Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ‹‹ሥልጣን ላይ ያለው አመራር አገራዊ ውይይት እንዲካሄድ በሩን ካልከፈተ አደገኛ ሁኔታ ነው የሚፈጠረው››

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ፕሮፌሰር አሌክስ ዲዋል፣ የዓለም የሰላም ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር

  ፕሮፌሰር አሌክስ ዲዋል የዓለም የሰላም ፋውንዴሽን WPF) ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ በአሜሪካ የሚገኘው ዘፍሌቸር ኮሌጅ የምርምር ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በተለይ ደግሞ በዳርፉር አካባቢ ረዘም ላለ ጊዜ የሠሩ ከመሆናቸውም በላይ በተለይ በግጭቶች፣ በረሃብና በሰብዓዊ ቀውስ እንዲሁም በሰላም ግንባታ ላይ በአፍሪካ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1984 በዳርፉር በተከሰተው ረሃብ ላይ ጥናት በማድረግ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በቅርቡ ድርጅታቸው የአፍሪካ ግጭቶችንና የሰላም ማስከበር ሥምሪቶችን በተመለከተ ያጠናቀረውን ሪፖርት ለአፍሪካ ኅብረት አስረክበዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ ሳለ በረሃ ድረስ በመሄድ የድርጅቱን መሪዎች ከማነጋገራቸው በተጨማሪ ላለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ይከታተላሉ፡፡ ስለቀረበው ሪፖርት፣ በቀይ ባህር አካባቢ እየተፈጠረ ስላለው ፉክክር፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካና በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡      

  ሪፖርተር፡- በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይ ደግሞ በየመን አካባቢ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራ ትልቅ ኅብረት እየተፈጠረ ነው፡፡ የየመን ቀውስ ለአፍሪካ (በተለይ ደግሞ ለአፍሪካ ቀንድ) ምን እየጋበዘ ነው ይላሉ?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ ቀደም ሲል በሊቢያ እንደተከሰተው ተመሳሳይ አደጋ ሊጋብዝ ይችላል የሚል ግምት አለኘ፡፡ የመን ውስጥ ያለው የፖለቲካ ቀውስና የተለያዩ የዓረብ ኃይሎች ጣልቃ ገብነቶች በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ አደጋ አይጋብዙም አይባልም፡፡ እስካሁን ሳዑዲዎች፣ ኤምሬቶችና ኳታሮች በኤርትራ፣ በጂቡቲና በሶማሊያ እጃቸው እየረዘመ ነው፡፡ አንዳንድ ያልተገባ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የገልፍ አገሮች (በየመን ኅብረት የፈጠሩ የዓረብ አገሮች) በየመን የተከሰተውን ቀውስ በጉልበት ለመፍታት በወታደራዊ ኃይል ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የተከሰቱ ችግሮችና የፖለቲካ ቀውሶች በፖለቲካ ድርድርና በዴሞክራሲያዊ አግባብ መፍትሔ እንዳያገኙ በሩን እየዘጉ ይገኛሉ፡፡ በጉልበት ላይ እንጂ የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ምንም ፍላጎት አላሳዩም፡፡ ይኼው ችግር እዚያ ተወስኖ የሚቀር አይሆንም፡፡ ወደ አፍሪካ ቀንድ መሻገሩ አይቀሬ ነው፡፡ 

  ሪፖርተር፡- በቅርቡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የዓረብ አገሮች በየመን መሰባሰባቸው፣ የተባበሩት ኤምሬትስ የአሰብ ወደብን ለ30 ዓመታት ያህል መከራየቷ ሲታይ፣ በቀይ ባህር አካባቢ የእስራኤልና የዓረቦች ፉክክር እየተፈጠረ ይሆን እንዴ?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- በእርግጥ ኤምሬቶች አሰብን ወታደራዊ የጦር ሠፈር ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ካቀረብከው ይልቅ ሌላ ስትራቴጂካዊ መቧደን ያለ መስሎ ይሰማኛል፡፡ በእስራኤልና በግብፅ መካከል ያለው ወዳጅነት ጠንካራ ነው፡፡ በግልጽ ሊያወሩት አይፈልጉም እንጂ መቼም ቢሆን እስራኤል ለግብፅና ለሳዑዲ ዓረቢያ የፖለቲካ ቀረቤታ አላት፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው የእስራኤልና የዓረቦች ፀብ (ጦርነት) ትልቅ ግምት የሚሰጠው አይሆንም፡፡ በመካከለኛ ምሥራቅ ያለውና በአፍሪካ ቀንድ የራሱ የፖለቲካ በሽታ የሚኖረው የሳዑዲና የኢራን ግጭት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ በሳዑዲዎችና በሙስሊም ወንድማማቾች መካከል አንድ ግጭት አለ፡፡ ኳታርና ቱርክ ደግሞ በቅርበት የሚከታተሉት ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በቱርክ የተከሰተው ፖለቲካ ወዴት እንደሚያመራ ባይታወቅም፣ ኳታርና ቱርክ በሶማሊያ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ ብዙ ገንዘብም ያፈሳሉ፡፡ ለኤምሬትስ፣ ለሳዑዲዎችና ለግብፆች እንቅልፍ የሚነሳ ነገር ነው፡፡ የኳታርና የቱርክ እንቅስቃሴ ያስጨንቃቸዋል፡፡ ይኼ ማለት በሶማሊያ የሁለት ዓረቦች ጎራዎች ፉክክር አለ ማለት ነው፡፡

  የዓረቦችና የኢስላሚክ ጎራዎች መሆናቸው ነው፡፡ ጉዳዩን መጥፎ የሚያደርገው ደግሞ ይህንን ፉክክራቸው የሚያካሂዱት በቀጥታ ከገንዘብ ጋር በተገናኘ ፖለቲካ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በሶማሊያ በቅርቡ የሚካሄደው ምርጫ እነዚህ አገሮች ብዙ ገንዘብ የሚያፈሱበት ሆኗል፡፡ እናም ለኢትዮጵያና ለኬንያ (በይበልጥ ግን ለኢትዮጵያ) የራሱ አደጋ ሊኖረው ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ በሶማሊያ ፖለቲካ ላይ ብዙ ነገር ኢንቨስት አድርጋለች፡፡ በተለይ የሶማሊያ የጦር ኃይልን በመደገፍ ብዙ የገንዘብ ወጪ ጠይቋት እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡ እጅግ ከባድ ወጪ ነው (That’s very expensive investment)፡፡ በአገሪቱ ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ ውጤት ግን ኢትዮጵያን የሚያስደስት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የሶማሊያ ፖለቲካ ከጦር ኃይል ይልቅ በገንዘብና በጎሳ የሚዘወር ነው፡፡ ይኼንን የገንዘብ ወጪ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትሸከመው አይሆንም፡፡

  ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ባላንጣ የሆነችው ኤርትራ ደግሞ የዓረቦች ኅብረት ዋና አካል እየሆነች ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ስለምትከተለው ፖሊሲስ ምን ይላሉ?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- የኤርትራን ጉዳይ ስንመለከት ባለፉት አሥር ዓመታት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ኤርትራን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መነጠል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በእርግጥም ውጤታማ ፖሊሲ ሲሆን፣ ኤርትራ ከቀጣናው፣ ከአኅጉሩና ከተመድ ተነጥላ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ድጋፍ አጥታለች፡፡ በዲፕሎማሲም አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል፡፡ ኤርትራ በሁሉም መስክ ከዓለም ተነጥላ ቆይታለች፡፡ በዚህ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው ፖሊሲ ውጤታማ ነበር፡፡ ዘላቂነቱ ላይ ግን ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ኤርትራን በዚሁ ደካማ ሥፍራ ተነጥላ እንድትቆይ ቢያደርግም፣ ከዚያ ቀጥሎ ምን እንደሚያደርግ አማራጭ ፖሊሲ የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ለሚሰነዘርባት ትንኮሳ የምትሰጠው ምላሽ መሠረት ያደረገው ፖሊሲ ጥያቄ ውስጥ የገባው፣ ነገሮች ሲቀያየሩ ተለዋጭ ስትራቴጂ ሳይኖረው መቆየቱ ሲታይ ነው፡፡ የመን ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከሰተው ቀውስ ነገሮች ትናንት በነበሩበት ላይ አይደለም፡፡ በየመን ቀውስ ምክንያት ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ሀብታሞቹ ኤምሬቶችና ሳዑዲዎች በዚህ ቀይ ባህር ዞን ላይ ፍላጎት ማሳደራቸው፣ ለኤርትራ ትልቅ ማምለጫ ነው የተከፈተላት፡፡ ከተደበቀችበት መውጣት ጀምራለች፡፡ ኢሳያስ ምንም ሳያቅማማ የመን ውስጥ ከተፈጠረው ኅብረት ጋር አብሯል፡፡ በዘላቂነት ለአፍሪካ ኅብረትም ሆነ ለኢጋድ ከኢሳያስ ጋር መወዳጀት ዋስትና የለውም፡፡ ኤርትራ ከዓረብ አገሮች ጎራ መሠለፏ የሚያስከትለው ጉዳት ይኖራል፡፡

  በተቃራኒው ኢትዮጵያ የኃይል ሚዛኑ ያላት ቢሆንም ከዓረቡ ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት እስከዚህም ነው፡፡ እንደ ጎረቤት መልካም ግንኙነት ሳትመሠርት ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዓረቡ ዓለም ጋር ነገሮችን ቀድሞ የተመለከተ ፖሊሲ (Proactive Policy) ሳይኖራት ቆይቷል፡፡ ይኼ ለአፍሪካ ኅብረትም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ የኅብረቱ የሰላምና የፀጥታ ንድፍ (Architechure) የአፍሪካ የውስጥ ችግሮች ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ የተቀረፀ ነው፡፡ ከዓረብና ከአውሮፓ ተሻግረው ስለሚመጡ የፖለቲካ ችግሮች የሚለው ነገር የለውም፡፡ በተቃራኒው የገልፍና የዓረብ አገሮች በአፍሪካ ብዙ ገንዘብ እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡ እናም የዚህ አዲስ ሪፖርት አንዱ ምክረ ሐሳብ የአፍሪካ ኅብረት የዓረቡ ዓለምን እንደ አንድ ጎረቤት በመመልከት፣ ከዓረቦች በኩል ሊመጣ የሚችልን ግጭት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ አሠራር መንደፍ አለበት የሚል ነው፡፡

  ይህ ማለት ኅብረቱ ከዓረቦች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የሰላምና የፀጥታ መንገድ መንደፍ አለበት ማለት ነው፡፡ ከአውሮፓ ጋር እንዲሁ በተለይ ከስደት ጋር በተያያዘ የጋራ ፖሊሲ መቅረፅ ይኖርበታል፡፡ በዓረቡ ዓለም በቀይ ባህር አካባቢ የጀመሩትን እንቅስቃሴ በመተንተንና በማጥናት ነው መፍትሔ ማበጀት ያለበት፡፡ ከአውሮፓ ጋር ጠንካራ ትብብር ተፈጥሯል የሚል እምነት ነው ያለው፡፡ ችግሩ ግን አፍሪካዊያን ያንን ጠንካራ ትብብር በጋራ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ የገንዘብ ትብብር ብቻ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ በመሆኑም የስደትን ጉዳይ የወሰድን እንደሆነ ጉዳዩ በተናጠል የአንድ የአፍሪካ አገር በሚያሳድረው ተፅዕኖ ላይና አንድ አገር ሊያደርገው የሚገባ የፖሊሲ ማሻሻያ ላይ እንዲያተኩር ሆኗል፡፡  

  ሪፖርተር፡- አሁን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ልመልስዎትና የኢትዮጵያ መንግሥት መርህ የሆነው ‹‹ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት›› የሚለው ፖሊሲ ምንነት ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- አንዳንድ ተጨባጭና አስገዳጅ ነገሮች ያሉት ይመስላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሕገ መንግሥት መሬት ላይ አለ፡፡ እሱን ተግባራዊ ማድረግ ሒደት ላይ ግን እሱን የሚቃረኑ የሚመስሉ አካሄዶች ሲደረጉ ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱንና ውክልናውን እንዴት ነው የሚመለከተው? ከሚመራው ሕዝብ ጋር እንዴት መግባባት አቃተው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ አንዱ የዘመናችን አነጋጋሪ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ብዙ ጊዜ ስላወሱት የታይዋንና የኮሪያ የዕድገት መንገድ ነው፡፡ ያ ዘመን ከ30 እና ከ40 ዓመት በላይ ነው፡፡ እንደ እኔ እምነት በዚያን ጊዜ ዴሞክራሲን ወደ ጎን በማለት ልማትን ማምጣት ይቻል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሞዴል እየተወሰደ ያለው ይኼው አካሄድ ዘመኑ ያለፈበት ነው፡፡ በወቅቱ የዴሞክራሲ ጥያቄ ገና በእንጭጩ ነበር፡፡ ዛሬ ለማናቸውም ጉዳዮች ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት በቅድመ ሁኔታነት የሚቀመጡበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ በአሁኑ ዘመን አንድ መንግሥት ሕዝባዊ ተቀባይነት (Legitmacy) የሚኖረው በሚሠራው ብቻ ሳይሆን ስለሚሠራውም ጉዳይ ከሕዝቡ ጋር በቂ ውይይትና ምክክር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሕዝቡ የእኔነት ስሜት የሚኖረው ራሱ የተሳተፈበት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ተዓምርም ቢሠራ የእኔነት ስሜት አይኖረውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በሕዝቡና ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት መካከል ሰፊ ክፍተት ያለ ይመስለኛል፡፡ ዋና መርህ (The Statute) መሆን ያለበት ሕዝብን ማብቃትና (Empowering) እና ተሳትፎውን ማሳደግ ነው፡፡ ካልሆነ መንግሥት በሚያከናውነው ሥራ ሕዝቡ መወከሉን አያውቅም፡፡ መንግሥት ሕዝቡን ወክሎ እየሠራ ስለመሆኑም አይቀበልም፡፡ አንዳንድ የድርጅቱ አባላትና ጽሑፎች ይህንን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥልጣን አልባ እንደሆነ የሚሰማው ይመስለኛል፡፡ ወይም በዚህ መንግሥት ተወክያለሁ የሚል ስሜት የለውም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በፖለቲካ ውሳኔዎችና በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡን በግልጽና በስፋት አላሳተፈም፡፡ ሕዝቡን ይህ ይሰማዋል፡፡     

  ሪፖርተር፡- መንግሥት በየአምስት ዓመቱ በሚያካሂዳቸው ምርጫዎች የሕዝቡን ድምፅ ማግኘቱንና መወከሉን ይገልጻል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ማሸነፉን ነው የሚገልጸው፡፡ አባባልዎ ከዚህ ውጤት ጋር አይቃረንም?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- ምርጫ አንድ የዴሞክራሲ መንገድ ነው፡፡ ብቸኛው ግን አይደለም፡፡ ዴሞክራሲያዊ የሚያደርገው ደግሞ መካሄዱ ብቻ ሳይሆን ሒደቱ ነው፡፡ ስለአውራ ፓርቲ ሥርዓት ነው የምናወራው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የዚሁ ሥርዓት ተከታይ ሆና ወጥታለች፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት የሚቻለው እርግጠኛ ባልሆኑና በአስቸጋሪ ሒደቶች ስታልፍ ብቻ ነው፡፡ ጥብቅ ተጠያቂነትና ግልጽ ውክልና የሚያረጋግጥ አሠራር ባለበት ዓለም ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽና ግልጽ የሆነ ክርክርና ውይይት ለማድረግ አስቸጋሪ በሆነ ሥፍራ ስለዴሞክራሲ ማውራት አይቻልም፡፡ ስለአውራ ፓርቲ ብቻ ነው ማውራት የምትችለው፡፡ እዚህ አገር እየሆነ ያለው ይኼ ይመስለኛል፡፡ በሌላ መንገድ ልግለጸው መሰለኝ፡፡ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ አንድ ፓርቲ አውራ የመሆን ዕድል የለውም፡፡ ሥልጣንን በሙሉ የመውሰድና የመጠቅለል ሁኔታ አይኖርም፡፡ በተለይ ደግሞ አንድ ፓርቲ አውራ ሆኖ ለብዙ ጊዜ ሥልጣን ላይ ከቆየ ተጠያቂነትና ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ረገፉ ማለት ነው፡፡ እውነት ለመናገር ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት ይቀየራል፡፡ ያንን ለማስወገድ የሚቻለው ምናልባት ድርጅቱ ውስጥ የእርስ በርስ የመተካካትና ሽኩቻ ካለ ብቻ ነው፡፡

  ኢትዮጵያ ተፎካካሪነት ወደሚኖርበት መድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየተጓዘች ካልሆነ ወደ አውራ ፓርቲ ሥርዓት ገብታለች ማለት ነው፡፡ እዚህ ውስጥ የዴሞክራሲ ጭላንጭል የሚኖረው፣ በድርጅቱ ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች እየተስተናገዱ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካለ በፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ የአመራር ፉክክር ይታያል፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ችግሮች አፍጥጠው ይታያሉ፡፡ አንዱ ሥርዓቱ ወደ አውራ ፓርቲነት መቀየሩ ነው፡፡ ሁለተኛው የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች እየተንፀባረቁ ያሉት ብሔርን መሠረት አድርገው እንጂ፣ የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተው አይደለም፡፡ ይኼ በጣም አደገኛ ችግር ነው፡፡  

  ሪፖርተር፡- አሁን ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሂዶ ሂዶ ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- እኔ እንደሚመስለኝ የሥርዓቱ ተፈጥሮዓዊ ሒደት ወዴት እንደሚወስድ መተንበይ አይከብድም፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ አገሮች ተርታ ሆና ጥቂት ቡድኖች በፖለቲካና በኢኮኖሚ የሚመሩት (Political Economic Oligarchy) አገዛዝ ውስጥ ትገባለች፡፡ ልክ በሙባረክ ጊዜ የነበረችው ግብፅና እንዲሁም የቱኒዝያን ቅርፅ ትይዛለች ተብሎ ይገመታል፡፡ ከፍ ያለ ሙስና ይፈጸማል፡፡ አሁንም ግን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመዘገብ ይችላል፡፡ ይህንን ሀብት የሚያከፋፍል ጠንካራ መንግሥትም ይኖራል፡፡ ፖለቲካዊ ገጽታውም ሕገ መንግሥታዊ ሆኖ ጥቂት ቡድኖች የሚዘውሩት የሥልጣን ዓይነት ይመጣል፡፡ ይህንን ነው መገመት የሚቻለው፡፡ ያ ማለት ጨቋኝ ዴሞክራሲ የሚሰፍን ሲሆን፣ በተለይ የጦር ኃይሉ በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም ከፍተኛ ተሳትፎ ይኖረዋል፡፡ ሙስና ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከፍ ይላል፡፡

  ሪፖርተር፡- ከመነሻው ጀምሮ የአገሪቱን ፖለቲካ ሲከታተሉ ቆይተዋልና ይኼ መንገድ ድርጅቱ ሥልጣን ላይ ሲወጣ የያዘው ዓላማ ነው? ወይስ የሚሉት ነገር አለ?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- ትልቁ ነገር ሥልጣን ላይ ያለው አመራር አገራዊ ውይይት እንዲካሄድ በር መክፈት አለበት፡፡ አለበለዚያ አደገኛ ሁኔታ ነው የሚፈጠረው፡፡ እጅግ አደገኛ የሚሆነው ደግሞ እስካሁን በጣም ብዙ ጥሩ ስኬቶች መመዝገባቸው ነው፡፡ ግልጽ የሆነ ሰፊ ውይይት ካልተከፈተ ግን ኢሕአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት ሙሉ ያስመዘገባቸው ድሎች በሙሉ ዕውቅና ሳያገኙ ሊጠፉ ይችላሉ፡፡

  ሪፖርተር፡- ሕወሓት በትጥቅ ትግል ላይ ሳለ ትግራይ ድረስ ሂደው አቶ መለስን ጨምሮ በርካታ ታጋዮችን አነጋግረው ነበር፡፡ እስከ ዛሬ የማይረሱት ውስጥዎ የቀረ ትዝታ አለዎት?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- በትጥቅ ትግሉ ወቅት ትግራይ ሄጄ የታዘብኩት በጣም አስደናቂ ነገር፣ ትግሉ መሠረታዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አጀንዳ እንደነበረው ነው፡፡ እሱም በጣም ብዙ ግምገማና ውይይት ተደርጎበታል፡፡ እናም አገሪቱን ከደርግ ነፃ ማውጣት ብቻም ሳይሆን የትጥቅ ትግሉን የአገሪቱን የሽግግር አጀንዳ ለመፍጠር ተጠቅመውበታል፡፡ እሱ ነበር የሚገርመኝ፡፡ ያ ማለት ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ በከፍተኛ በራስ የመተማመን መንፈስ፣ በከፍተኛ የዕውቀትና የፖለቲካ ዝግጅት ነበር፡፡ ይኼ በረሃ የቀረፁት እውነተኛ አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ በቂ ዕውቀትና ፖለቲካ ነበር፡፡ የራሳቸው ከበቂ በላይ አጀንዳ ስለነበራቸው ከየትም ማምጣት አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡ የትጥቅ ትግሉ ለድርጅቱ ሰዎች የጋራ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ግልጽ ውይይትና ክርክር የሚደረግበት እንዲሁም ሐሳብ በሐሳብ የሚሸናነፍበት ሜዳ ነበር፡፡ ያንን መንገድ የለቀቀ ጊዜ ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2001 ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት የሚባል መርህ በተናጠል በግላቸው ቀርፀው፣ ምንም ውይይትና ክርክር ሳያደርግበት የአገሪቱ መርህ ሲያደርጉ ማለት ነው፡፡ አቶ መለስ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው፣ ከፍተኛ ዕውቀት ያካበቱና በራሳቸው ከፍተኛ መተማመን የነበራቸው ቢሆንም፣ ይህንን ሥርዓት ሲያውጁ ኢሕአዴግን እንደ ድርጅት አልተመለከቱትም፡፡ የትምህርት አሰጣጡ ዘይቤ ተቀየረ ማለት ነው፡፡ የእርስ በርስ መማማር መሆኑ ቀርቶ ራሳቸው የአስተማሪነት ሚና ተጫወቱ፡፡

  ሪፖርተር፡- “The Theory and Practise of Meles Zenawi” በሚለው ጽሑፍዎ፣ ‹‹መለስ የሥልጣን አድማቂ አልነበሩም፣ በሥልጣን ስለሚሠራ ነገር ብቻ ያተኩሩ ነበር፤›› ብለዋል ምን ለማለት ነው?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- ቤተ መንግሥት ውስጥ እንደ አገር መሪ የራሳቸው የተለየ አኗኗርና አመጋገብ አልነበራቸውም፡፡ የራስን ምሥል ከፍ ለማድረግም አልፈለጉም፡፡ ፎቶግራፋቸውን ተመልክተው የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ እንዲህ ዓይነት መሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ የደቡብ አፍሪካው ታቦ ምቤኪ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ ከግላቸው ይልቅ ለፖለቲካዊ አጀንዳ ትኩረት የሚሰጡ ሰው ነበሩ፡፡ ለነገሩ ኢሕአዴግም ውስጥ ይኼ ባህሪ እንዳለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሙስና ደረጃ ከጎረቤት አገሮች ዝቅ ያለ ለመሆኑ ምክንያቱ ይኼ ይመስለኛል፡፡

  ሪፖርተር፡- እስቲ ስለ ደቡብ ሱዳን እናውራ፡፡ በተደረሰው ስምምነት መሠረት የጋራ መንግሥት ተመሥርቷል፤ ነገር ግን ዛሬም ድረስ ብልጭ ድርግም እያለ ነው፡፡ ምን ያስባሉ?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- ባለፈው ዓመት የተፈረመው ስምምነት መሠረታዊ ስህተት ነበረበት፡፡ ያ ስህተት በመሠረቱ ጦርነቱ መጀመር ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ማስቻሉ ነው፡፡ ስምምነቱ ለጦርነት ምክንያት የሆነው መሠረታዊ የፖለቲካና የአስተዳደር ቀውስ የሚፈታ መስሏቸው ይሆናል፡፡ ለጦርነቱ መነሳት ሦስት መሠረታዊ መነሻዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ፉክክሩ በሁለቱም ማለትም በሰልቫ ኪርና በማቻር መካከል ተደርጎ የሚቀርበው ስህተት ነው፡፡ በብዙ ፖለቲከኞች መካከል ፉክክር ነበር፡፡ በድርድሩ ይህንን ችግር መፍተት ነበረባቸው፣ አላደረጉትም፡፡ ሁለቱም መሪዎች ተሸማግለው ሁኔታውን ወደነበረበት መለሱት እንጂ አልፈቱትም፡፡ ሥልጣን ተጋሩ እንጂ የግጭቱ መንስዔ አልተነካም፡፡ ስትራቴጂው በሳልቫ ኪር የተቀረፀ ሲሆን፣ ሙስና እንደ መጋራት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ለማበልፀግ ሲሠራ ነበር፡፡ ብሩ ደግሞ ከአገር ወጥቷል፡፡ በአገሪቱ የሚሰረቅ ከፍተኛ ብር ሲኖር ፀብ የለም፣ ሁሉም ሰው ደስተኛ ነው፡፡ በቂ ገንዘብ ሲጠፋ ጥቂት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ብቻ ይሰርቃሉና ፀቡ ወደ ፖለቲካ ይቀየራል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 እና በ2012 መካከል ብዙ ገንዘብ ስለነበር ሰላም ነበር፡፡ የነዳጅ ዋጋ ቀውስ በመከሰቱ ግን ገንዘብ ደረቀ፣ ጦርነቱም ተጀመረ፡፡

  ሦስተኛው ምክንያት ኤስፒኤልኤም (SPLM) በዋናነት ወታደራዊ ድርጅት ሲሆን፣ አንድ ወጥነት ያለው የኮማንድ አመራር የለውም፡፡ እያንዳንዱ ጎሳ የራሱ የሆነ ወታደራዊ ኃይል ያለው በመሆኑ፣ ድርጅቱ የእነዚህ ወታደራዊ ዩኒቶች ስብስብ ነው፡፡ ወጥነት ያለው የተማከለ አመራር እንዲኖረው የተደረገ ነገር የለም፡፡ ይኼ ችግር ባለበት ነው ስምምነት የተፈራረሙት፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ልዩነቶችን መፍታት ሳይቻል ሲቀር ችግሩ ወደ ወታደሮች ይሄዳል፡፡ ከዚያም ወደ ጎሳ ይቀየራል፡፡ አሁን እነዚህ ችግሮች ሳይነኩ ነው ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሞከረ ያለው፡፡ የማቻርን ጦር ወደ ጁባ ማምጣት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በከተማዋ እንዲፋጠጡ ነው ያደረገው፡፡ አሁንም ጦርነት ላይ ነው ያሉት፡፡ ወደፊትም የጊዜ ጉዳይ እንጂ እነዚህን ችግሮች መፍታት ካልቻሉ መዋጋታቸው አይቀርም፡፡ የአሁኑ ስምምነት ሁኔታው ጦርነቱ ሲጀመር ወደነበረበት ነው የመለሰው፡፡ የፖለቲካ መከፋፈሉም አሁን የባሰበት ነው፡፡ 

  ሪፖርተር፡- የዓለም የሰላም ፋውንዴሽን ሠርቶ ባቀረበው በዚሁ ሪፖርት እንደተመለከተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ከተሸጋገረ ጊዜ ጀምሮ፣ በአኅጉሪቱ የእርስ በርስ ግጭቶች በቁጥር እየጨመሩ መምጣታቸውን ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- በመጀመርያ እ.ኤ.አ. ከ1990 አንስቶ በአፍሪካ የመንግሥት ግልበጣዎችና የእርስ በርስ ግጭቶች በቁጥር እየቀነሱ መጥተው ነበር፡፡ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ነበሩት፡፡ አንዱና ዋነኛው የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃቱ ነው፡፡ ነገር ግን ከ1990 በኋላ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ለማለት ይቻላል አፍሪካን ረስቷል፣ አልያም አግሏል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት በአፍሪካ አንዳንድ ክስተቶች ታይተዋል፡፡ የየራሳቸው አሉታዊም አወንታዊም ተፅዕኖም ነበራቸው፡፡ አንዱ በአወንታዊነት የሚታየው ክስተት የአፍሪካ አገሮች የውስጥ ችግሮቻቸውን በራሳቸው መንገድ ለመፍታት ዕድል የፈጠረ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሶቪየት ኅብረትም አሜሪካም እጃቸውን ሰብስበዋል፡፡ ለምሳሌ በወቅቱ የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በኢትዮጵያ የተጀመረው የዴሞክራሲ ግንባታ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በሶማሊያ ስትመለከት በወቅቱ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በማብቃቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መንግሥት አልባ ልትሆን ችላለች፡፡ በሩዋንዳ ደግሞ አሳዛኝ የሆነው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር በጉዳዩ ላይ ፈጥኖ ዕርምጃ አልወሰደም፣ ጣልቃም አልገባም፡፡

