Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ቪዛ አፍሪካ – ለድንበር የለሽ አኅጉር

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  የአውሮፓ አገሮች አንድነትና አብሮነት የሚገለጽበት አንዱ ገጽታ ሸንገን ቪዛ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት አባልነቷ ጥያቄ ውስጥ የነበረውን አየርላንድን ጨምሮ 22 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2004 ከፀደቀው አዋጅ በኋላ፣ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አባል አገር በድንበር ላይ ምንም የተለየ ቪዛ ሳያስፈልጋቸው በነፃነት መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡

  በቅርቡ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት የወሰነችውና በመውጣት ሒደት ላይ የምትገኘው ብሪታኒያና ጎረቤቷ አየርላንድ ሪፐብሊክ በራሳቸው ቪዛ ለመሥራት የመረጡ በመሆናቸው፣ የዚህ የሸንገን ቪዛ አካል አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል እስካሁን የኅብረቱ አባል ያልሆኑት ቡልጋርያ፣ ክሮሽያ፣ ቆጵሮስና ሩማንያ ደግሞ በተቃራኒው የአውሮፓ ኅብረት መገለጫ የሆነው የአውሮፓ ቪዛ ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  ሸንገን ቪዛ የኅብረቱ አባል ሳይሆኑ የቪዛው ተጠቃሚ የሆኑትና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በአንድ ፓስፖርት እንዲንቀሳቀሱና ድንበር ላይ ምንም ዓይነት የይለፍ ቪዛ ሳያስፈልጋቸው እንዲሻገሩ የሚያስችል ብቻም አይደለም፡፡ ከተለያዩ የዓለም አገሮች ወደ አንድ አባል አገር የሚሰጠው ቪዛ፣ ወደ ሌሎች የኅብረቱ አባል አገሮችም ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ስምምነት ነው፡፡

  በሕግ ማዕቀፎች፣ በአወቃቀሩና በተቋማቱ አደረጃጀት የአውሮፓ ኅብረት ገጽታ እንዳለው የሚነገርለት የአፍሪካ ኅብረት ወደ ተመሳሳይ ሒደት ለመግባት የወሰነ ሲሆን፣ ይኸውም ቀደም ሲል የኅብረቱ የወርቅ ኢዮቤልዩ በተከበረበት ከሦስት ዓመት በፊት ስምምነት ላይ በተደረሰው 2063 አጀንዳ ተመሥርቶ የተደረገ ነው፡፡ አጀንዳ 2063 ኅብረቱ በቀጣዮች ሃምሳ ዓመታት በአንድ መንግሥት፣ በአንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የመከላከያ ሚኒስትር ለመተዳደርና በአጭሩ የተባበረው የአፍሪካ መንግሥት (USA) ለመመሥረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ ለመጨረስ ያለመ ነው፡፡ በቅርቡ እንዲከናወኑ ካስቀመጣቸው ዓላማዎች መካከል እ.ኤ.አ. በ2018 አኅጉሪቱ በአንድ ቪዛና ፓስፖርት እንድትሠራ የሚለው ይገኝበታል፡፡

  መሰንበቻውን መደበኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ከኅብረቱ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ ከሆነችው ከአዲስ አበባ ውጪ ሲካሄድ ከረጅም ጊዜ በኋላ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በኪጋሊ ሩዋንዳ በተካሄደው ጉባዔ ለየት ያሉ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ለመመረጥ ከቀረቡት ሦስት ተፎካካሪዎች መካከል አንዳቸው አስፈላጊውን ድምፅ ሳያገኙ መቅረታቸው ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ግን በዚሁ ከሐምሌ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለጥቂት ቀናት በቆየው የኅብረቱ ጉባዔ፣ ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማይታወቀውና ምናልባትም ለአፍሪካውያን ህልም የሚመስለው በአንድ ፓስፖርትና ቪዛ የመጠቀም ውሳኔ የብዙዎቹን ትኩረት የሳበ ይመስላል፡፡

  የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ አንዱ ድል ተደርጎ የተቆጠረው ይኼው ውሳኔ ለዚሁ 27ኛው የኅብረቱ ጉባዔ የተለየ መነቃቃትና መነሳሳት እንደፈጠረ በአካባቢው የነበሩ ታዛቢዎች እየገለጹ ነው፡፡ የአፍሪካ ቪዛ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲሆን፣ አንድ አፍሪካዊ ዜጋ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በነፃነት ለመንቀሳቀስ ያስችለዋል ተብሏል፡፡

  የአንድ አኅጉራዊም ሆነ አካባቢያዊ ውህደት የመጀመሪያ ሒደት ተደርገው ከሚታዩት ነፃ የሰዎችና የዕቃዎች እንቅስቃሴ አንዱ የሆነው ይኸው ውሳኔ፣ አፍሪካ ውስጥ በድንበር አካባቢ በሚያጋጥሙ ውስብስብ ሁኔታዎች የሰው ኃይልና የንግድ እንቅስቃሴ ልውውጥ እስከዚህም እንዲሆን ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

  የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የሆኑት የቻድ ፕሬዚዳንት እድሪስ ዴቢና የጉባዔው አዘጋጅ አገር የሆነችው የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ‹‹የመላው አፍሪካ ቪዛ›› ከኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮንዛና ድላሚ ዙማ እጅ በመቀበል የመጀመሪያዎቹ ሆነዋል፡፡

  ፕሬዚደንት እድሪስ ዴቢ የአፍሪካ ቪዛ በመቀበል የመጀመሪያ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ፣ ‹‹ይህንን ፓስፖርት ከተቀበልኩ በኋላ ኩሩና ጥልቅ ስሜት ያለኝ የአፍሪካ ልጅ መሆኔን ተሰምቶኛል፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹ለአፍሪካ አገልግሎት በምንሰጥባቸው ዓመታት ኅብረቱ የመሪዎች ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ ሕዝቦች መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩ ተቋማትንም ስናገኛቸው ከነበሩበት የበለጠ ጠንካራ ማድረግ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡ ቀጣዩ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር የኅብረቱ ጠንካራ ጐን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ሊስተካከሉ የሚገቡ ድክመቶችም እንደሚጠብቋቸው ገልጸዋል፡፡

  በወቅቱ ኃላፊነቱን ለአሸናፊው ይለቃሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር አሸናፊ ያልተገኘ በመሆኑ ለሚቀጥሉ ስድስት ወራት በሊቀመንበርበት እንዲመሩት አደራ ተሰጥቷቸዋል፡፡

  የአፍሪካ ኅብረት ቪዛውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 አፍሪካውያን በአኅጉራቸው ከቪዛ ነፃ ሆነው ለመንቀሳቀስ ያላቸው ህልም እውን እንደሚሆን የሚያመለክት ውሳኔ ብሎታል፡፡

  እስከ ዛሬ አፍሪካውያን በአኅጉሩ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የቪዛ ሒደቱ ጉዞአቸውን አስቸጋሪ ያደርገው እንደነበር ይገለጻል፡፡

  እስካሁን አሥራ ሦስት የአፍሪካ አገሮች ብቻ ያለቪዛ ነፃ ጉዞ ፈቅደው የቆዩ ሲሆን፣ በተቃራኒው አሜሪካውያን ያለቪዛ በነፃ ወደ 20 የአፍሪካ አገሮች ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ጥቁር አፍሪካውያን ወደ ተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ከሚደርስባቸው ግፍና ከተጠርጣሪነት አጋጣሚ ባልተናነሰ፣ በዚሁ ‹‹አኅጉራችን›› በሚሉት በአፍሪካ ተመሳሳይ ችግር ይገጥማቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

  የአፍሪካው ትልቁ ባለሀብት የሆኑት ናይጄሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ ይህንን ውሳኔ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ ወንድማቸው በአሜሪካ ድንበር የመያዝ ዕድል እንደገጠመው ሁሉ እሳቸው ራሳቸው በደቡብ አፍሪካ የኢምግሬሽን ሠራተኞች ከአውሮፕላን ማረፊያ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

  አናቤል ጎንዛሌዝ የተባሉ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ኃላፊ በበኩላቸው፣ በዚሁ የቪዛ ሥርዓት ምክንያት በየትኛውም የዓለም አካባቢ ካለው የንግድ ልውውጥ በአፍሪካ ያለው የእርስ በርስ ግንኙነት ዝቅተኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ቪዛ ከሁለት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2018 የአፍሪካ ዜጎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል መሆኑን፣ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ በአኅጉሪቱ ነፃና ቀረጥ አልባ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ቃል ተገብቷል፡፡

  እስካሁን ሲሸልስ፣ ሩዋንዳ፣ ሞሪሺየስና ጋና አፍሪካውያን በነፃ ወደ አገራቸው እንዲገቡ ከፈቀዱ አገሮች መካከል ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የቪዛ ነፃ እንቅስቃሴ የተፈቀደው ለአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ሌሎች የኅብረቱ ሠራተኞች ብቻ ነው፡፡

  የዳንጎቴ ግሩፕ ባለቤት አሊኮ ዳንጎቴ የመላ አፍሪካ ቪዛ ከአገር መሪዎች በእኩል ጊዜ እንደሚሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የመላው አፍሪካ ቪዛ መሬት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ሊያስቸግር እንደሚችል አንዳንድ ጥርጣሬዎች ከወዲሁ እየተገለጹ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በሚካሄዱ ግጭቶች ሳቢያ ከሚፈናቀሉ ስደተኞች ጋር በተያያዘ፣ እንዲሁም እንደ አልሸባብና ቦኮ ሐራም የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖች አጋጣሚውን ለጥፋት እንዳይጠቀሙበት ተሰግቷል፡፡ እንዲሁም ደግሞ እንደ ኢቦላ የመሳሰሉ ወረርሽኞችና ዜግነት ከሌላቸው አፍሪካውያን ጋር በተያያዘ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ እንዳያደርጉት ተሰግቷል፡፡

  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መሥራችና የኅብረቱ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ ብትሆንም፣ እስከ ዛሬ ከቪዛ ነፃ እንቅስቃሴ ያልፈቀደች ተብላ ስትተች ቆይታለች፡፡         

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -