በመንግሥት ላይ የ3.9 ሚሊዮን ብር ጉዳት ማድረሳቸው ተገልጿል
የቦሌ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት የኅብረት ሥራ ማኅበራት መኖሪያ ቤት የመስተንግዶ ባለሙያና የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ቡድን መሪን ጨምሮ፣ ስድስት ግለሰቦች በሙስና ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው::
ተከሳሾቹ በጥቅም በመተሳሰር ቀራኒዮ ተራራ ቁጥር 2/33 የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት ኃላፊነቱ የተወሰነ የኅብረት ሥራ ማኅበር አባላት ሲተካኩ፣ የማኅበሩን ሕጋዊነት ሳያረጋግጡ ማፅደቃቸውን ክሱ ይጠቁማል:: በመሆኑም የማኅበሩ ሕጋዊነት ሳይረጋገጥ የመተካካት ሥራ እንዲፈጸም በማድረግና የመንግሥትን ይዞታ ያላግባብ በማስተላለፍ፣ በመንግሥት ላይ የ3,914,949 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ ያስረዳል::
ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ የቦሌ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት የኅብረት ሥራ ማኅበራት መኖሪያ ቤት የመስተንግዶ ባለሙያ አቶ ብርሃነ ግርማይ፣ በግል ሥራ የሚተዳደሩት አቶ መህዲ ሰፋና አቶ ዓለማየሁ ወልደየስ፣ የኅብረት ሥራ ከፍተኛ አደራጅና ምዝገባ ባለሙያ አቶ ተወልደ ገብረ ሚካኤል፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ተሞገስ ወልደ አምላክና አቶ ጌታቸው ድንቁ ናቸው::
ተከሳሾቹ በተጠቀሰው የጋራ መኖሪያ ሕንፃ የመኖሪያ ቤት ማኅበር መሥራች አባላቱ በወቅቱ ሲደራጁ የአዲስ አበባ ነዋሪነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ በወቅቱ መዘጋጀት ሲገባው፣ በተለያዩ ጊዜያት መታወቂያ በመስጠት ሕገወጥ ተግባር መፈጸማቸውን ክሱ ያብራራል:: በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በማለትና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው፣ በሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያስረዳል::