቅረብ የተመረጡት ‹‹የተጀመረውን ሥራ አስጨርስልን ተብዬ ከአባላት በመጠየቄ ነው፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹መራጩ ከፈለገ መምረጥ ይችላል፡፡››

  የደቡብ ዘርፍ ምክር ቤት ጉባዔ ረግጦ መውጣት

  የእሑዱ የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ካስተናገዳቸው ክስተቶች መካከል በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የተወከሉት የደቡብ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው መውጣት አንዱ ነበር፡፡

  የደቡብ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ስብሰባውን ረግጠው ለመውጣታቸው አንዱ ምክንያት፣ በዕለቱ ለውይይት የቀረበው አዲስ የመተዳደሪያ ደንብና የአባላት ቁጥር ውክልናን በተመለከተ ያቀረበው ሐሳብ ነው፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው የሚወከለው አባል ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ባላቸው አባል፣ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባላቸው ወንበር ልክ የሚወሰን ቢሆንም፣ የውክልና ቁጥር ድልድሉ ግን ከጠቅላላ ጉባዔ ውክልና ውጭ ነው፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት የደቡብ ዘርፍ ምክር ቤት 28 ሺሕ አባላት ያሉትና በአባላቱ ልክ ዓመታዊ መዋጮውን የከፈለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ግን የደቡብ ውክልና በዘጠኝ ወንበር ብቻ እንዲወሰን ማድረጉ አላግባብ አልነበረም ተብሎ ክርክር ተነስቷል፡፡

  ይህ አሠራር ትክክል አለመሆኑን የደቡብ ክልል ዘርፍ ምክር ቤት አመራሮች ጠቅሰው፣ አሠራሩ ሕጋዊ ጥሰት መሆኑን በመግለጽ የተቃውሞ ድምፅ በማሰማት ብቻም ሳይወሰኑ ጠቅላላ ጉባዔውን ረግጠው ወጥተዋል፡፡ በዕለቱ እንዲፀድቅ ተፈልጎ የነበረው የመተዳደሪያ ደንብ ረቂቅም ያልተመከረበት በመሆኑ፣ ሊፀድቅ አይገባም ብለዋል፡፡ በዚህ ተቃውሞ ምክንያትም ጠቅላላ ጉባው ሳያፀድቀው ቀርቷል፡፡ የደቡብ ዘርፍ ምክር ቤት ተቋውሞ አግባብ አልነበረም ያሉት አቶ ገብረ ሕይወት፣ የውክልና መጠኑን ከጠቅላላ ጉባዔ በፊት ማቅረብ ነበረበት ብለዋል፡፡

  የዘርፍ ምክር ቤቱ አባላት ቁጥርና ምስጢር

  በዕለቱ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት በዓመታዊ ሪፖርቱ ውስጥ ያልተካተተው ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምን ያህል አባላት አሉት የሚለው ነው፡፡

  የጠቅላላ ጉባዔው አንዳንድ ተሳታፊዎችም ይህንኑ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን ምላሽ ሳይሰጥበት ታልፏል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በዕለቱ ለሚካሄደው ምርጫ የውክልና ጉዳይን እንደፈተለገ ለመዘርዘር ነው የሚል ስሞታ አስከትሏል፡፡ የአባላት ብዛት ምስጢር ሆኖ መቆየቱም ኋላ ላይ ተቃውሞ እንዲነሳ ሰበብ ሆኗል፡፡ በቂ ማብራሪያ ባይሰጥበትም አከራሪ ነበር፡፡ አቶ ገብረ ሕይወት ግን አባሎቻችን ከ110 ሺሕ በላይ ይደርሳሉ በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  ምርጫውና ውጤቱ

  የዘርፉ ምክር ቤት ምስጢር አድርጎ ባቆየው የውክልና ቀመር መሠረት ምርጫው እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ በዕለቱ የዘርፍ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የቀረቡት ብቸኛው ተወዳዳሪ አቶ ገብረ ሕይወት ናቸው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገ ምርጫም በብቸኝነት ቀርበው ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ አሁንም ያለተወዳዳሪ ተወዳድረው አሸናፊ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ይህም አቶ ገብረ ሕይወት ለአራት ተከታታይ የምርጫ ዘመን መመረጣቸውና ስምንት ዓመት በፕሬዚዳንትነት መቆየታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት የቀረቡትም ዕጩ ያለተወዳዳሪ የቀረቡ ናቸው፡፡ ለቦርድ አባልነት በተደረገው ምርጫም አሸናፊ የሆኑት አብዛኛዎቹ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ ያገለገሉ ናቸው፡፡

  ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ወገኖች፣ በምርጫው ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ የተመረጡት አመራሮች በቦርድ አባልነት ለዓመታት ያገለገሉ ናቸው በማለት ወርፈዋቸዋል፡፡ የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ግን ከሁለት ጊዜ ምርጫ በላይ ማገልገል እንደሌለባቸው የሚደነግግ ነው፡፡ ይሁንና አቶ ገብረ ሕይወትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አመራሮች ለሦስትና ለአራት የምርጫ ዘመን ተወዳድረዋል፤ መምራታቸውንም ቀጥለዋል፡፡ አቶ ገብረ ሕይወት ግን የተጠቀሰውን መተዳደሪያ ደንብ ስለመኖሩም አያውቁም፡፡

   ‹‹አለ የሚባለውን የመተዳደሪያ ደንብ አናውቅም፡፡ ተደብቆ የቆየ ነው፡፡  በእጃችን ላይ ያለው መተዳደሪያ ደንብ የሥልጣን ዘመኑን የሚገድብ አይደለም፤›› ከማለታቸውም በላይ፣ ይህንን አስተያየት የሚሰጡት ሰዎች ራሳቸው በተደጋጋሚ ተመርጠው ሲሠሩበት ነበር በማለት መልሰው ይወቅሷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የጻፈው ደብዳቤም ራሱን እንጂ እኛን የሚመለከት አይደለም ብለዋል፡፡

  ለወደፊቱስ ምን ይሆናል?

  ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰነዘሩት አስተያየቶች፣ የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ሕጋዊ መንገዱን ያልተከተላ ነው የሚሉ ትችቶችን ያዘሉ ናቸው፡፡ ሁሉንም ንግድና ዘርፍ ማኅበራትን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የጠቅላላ ጉባዔው አካሄድ የሚያሳስበው መሆኑን ቀድሞ የገለጸ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ጉባዔው በኋላ ለታየው ችግር ነገሩን በመመርመር ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

  አቶ አሸናፊ እንደገለጹት፣ የጠቅላላ ጉባዔውና የምርጫ ሒደቱ በአጠቃላይ የሕግ ጥሰት ያለበት ስለሆነ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት አሳውቀዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅ መሻሻል ሌላው መፍትሔ መሆኑን የገለጹ አባላት ደግሞ፣ ተቋማት መፈተሽ አለባቸው በማለት እንዲመረመሩ ይጠይቃሉ፡፡ ወደ ፍትሕ አካላት እንሄዳለን ያሉም አሉ፡፡ አቶ ገብረ ሕይወት ግን ‹‹ሁሉም አሠራር በመረጃ የተደገፈና በሕግ አግባብ የሄድን በመሆኑ ምንም ሥጋት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡ አሁን የተፈጠረው ቀውስ ግን በብሔራዊ ምክር ቤቱ ምርጫ ላይ ሥጋት እንዳጠላበት እየተነገረ ነው፡፡ ከሰሞኑ የሚካሄደው ጉባዔ ምን ይዞ እንደሚመጣ ከወዲሁ ጉጉት አሳድሯል፡፡

   

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች