Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ የባንክና የኢንሹራንስ ባለአክሲዮኖች ጉዳይ በድጋሚ እንዲታይ ተጠየቀ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በባንክ፣ በኢንሹራንስና በማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ አክሲዮን የገዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የትርፍ ክፍፍል እንዲታገድና ባለአክሲዮኖች ከሆኑም ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ በድጋሚ እንዲታይ ተጠየቀ፡፡ መመርያውን ለማሻሻል በቅርቡ የተላለፈው ሰርኩላርም እየታየ ያለውን ችግር የሚቀርፍ እንዳልሆነ ተገለጸ፡፡

  በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የወጣው መመርያ ኢትዮጵያውያን ላልሆኑ ወይም ዜግነታቸውን ለቀየሩ ባለአክሲዮኖች ምንም ዓይነት የትርፍ ክፍፍል እንዳይፈጸም፣ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች ከተገኙ የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ለፖሊስ እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ ነው፡፡ ይህ መመርያ ለፋይናንስ ተቋማት ከተላለፈ በኋላ ባንኮች ይህንን መመርያ ለማስፈጸም ሲቸገሩ በመቆየታቸው፣ በተለያዩ መንገዶች መመርያው እንዲሻሻል ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡

  መመርያውን ሊጣረስ ይችላል በሚል ሥጋት ጥቂት የማይባሉ የፋይናንስ ተቋማት ባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍላቸው ታግዶ ቆይቷል፡፡ የመመርያው ተግባራዊ መሆን ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ከግምት በማስገባትና ከሕግ አንፃርም ሊፈተሽ እንደሚገባው በማመን መመርያው እንዲጠና ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ሲቀርብ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ ጉዳዩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲመረምረው ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡

  ከዳያስፖራዎችም ዜግነታቸው በመቀየሩ ብቻ ገንዘባቸው ሊወረስባቸው በመሆኑ  ሥጋት እንዳደረባቸው ተጠቁሟል፡፡  በቅርቡ በባህር ዳር በተደረገው የዳያስፖራ ቀን ክብረ በዓል ላይም ጉዳዩ ተነስቶ መመርያውን በማየት ምላሽ እንደሚሰጥበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያ ሰጥቶበታል ተብሏል፡፡

  ይህ መመርያ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በመመልከት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤና በግንባር በመቅረብ ማብራሪያና መፍትሔዎችን በማያያዝ  አቤቱታዎችን ካቀረቡት መካከል፣ ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ይገኙበታል፡፡ መመርያው በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ዜግነት የቀየሩ ባለአክሲዮኖች የፈጠረባቸውን ሥጋት በመግለጽ አቅርበዋል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ‹‹ከኢትዮጵያውያን ውጪ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ መሳተፍ እንደማይቻል ክልከላ የሚያደርግ ነው፡፡ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚሳተፉ ባለአክሲዮኖች በአንድ አጋጣሚ ዜግነታቸውን ቢቀይሩ ምን መደረግ እንደሚኖርበት የማይገለጽ በመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች እያሉ መመርያውን ተግባራዊ ከማድረግ የተሻለ የሚሆነውን አሠራር መምረጥ ያሻል፤›› ብለዋል፡፡

  አክሲዮን ሲገዙ ኢትዮጵያውያን የነበሩ በኋላ ግን ዜግነታቸውን የቀየሩ ባለአክሲዮኖች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ምን ይሆናሉ? የሚለው ግልጽ እንዳልሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም አጠራጣሪ የሆነ ዜግነት አላቸው የተባሉ ባለአክሲዮኖችን የትርፍ ድርሻ ካከፋፈሉ ቅጣት እንደሚጣልባቸው መመርያው የሚደነግግ በመሆኑ፣ የውጭ ዜግነት ያለው ባለአክሲዮን ካለም ይህንን ባለአክሲዮን ያለመጠቆም ስለሚያስቀጣ አሠራሩ እንዲወሳሰብ አድርጓል፡፡  

  ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያውን ያለሳልሳል፣ እየታየ ያለውንም ችግር ይፈታል ብሎ ያመነበትን ሰርኩላር በቅርቡ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ሰርኩላር ችግሩን የሚፈታ እንዳልሆነ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ይገልጻሉ፡፡

  ብሔራዊ ባንክ ሰኔ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ለባንክና ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጻፈው ደብዳቤ ኢትዮጵያዊ ዜግነት በሌላቸው ግለሰቦችና ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያውያን ባልሆኑ ባለሀብቶች (ግለሰቦችና ድርጅቶች) የተቋቋሙ ድርጅቶች የመድን ሰጪዎች ባለአክሲዮን ሆነው መገኘታቸው፣ በአክሲዮን ዝውውርና በትርፍ ክፍፍል ላይ ችግሮች ማስከተሉ ይታወቃል ይላል፡፡

  በመሆኑም ለችግሩ መንስዔ ተደርገው በፋይናንስ ተቋማት የቀረቡትን ጉዳዮች ብሔራዊ ባንክ ሲመረምር መቆየቱን በመግለጽ፣ መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉና መመርያውን ያላላሉ ያላቸውን ነጥቦች አስቀምጧል፡፡ በሰርኩላሩ ከተላለፈው መካከል ዕድሮች በባለአክሲዮንነት እንዲቀጥሉና የትርፍ ድርሻቸውም ሌላ ተጨማሪ መረጃ ሳያስፈልግ እንዲከፈላቸው የሚለው አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ ኢትዮጵያዊ በሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ሥር የሚገኙ የልማትና የዕርዳታ ድርጅቶችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በባለአክሲዮንነት እንዲቀጥሉ፣ የትርፍ ድርሻቸውም ሌላ ተጨማሪ መረጃ ሳያስፈልግ እንዲከፈላቸው የሚል ውሳኔንም አካቷል፡፡

  የመድን ሰጪዎችን በባለቤትነት የያዙ ባንኮች፣ እንዲሁም የባንኮችን አክሲዮኖች የያዙ መድን ሰጪዎችን ጨምሮ ሌሎች የንግድ ተቋማት ከ99 በመቶ በላይ አክሲዮኖቻቸው የተያዙት በኢትዮጵያውያን መሆኑን የንግድ ተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎች ማረጋገጫ እንዲሰጡ ተደርጐ፣ ተቋማቱ በባለአክሲዮንነት መቀጠል እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ የትርፍ ድርሻቸውም እንዲከፈልም በመወሰን ለፋይናንስ ተቋማቱ ሰርኩላር ተላልፍሏል፡፡ ይህ የብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ ቀድሞ የወጣውን መመርያ የሚያለሳልስና ታግዶ የቆየውን የትርፍ ክፍፍል እንዲለቀቅ አስችሏል ቢባልም፣ ሰርኩላሩ ችግሩን የሚፈታ አለመሆኑንና ተጨማሪ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል ተብሏል፡፡

  አቶ ኢየሱስ ወርቅም፣ ‹‹ሰርኩላሩ ዋናውን ችግር የሚፈታ አይደለም፡፡ ውስብስብ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ መመርያ ሥር ነቀል ለውጥ ይደረግበት ይላሉ፡፡ ‹‹መመርያው ኢትዮጵያውያን አለመሆናቸውን እያወቁ አክሲዮን ከገዙት ውጪ ያሉ ዳያስፖራዎችን ወደ ቅጣት ከመውሰድ፣ አክሲዮናቸውን ወደ ኢትዮጵያውያን እንዲያሸጋግሩ ማድረግ አንድ አማራጭ እንዲሆን እንኳን ዕድል መስጠት ነበረበት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

  ይህ ግን የመጨረሻ መፍትሔ አለመሆኑን የሚገልጹት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ የተሻለ መፍትሔ የሚሆነው ዳያስፖራዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ባለአክሲዮን እንዲሆኑ መፍቀድ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆኗ አይቀርም፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ እያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ 25 በመቶ አክሲዮን ለዳያስፖራዎች ቢፈቀድ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ያምናሉ፡፡

  ከጥቂት ወራት በፊት ከብሔራዊ ባንክ የተገኘን መረጃ በዋቢነት በመጥቀስ የፋይናንስ ተቋማቱ ካፒታልና ሀብት 200 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ አኃዝ መሠረት 25 በመቶው አክሲዮን ቢሸጥ በሦስትና በአራት ዓመታት ከአራት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የሚያስችልና ያለውንም ችግር ለመፍታት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተከራክረዋል፡፡ መመርያው በድጋሚ ሊታይ እንደሚገባው የተጠየቀበት ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ባለአክሲዮኖች ሲሞቱ ያወረሱት የውጭ ዜግነት ላላቸው ልጆቻቸው በመሆኑ አሁን ትርፍ አይሰጣችሁም መባሉ ከሕግ አንፃር ክፍተት ያለው ነው መባሉ ነው፡፡  ጉዳዩ የቀረበለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከሕግ አንፃር ማብራሪያ ጠይቆበት ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡  

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች