Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ሪ ኢንሹራንስ ኩባንያውና የመድን ሰጪዎች አዲሱ ግዴታ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለጠፋ ዋስትና ሽፋን ለውጭ ኩባንያዎች በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ሲያወጡ ቆይተዋል፡፡ ይህንን የውጭ ምንዛሪ መጠን በአገር ውስጥ ለማስቀረት፤ የጠለፋ ዋስትና ሽፋኑን በአገር በቀል ኩባንያ ለመስጠት ሲታሰብ  ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

  ይህ ውጥን ዘግይቶም ቢሆን በ2008 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ የተባለውን ኩባንያ በመመሥረት እውን ሆኗል፡፡ 17ቱንም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የተወሰኑ ባንኮችን ባለአክሲዮን በማድረግ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር፣ ባለፈው ወር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተሰይሞለት ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማግኘት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

  የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን የተሰየሙት አቶ የወንድወሰን ኢተፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና በአገር ውስጥ በተመሠረተ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ አማካይነት አገልግሎት ማግኘት ጀምረዋል፡፡

  እስከዛሬ ከውጭ ኩባንያዎች ብቻ የሚገዙትን የጠለፋ ዋስትና ሽፋን ለማግኘት እንዲያስችላቸውም ራሱን የቻለ ሕግ በብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ኩባንያዎቹ የጠለፋ ዋስትና ግዥውን የሚፈጽሙትም ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት ሆኗል፡፡

  በመመርያው መሠረት ሁሉም የአገር ውስጥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በየዓመቱ ለጠለፋ ዋስትና ግዥ ከሚያውሉት ገንዘብ ውስጥ 25 በመቶውን ከኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ መግዛት እንዳለባቸው ግዴታ ይጥላል፡፡

  ከዚህም ሌላ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ከአቅማቸው በላይ የሆነን የኢንሹራንስ ሽፋን በቀጥታ ለውጭ የጠለፋ ዋስትና ከመስጠታቸው በፊት ከሌላ ኢንሹራስ ኩባንያ ጋር መነጋገር ወይም ለኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ ማሳወቅ አለባቸው፡፡

  በመሆኑም ኩባንያዎቹ የኢንሹራንስ ሽፋኖችን ለውጭ የጠለፋ ዋስትና ሰጭ ድርጀቶች ከመስጠታቸው በፊት ሰፊው ድርሻ በአገር ውስጥ ኩባንያ እንዲሸፈን ዕድል ይፈጥራል ተብሎለታል፡፡ ወደ ውጪ የጠለፋ ዋስትና የሚሄዱት የአገር ውስጥ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያዎች አለመቻላቸው ሲረጋገጥ ብቻ በመሆኑ የመድን ሰጪዎቹ ትላልቅ የጠለፋ ዋስትናዎች በኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ በኩል እንዲሸፈኑ መመርያው ያስቀምጣል፡፡

  ከዚህ መመርያ ጎን ለጎን እያንዳንዱ የኢንሹራንስ ኩባንያ ከሚጽፈው ዓረቦን አምስት በመቶው እየተነሳ ለሪኢንሹራንስ ኩባንያው ገቢ መደረግ እንደሚኖርበት ለአገልግሎቱ ማስፈጸሚያነት ያዛል፡፡ የወጣው መመርያ በዚህ መመርያ መሠረት የአገሪቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓመት ስድስት ቢሊዮን ብር ዓረቦን ቢሰበስቡ 300 ሚሊዮን ብር ቀንሰው ለኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ ገቢ ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡ ይህ አሠራር እንደ ግዴታ የተጣለው ኩባንያውን ለማጠናከር ታስቦ ሲሆን፣ አምስት በመቶ እየተሰላ ለሪኢንሹራንስ ኩባንያው እንዲገባ የሚደረገው ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ብቻ ይሆናል ተብሏል፡፡

  እንደ ግዴታ የተቀመጡትን እነዚህ አሠራሮች የሪኢንሹራንስ ኩባንያውን እያጠነከሩ ወደፊት ወደ አትራፊ ኩባንያነት ያደርሱታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለውጭ ጠለፋ ዋስትና ሰጪ ከሚሰጡት የጠለፋ ዋስትና ውስጥ 25 በመቶውን በአስገዳጅነት ለኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ የሚያስገቡትም በየሩብ ዓመቱ ይሆናል፡፡ ከእያንዳንዱ የኢንሹራንስ ሽፋን አምስት በመቶ ተሰልቶ መግባት ያለበት ገቢም በተመሳሳይ ጊዜ ሒደት የሚታሰብ ነው፡፡

  የጠለፋ ዋስትና ሽፋኑን በአገር ውስጥ ኩባንያ መስጠት መጀመሩ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይገለጻል፡፡ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በየዓመቱ ከሚሰበስቡት ዓረቦን እስከ 30 በመቶ የሚሆነው ለጠለፋ ዋስትና ሽፋን ግዥ ይውላል፡፡ ገንዘቡም ሲከፈል የቆየው በውጭ ምንዛሪ በመሆኑ አገልግሎቱን በአገር በቀል ኩባንያ መስጠት መጀመሩ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ያድናል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ከውጭ የሚገዙትን የጠለፋ ዋስትና ሽፋን ሙሉ ለሙሉእንደማያስቀር ከመመርያው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

  ከአገር ውስጥ አቅም ብላይ የሆነው ወደ ውጭ የጠለፋ ሽፋን ሰጪዎች ስለሚሄዱ ነው፡፡ በመሆኑም 75 በመቶው የጠለፋ ዋስትና ግዥ አሁንም ለውጭ ኩባንያዎች የሚሰጥ ነው፡፡

  እንደ አቶ ወንድወሰን ገለጻ በመጀመርያው ዓመት ማለትም በ2009 ዓ.ም. እስከዛሬ በየዓመቱ ለጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ ይከፈል የነበረውን ገዘነብ በ30 በመቶ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ወደፊትም ለውጭ ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና ሽፋን ይውል የነበረውን የገንዘበ መጠን በየዓመቱ በመቀነስ የጠለፋ ዋስትና ሽፋን በአገር ውስጥ እንዲሸፈን ለማድረግ መታቀዱን መመርያው አስፍሯል፡፡

  ይህንን ለማስቀረት ቀስ በቀስና በሒደት የሚሠራበት ይሆናል ተብሏል፡፡ አንዳንድ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ከውጭ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያዎች ጋር ካላቸው ውል በመነሳት የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ የተወሰነ እንደማይሆን ይጠበቃል፡፡ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ገበያ ውስጥ የመግባት ውጥን እንዳለው አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡

  እንደ አቶ የወንድወሰን ማብራሪያ በአጎራባች አገሮች ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመግባት የሚያስችል ዕድል አለ፡፡ ይህንን ዕድል ለመጠቀም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በአገር ውስጥ የሚከናወኑ በርካታ ወሳኝ ሥራዎች እንደሚኖሩም ጠቅሰዋል፡፡

  በዓለም አቀፍ ገበያ ለመግባት የሚያስችል ግምገማና ምዘና ተካሂዶ ለኩባንያው በሚሰጠው ደረጃ መሠረት ገበያውን በመቀላቀል ኩባንያው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ጭምር እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት 17ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሚሰጡት የኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰበስቡት ዓረቦን ከ6.3 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብሩን ለጠለፋ ዋስትና ያውላሉ፡፡

    

   

    

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች