በኪንታሮት ሕመም እየተሰቃየ በማደንዘዣ በሚገኘው የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አመራር አቶ ሀብታሙ አያሌው ላይ፣ ይግባኝ ባይ ዓቃቤ ሕግ መከራከሪያውን ሐምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሑፍ አቀረበ፡፡
አቶ ሀብታሙ ከአገር እንዳይወጣ ዕግድ ስለተጣለበት ጉዳይ ምንም ማለት እንደማይችል የገለጸው ዓቃቤ ሕግ፣ ሕመሙን በሚመለከት ከአገር ወጥቶ መታከም እንዳለበት በቀረበው የካዲስኮ ጠቅላላ ሆስፒታል የሦስት ዶክተሮች ፊርማ ያረፈበት የሕክምና ሪፖርት ላይ ግን ጥያቄ አንስቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የጽሑፍ ክርክር ለአቶ ሀብታሙ የሕክምና ሪፖርት የሰጠው ሆስፒታል ወደ ውጭ በሪፈራል ሄደው ለሚታከሙ የቦርድ ውሳኔ ለማሰለፍ ወይም ለመስጠት ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ ያያያዘው ማስረጃ አለመኖሩን ጠቅሶ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወይም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የተሰጠ ሕጋዊ ማስረጃ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡
አቶ ሀብታሙ በቀረበው ክርክር ላይ ሐምሌ ሰኞ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ምላሹን በጽሑፍ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርብ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ማክሰኞ ሐምሌ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ብይን እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
አቶ ሀብታሙ እስካሁን በማደንዘዣ መሆኑን የገለጹት ቤተሰቦቹ፣ አሁን አሁን እየተለማመደው በመምጣቱ ማደንዘዣው የማስታገስ ኃይሉ ከስምንት ሰዓት ወደ ሁለትና ሦስት ሰዓት መውረዱን ተናግረዋል፡፡