  እነዚህ ክስተቶች ለየአፍሪካ መሪዎች ፈተና ሆነውባቸው ነበር፡፡ በራሳቸው መንገድ ለመፍታት አልያም ያንን ማድረግ አለመቻል የሚያስከትለውን ተፅዕኖ መቀበል አንዱን መምረጥ ነበረባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች›› የሚሉ አስተሳሰቦች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ በተለይ አንዳንድ ስመ ጥሩ የአፍሪካ መሪዎች እንደ ታቦ ምቤኪ (ደቡብ አፍሪካ)፣ የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦባ ሳንጃ የመሳሰሉት የአፍሪካ ችግሮችን ለመፍታት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ራሱን የቻለ የሰላምና የደኅንነት አደረጃጀትና መዋቅር እንዲዘረጋ ያቀረቡት የተደራጀ ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የአፍሪካ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት፣ እንዲሁም የአፍሪካ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ማቋቋም ተችሏል፡፡

  ሪፖርተር፡- የሪፖርቱ ሌሎች ግኝቶች ለፖለቲካ ጉዳዮች ቅድሚያ እንዲሰጥና ኅብረቱ በአፍሪካ አጀንዳዎች ላይ ዋና ባለቤት መሆን አለበት የሚሉ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የፋይናንስና የአቅም ድጋፍ የሚደረግለት ከውጭ (ከለጋሽ አገሮች) ሆኖ ሳለ፣ ይህንን ምክረ ሐሳብ ማስቀመጥ በተግባር የሌለ አፍአዊ የሚሆን አይመስልዎትም?

  ፕሮፌሰር አሌክስ፡- ‹‹ቅድሚያ ለፖለቲካ ትኩረት ይሰጥ›› ሲባል አንድ ችግር ሲከሰት ፖለቲከኞችን ብቻ አቀራርቦ በማነጋገር እርቅ መፍጠር ማለታችን ብቻም አይደለም፡፡ኅብረቱ የተመሠረተባቸው ዋና መርሆች ላይ ተመሥርቶ የፖለቲካ መፍትሔ ማፈላለግ ማለት ነው፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን፣ እንዲሁም አሳታፊ በሆነ መንገድ ለችግሮች መፍትሔ ማግኘት ለማለት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በመርህ ደረጃ ከሌሎች ሁሉ የተለየ መሆን አለበት ነው፡፡ ስለገንዘብና ጥገኝነት በተመለከተ ያነሳሃው ነገር ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ በገንዘብ ራስህን የቻልክ ካልሆንክ፣ በፖለቲካም በነፃነትና በገለልተኝነት መንቀሳቀስ አትችልም ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት የኅብረቱ ችግሮች ሆነው ከሚጠቀሱት ዋነኛው ይኼው የገንዘብ እጥረት ነው፡፡ ይኼው የአቅም ችግር ሌሎች የፖለቲካ ችግሮችን ሁሉ ሲያባብስ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ እንደ ሊቢያ የመሳሰሉ አገሮች ዓመታዊ መዋጮ መክፈል አልቻሉም፡፡ ሁሌም ቢሆን የፋይናንስ ችግር በኅብረቱ ውስጥ በተለይ ደግሞ የኅብረቱ የተለጠጡ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ችግሩን ያባብሱታል፡፡ ለምሳሌ በሶማሊያ የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግለት በአውሮፓ ኅብረት ነው፡፡

  የገንዘብ ጥገኝነትን ተከትሎ የሚመጣ የፖለቲካ ተፅዕኖ ይኖራል፡፡ ለዚህም ነው ኪጋሊ (ሩዋንዳ) ላይ ኅብረቱ የወሰነው አማራጭ የገንዘብ ምንጭ ጠቃሚ የሚሆነው፡፡ ሐሳቡ የመነጨው በአሜሪካ ነው፡፡ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች 25 በመቶ ከአፍሪካ አባል አገሮች መዋጮ እንዲሆን፣ የተቀረው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች እንዲሸፈን የሚል ነው፡፡ አለበለዚያ የአፍሪካ ኅብረት እንዲህ ዓይነት ዘላቂ የገንዘብ ምንጭ ካላገኘ በግልጽ በሊቢያ የሆነው የማይደገምበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለሊቢያ ቀውስ የአፍሪካ ኅብረት ያቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ ትክክለኛ ነበር፡፡ ነገር ግን ተግባራዊ አልሆነም፡፡ አንድም በአቅም እጥረት ሁለትም በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ደካማነት የተነሳ፡፡   

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -