Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው!

  አገር ማስተዳደር ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ ጥበብ፣ ትዕግሥትና አርቆ አሳቢነትን ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ሁለገብ ሰብዕናና የአመራር ክህሎትን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህን ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ግብዓቶችን ማግኘት የሚቻለው ለሰላም፣ ለዕድገትና ለዴሞክራሲ ቁርጠኛ መሆን ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መንግሥት ሕዝባዊነቱ በአንደበት ብቻ የሚነገር ሳይሆን፣ በተግባር የሚረጋገጥና የሚፈተን ነው፡፡ የሕዝብ ወገንተኝነት ያለው መንግሥት ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ታዛዥ ሲሆን፣ አሠራሩም ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ነው፡፡ ከሕዝብ ለሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ ፈጣን፣ ምክንያታዊና የሚያግባባ ይሆናል፡፡ እርካታ ባይኖር እንኳ ለውይይት መድረክ ያመቻቻል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ በዚህ መንፈስ የተቃኘ አስተሳሰብ ሊዳብር ይገባል፡፡ ከዚህ ቀና አስተሳሰብ የሚያፈነግጥ ፍላጎት ግን ከሕዝብ ጋር ያጋጫል፡፡

  በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሕዝብ ጥያቄ ሲነሳ ሕዝባዊነት እየከዳቸው ጉልበት የሚያስቀድሙ፣ ሐሳቦች በነፃነት እንዳይንሸራሸሩ እንቅፋት የሚሆኑ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሳይሆን ለአምባገነንነት የሚተጉ፣ ከአገር ህልውና ይልቅ ለሥልጣን የሚንገበገቡ፣ ከውይይት ይልቅ ስድብ የሚቀናቸው፣ በአጠቃላይ ዴሞክራሲን በአፍጢሙ ደፍተው የሹም ዶሮ መሆን የሚዳዳቸው ወገኖች በገዥው ፓርቲ መዋቅር ውስጥ አሉ፡፡ ዋና ተግባራቸውም ሕዝብን እያፈኑ ማስመረር፣ ሰብዓዊ መብት መጣስ፣ ጊዜ ባለፈበት የኃይል ድርጊት በመመካት ተቃውሞን ለማጥፋት መሞከር፣ ወዘተ መገለጫዎቻቸው ናቸው፡፡ ጠንካራ ግምገማና ውስጥን የማጥራት ሥራ ስለማይከናወን ችግሮች እየተቆለሉ በየቦታው ለሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት እየሆኑ ናቸው፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲጠፋና ሕገወጥነት እንዲሰፍን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እያገዙ ነው፡፡ ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ሲል በአንክሮ አዳምጦ መፍትሔ መስጠት ሲገባ፣ አጓጉል ምክንያቶች እየደረደሩ ችግር መጥራት አገርና ሕዝብን ይጎዳል፡፡

  ኢትዮጵያችን የሁላችንም የጋራ አገር እስከሆነች ድረስ፣ መንግሥት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለሕዝብ ጥያቄዎች ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲፈቱ ከግጭት ይልቅ ሰላም፣ ከውድመት ይልቅ ዕድገት፣ ከአምባገነንነት ይልቅ ዴሞክራሲ ያብባሉ፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ እየተነገረለት ያለው ሕዝባችን በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አቋም፣ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ወዘተ የተለያዩ ገጽታዎች ቢኖሩትም ከሚለያይባቸው ይልቅ የሚመሳሰልባቸው ያመዝናሉ፡፡ ልዩነቶችን አክብሮ በሰላምና በፍቅር መኖር የሚችል ሕዝብ ነው ያለን፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሉባት አገራችን በመቻቻል፣ በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ያስፈልጋታል ሲባል ለሁሉም ዜጎች በፍትሐዊ እኩልነት ላይ የተመሠረተ ምኅዳር መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ምኅዳር ውስጥ የሁሉም ዜጎች ፍላጎት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተስተናገደ ግጭት የመነጋገሪያ አጀንዳ አይሆንም፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ጥበብ፣ ትዕግሥት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ሁለገብ ሰብዕናና የአመራር ክህሎት ያስፈልጋሉ፡፡

  በአሁኗ ኢትዮጵያ በሕዝቡ ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎች ሊነሱ የግድ ነው፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ በዘመኑ የሚያነሳቸው የራሱ ጥያቄዎች አሉት፡፡ ጥያቄዎቹ እውነት ይኑራቸው አይኑራቸው ወሳኙ የሕዝቡ የህሊና ዳኝነት ነው፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የማንነት ጥያቄ፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ፍትሐዊ ዳኝነት፣ የሥራ ዕድል፣ ወዘተ. በተመለከተ ጥያቄዎች ሲቀርቡ በአግባቡ በሕጉ መሠረት ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ በእርግጥ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ መሆን አለባቸው፡፡ ምላሾቹም እንዲሁ፡፡ ከዚህ ውጪ በምክንያታዊነት ላይ የማይመሠረቱ፣ ከሕጋዊነት ይልቅ ዘለፋ የሚቀናቸው፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሱ፣ ከአገርና ከሕዝብ ህልውና ይልቅ ለሥልጣን ሲሉ ብቻ ግጭት ለመቆስቆስ የሚተጉ፣ ከዚያም አልፈው ተርፈው የጠላት ተላላኪ ከመሆን የማይመለሱ ወገኖችና መሰሎቻቸው ሕዝብን እንወክላለን ሲሉ የሚዳኙት በሕዝብ የህሊና ዳኝነት ብቻ ነው፡፡ መልካሙንና ክፉውን እንዲለይና የፈለገውን እንዲመርጥ ዕድሉ ያለው ሕዝብ የሚበጀውን ያውቃል፡፡ በመሆኑም ከእነሱ ጋር በሚደረግ አምባጓሮ ምክንያት ትክክለኛውን የሕዝብ ጥያቄ መግፋት በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ ዴሞክራሲያዊም አይደለም፡፡

  ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሕዝቡ ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ጥያቄዎቹን ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት፣ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ፣ ከእኩል ተጠቃሚነትና ሁለንተናዊ ከሆኑ መሠረታዊ መብቶች ድንጋጌዎች መከበር አንፃር መመልከት ይኖርበታል፡፡ ከእነዚህ ምልከታዎች በተቃራኒ ሕዝብን አልሰማም ማለት ተገቢም ሕጋዊም አይደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ችግሮችን ሁሉ ውጫዊ የማድረግ አባዜ ቀርቶ ወደ ውስጥ መመልከት ይለመድ፡፡ ሕዝብ ጥያቄዎቹን የሚያዳምጥለትና መፍትሔ የሚሰጠው አካል ሲኖር ከማንም የበለጠ የሚመሰገነው የሚያስተዳድረው መንግሥት ነው፡፡ ፅንፍ ከረገጡ፣ ለአገር ከማይበጁና ሕዝቡም የእኔ አይደሉም ብሎ ከማይቀበላቸው ውጪ ያሉ ጥያቄዎችን በአግባቡ ማስተናገድና መፍትሔ መስጠት ግዴታው ነው፡፡ ለሕዝብ ፈቃድ ታዛዥ መሆን የማይፈልጉና ሕዝቡን እያስለቀሱ መግዛት የሚፈልጉ አባላቱንና ደጋፊዎቹን አደብ እንዲገዙ ማድረግ አለበት፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማትና በሕዝባዊ ማኅበራት ውስጥ ተሰግስገው በሕገወጥ መንገድ ከመክበራቸውም በላይ፣ ሕዝቡን አደገኛ ችግር ውስጥ በመክተት በአገሪቱ ላይ ጥፋት የሚጋብዙትን ያስታግስ፣ ወይም ገለል ያድርግ፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ በጣም ወደኋላ የራቁ፣ ለአዲሱ ትውልድ የማይመጥኑና ብቃት አልባዎች አያስፈልጉም፡፡ ለአገርም አይበጁም፡፡ ይልቁንም ለባዕዳን ጠላቶች ክፍተት በመፍጠር ለትርምስ በር ይከፍታሉ፡፡

  ግልጽነት መንግሥት አሠራሩ ተጠያቂነት እንዳለበት የሚያሳይበት አንድ መሣሪያ ነው፡፡ ሕዝብ መንግሥት ግልጽ በሆነና የበለጠ በቀረበው ቁጥር ጥያቄዎቹ ይደመጣሉ፡፡ መልስ ያገኛሉ፡፡ ተጨማሪ ውይይቶች በተለያዩ መድረኮች በስፋት በቀጠሉ መጠን ትክክለኛው የሕዝብ ጥያቄ ይታወቃል፡፡ ትክክለኛው የሕዝብ ፍላጎት የሚታወቀው በቀጥታ ከራሱ አንደበት ሲሰማ እንጂ፣ አፈቀላጤ ነን ባዮች ጠምዝዘውና አውገርግረው ሲያቀርቡት አይደለም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች በቂ ትኩረት ሳይቸራቸው ቀርቶ፣ የተለያዩ ወገኖች ከበስተጀርባ አሉ ተብሎ ነጋ ጠባ የሚነገረው ሕዝብ በቀጥታ ስለማይደመጥ ነው፡፡ ዴሞክራሲ መርህ የሚሆነው የሐሳብ ብዝኃነትን ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚስተናገዱበት የሐሳብ ገበያ ስለሆነ፡፡ አስተሳሰቦች የፈለገውን ያህል የማይረቡና አደገኛ ቢሆኑ እንኳ በዴሞክራሲያዊ አግባብ ተስተናግደው፣ ለሕዝብ የህሊና ዳኝነት ችሎት መቅረብ አለባቸው፡፡ ሕዝብ የተቀበለው እየፀና፣ ያንገዋለለው ለታሪክ እየተተወ ሲሄድ ሰላም፣ ብልፅግናና ዴሞክራሲ ይረጋገጣሉ፡፡ ቀደም ሲል በኦሮሚያ በቅርቡ ደግሞ በጎንደር የተነሱ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተደምጠው መፍትሔ ይፈለግ፡፡ በጥያቄዎቹም የሕዝቡ ፍላጎት በቀጥታ ታውቆ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ድባብ ይፈጠር፡፡ ለዚህም ነው የሕዝብ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መስተናገድ ያለባቸው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...