Friday, August 19, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የቀለበት መንገዱ ምረቃና አገር በቀል ኮንትራክተሮች ላይ ያነጣጠረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ዛሬ የምናየው ግንባታ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል፡፡ ከግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜው ከስድስት ወር በፊት አስቀድሞ መጠናቀቁ ለኛ ምን ትምህርት ይሰጠናል? አንዳንድ ግንባታዎቻችን እንኳን ከስድስት ወር ቀድሞ ለመጨረስ ይቅርና ለዓመታት ሲንከባለሉ ስናይ እኛስ ምን እንማራለን? በተለይም አገራዊ ኮንትራክተሮቻችንና አማካሪዎቻችን ከዚህ ትልቅ ትምህርት ይወስዳሉ የሚል እምነት አለኝ፤›› ይህንን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ ንግግሩን ያደረጉትም ከግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜው ስድስት ወራት ቀድሞ የተጠናቀቀውንና 4.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን የለቡ አቃቂ – አይቲ ፓርክ (ጎሮ) ውጫዊ የቀለበት መንገድ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ አዲስ አበባን ከሁለት አቅጣጫ ከአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ጋር የሚያገናኘው መንገድ በይፋ የተመረቀው ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር፡፡

  በዚህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ትኩረት ሰጥተው የተናገሩት በአገራዊ ኮትራክተሮች ሊተገብራቸው ይገባል ባሉት ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ) ተገንብቶ የተመረቀው ይህ መንገድ ለአገር በቀል ኮንትራክተሮች ትምህርት የሚቀስሙበት ሊሆን ይገባል የሚል እምነታቸውን ያንፀባረቁትም ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የቻይናው ኩባንያ ግንባታውን ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት የኩባንያው ውስጣዊ አደረጃጀት ጠንካራ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም እንዲህ ዓይነቱ ጥንካሬ በአገር በቀል ኮንትራክተሮች ዘንድም ሊታይ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

  እንደ ቻይናው ኮንትራክተር ውጤታማ መሆን ካስፈለገም የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ራሳቸውን ሊፈትሹ እንደገሚባ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በዘመድ አዝማድ የተሞላ ኩባንያ የትም እንደማያደርሰን፣ በዕውቀትና በክህሎት የተያዙ ኩባንያዎች ግን ረዥም ርቀት የሚጓዙ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ እያንዳንዱ ኮንትራክተር አቅሙንና ውስጡን መፈተሽ አለበት፤›› በማለትም ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የአገራችን ሕዝቦች በአነስተኛ የዕድገት ደረጃ ባሉበትና እጅግ አንገብጋቢ የሆነውን ካፒታላቸውን አሰማርተው የሚሠሯቸው ግንባታዎች ወደኋላ ማለታቸው አይቀርም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች የተሻለ ለመሥራት አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚኖርባቸው አስታውሰዋል፡፡ ግንባታዎችን በተያያዘላቸው በጀትና ጊዜ የማጠናቀቅ ኃላፊነት የአማካሪ ድርጅቶችም ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

  ከንግግራቸው መረዳት እንደተቻለውም አገር በቀል ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያሳሰበ ነበር፡፡

  ዘርፉን በተመለከተ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሌላው ጉዳይ ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ የሚታዩ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች መኖራቸውን ነው፡፡

  ዋና የሙስና ምንጭ ተብለው ከሚወሰዱት ውስጥ አንዱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ስለመሆኑ በመግለጽም፣ በዘርፉ የሚታየውን ሙስናና ብልሹ አሠራር መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም ሕዝቡና የሚመለከተው አካል ትብብር ወሳኝ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

  በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን ልምድ የቀሰሙበት ብቻ ሳይሆን 90 በመቶ የሚሆኑት የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ስለመደረጉ አመላካች ነው ብለዋል፡፡

  28.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የለቡ አቃቂ – አይቲ ፓርክ (ጎሮ) ውጫዊ የቀለበት መንገድ በከተማዋ ፕላን ላይ የተመለከውን መስመር ተከትሎ የተገነባ መንገድ ነው፡፡ የአዲስ – አዳማ የፍጥነት መንገድ ቀጣይ ክፍልና የፍጥነት መንገዱን ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በሁለት አቅጣጫዎች የሚያገናኘው ይህ መንገድ፣ በአንዴ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ይችላል፡፡

  በኮንትራት ውሉ መሠረት ሲሲሲሲ የመንገዱ በሁለት ዓመት ከስምንት ወራት ወይም በ33 ወራት ገንብቶ እንደሚጠናቀቅ የሚገልጽ ቢሆንም፣ ኮንትራክተሩ ግንባታውን አስቀድሞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

  ይህ መንገድ በቀን 20 ሺሕ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ የመንገዱ ለትራፊክ ክፍት መሆን በተለይ ነባሩን የደብረ ዘይት መንገድ የነበረበትን ጫና በማቃለሉ ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንደገለጸው ደግሞ እንደ አዲስ – አዳማ ያሉ የፍጥነት መንገዶችን ለመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመንም በአጠቃላይ 761 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የፍጥነት መንገዶች ለመገንባት አቅዷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሞጆ ሐዋሳና የአዳማ አዋሽ ሜኤሶ የፍጥነት መንገዶች ይገኙባቸዋል፡፡ ለዚህ መንገድ ግንባታ ከዋለው ወጪ 75 በመቶው ከቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ ነው፡፡ ሲሲሲሲ ከዚህ መንገድ ግንባታ ቀደም ብሎ የአዲስ – አዳማ የፍጥነት መንገድን መገንባቱ ይታወቃል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች