Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልየአዕምሮ ሕሙማኑ የጥበብ ሥራ

  የአዕምሮ ሕሙማኑ የጥበብ ሥራ

  ቀን:

  አዳራሹ በአዕምሮ ሐኪሞችና የሥነ ጥበብ አድናቂዎች ተሞልቷል፡፡ ዐውደ ርዕዩ የታዋቂ ሠዓሊ ወይም የሥነ ጥበብ ተማሪዎች ባይሆንም ዐውደ ርዕዩ በይፋ እስኪከፈት ታዳሚዎቹ በጉጉት ይጠብቁ ነበር፡፡ ሐኪሞቹና ዐውደ ርዕዩን ያስተባበሩ ሁለት ሠዓሊያን ንግግር ካደረጉ በኋላ ተመልካቾች በአዳራሹ ይዘዋወሩ ጀመር፡፡ ብዙዎቹ ተመልካቾች በሚያዩት ነገር ተገርመው ነበር፡፡ ሥዕሎቹ የተሠሩት በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒቴል ታካሚዎች ነበር፡፡

  ከሥዕሎቹ መካከል በደማቅ ቀለማት፣ በእስራስና በእስኪርቢቶ ወረቀት ላይ የተሠሩ ይገኙበታል፡፡ ታካሚዎቹ ስሜታቸውን በሥዕልና በቃላትም ገልጸው ነበር፡፡ ለአዕምሮ ሕሙማን ዝቅተኛ አመለካከት ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለአዕምሮ ሕሙማን የሥነ ጥበብ ሥራዎች ቦታ ማግኝት ይከብዳል፡፡ በዐውደ ርዕዩ የተገኙ ታዳሚዎች ለሕሙማኑ የሥነ ጥበብ ሕክምና (አርት ቴራፒ) እንደተሰጣቸው ተገልጾላቸው ነበር፡፡

  ይህ ዐውደ ርዕይ ‹‹በመስመር ውስጥ›› የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ በሒልተን አዲስ ሆቴል ከተካሄደ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ሁለት ሠዓሊዎች በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት የሥነ ጥበብ ሥልጠና ከሰጡ በኋላ የታካሚዎቹ ሥራዎች ለሕዝብ የቀረበበት ነበር፡፡

  የዐውደ ርዕዩ ሁለተኛ ክፍል ‹‹በመስመር ውስጥ 2›› በሚል ተዘጋጅቶ የፊታችን ነሐሴ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ለዕይታ ይበቃል፡፡ ከዐውደ ርዕዩ ጎን ለጎን የገቢ ማሰባሰቢያ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ይካሄዳል፡፡

  ለታካሚዎቹ የሥነ ጥበብ ሥልጠና ከሰጡት አንዱ ሠዓሊ ይድነቃቸው ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ‹‹በመስመር ውስጥ›› የተሰኘው ዝግጅት የመጀመርያው እንቅስቃሴ ገቢ ማሰባሰቢያ ነው፡፡ ነሐሴ 20 እና 21 በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ 1,000 ባዶ ሸራዎች ይቀርባሉ፡፡ በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ስለ አዕምሮ ጤና ትምህርት ይሰጣቸውና ከሸራዎቹ በአንዱ ላይ ሐሳባቸውን በሥዕል ያሰፍራሉ፡፡ ከዛም ሸራውን በ400 ብር ይገዛሉ፡፡ በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ የሚገኙ ሰዎች በሒልተኑ ዐውደ ርዕይ ላይ በአዕምሮ ሕሙማኑ የተሠሩ ሥዕሎችንም ተመልክተው ስለ ታካሚዎቹ እንዲረዱ ይደረጋል፡፡

  ሠዓሊው እንደሚለው፣ የገቢ ማሰባሰቢያው የአርት ቴራፒ የሚሰጥበትን ማዕከል ከማጠናከር ጎን ለጎን ደግሞ ኅብረተሰቡ ስለ አዕምሮ  ሕሙማን ያለውን የተዛባ አመለካከት እንዲለወጥ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ‹‹የአርት ቴራፒ ወጪ ብዙ ነው፡፡ አሁን እየተንቀሳቀስን ያለነው በበጎ ፈቃደኞች ነው፡፡ ማዕከሉን ለማጠናከርና ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ ግለሰቦችን ትኩረት ለመሳብም አስበናል፤›› ይላል፡፡

  የገቢ ማሰባሰቢያውን በሆስፒታሉ ውስጥ ያዘጋጁት በአዕምሮ ሕሙማንና በኅብረተሰቡ መካከል ያለውን ግንብ ለማፍረስም ነው፡፡ ስለ አዕምሮ ሕመም ያለው የግንዛቤ ውስንነት ሕሙማኑን ማግለልና መፍራትን ሲያስከትል ይስተዋላል፡፡ ይድነቃቸው ‹‹አማኑኤል ሆስፒታልን ብዙ ሰው ይፈራዋል፡፡ ሥዕልን እንደ ሚዲያ በመጠቀምና ስለ ሕመሙ መረጃ በመስጠት ለውጥ ማመጣት ይቻላል፤›› ይላል፡፡

  በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ የሚገኙ ሰዎች በየግላቸው ከሚሥሉት በተጨማሪ በአንድ ሸራ ላይ ከአዕምሮ ሕሙማን ጋር በኅብረት ይሥላሉ፡፡ ይኽም መቀራረብን እንደሚፈጥር ያምናል፡፡

  ቀጣዩ መርሐ ግብር የሚካሄደው ነሐሴ 26 ቀን ሲሆን፣ ከወራት በፊት በሒልተን ለዕይታ የበቁት ሥዕሎች በድጋሚ ይታያሉ፡፡ ከሕሙማኑ ሥዕሎች በተጨማሪ ለአዕምሮ ሕሙማኑ የአርት ቴራፒ በበጎ ፍቃደኝነት የሰጡ ሠዓሊዎች ሥራዎችም ይቀርባሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከ30 በላይ ሠዓሊዎች ለአዕምሮ ሕሙማኑ የበጎ ፍቃድ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ በሥልጠናው ወቅት ሠዓሊዎችና ታካሚዎቹ በኅብረት የሠሯቸው ሥዕሎችም ነበሩ፡፡ ሠዓሊው እንደሚለው፣ እነዚህ ሥዕሎች በዐውደ ርዕዩ ቀርበው ይሸጡና ገቢው ለማዕከሉ ይሆናል፡፡ ‹‹ገቢው አርት ቴራፒ የሚሰጡ ሠዓሊያንን ለማሠልጠን፣ ለሸራና ለቀለም እንዲሁም ለሌሎች ወጪዎች ይውላል፤›› ሲልም ገልጿል፡፡

  አርት ቴራፒ ሥነ ጥበብ፣ ሙዚቃና ሌሎችም ጥበባዊ ሥራዎችን በመጠቀም ለአዕምሮ ሕሙማን የሚሰጥ ሕክምና ነው፡፡ ሕሙማን ጥበባዊ ሥራዎች እንዲያዘጋጁ በማድረግ ወይም በሌሎች የተሠሩ የኪነ ጥበብ ውጤቶችን ሕሙማንን ለማከም መጠቀም ይቻላል፡፡ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ እንደተጀመረ የሚነገርለት አርት ቴራፒ በአዕምሮ ሕክምናው ዘርፍ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ሕክምናው ውጤታማ መሆኑም በተለያዩ ባለሙያዎች ተመስክሮለታል፡፡

  በአገራችንም በተለያየ ዘርፍ የአርት ቴራፒ ሙከራዎች ይስተዋላሉ፡፡ ከነዚህም የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንቅስቃሴ ይጠቀሳል፡፡ ለታካሚዎች በሚሰጠው ሕክምና ጥበባትን ከመጨመር ጎን ለጎን በሆስፒታሉ ለሚገኙ ሕሙማን የተለያዩ ጥበባዊ ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡ በቅርቡ ዕውቁን ድምጻዊ መሐሙድ አህሙድ ጨምሮ በርካታ አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን የተገኙበት የሙዚቃ ኮንሰርት በሆስፒታሉ ተካሂዶ ነበር፡፡ በሆስፒታሉ የሥነ ጽሑፍና የቴአትር መርሐ ግብሮችም ይቀርባሉ፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...