Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ለአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጣ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ቻይና ብድር ፈቅዳለች

  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ይገነባሉ ተብለው ከሚጠበቁ አዳዲስ የፍጥነት መንገዶች ውስጥ አንዱ የሆነው የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድን ለመገንባት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጣ፡፡ ለፕሮጀክቱ የቻይና መንግሥት ብድር ለመስጠት ተስማምቷል፡፡

  በሁለት ኮንትራክተሮች ተከፍሎ የሚገነባውና 130 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአዳማ መኢሶ የፍጥነት መንገድ በ2009 በጀት ዓመት ግንባታው እንደሚጀመር ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

  የአዳማ መኢሶ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነው የአዋሽ መኢሶ ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድን ለመገንባት የሚችሉ ኮንትራክተሮችን ለመጋበዝም በቅርቡ ጨረታ እንደሚወጣ እየተጠበቀ ነው፡፡ ለዚህ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ወጪ የቻይና ገቢና ወጪ ንግድ (ኤግዚም) ባንክ ብድር ለመስጠት መስማማቱ ታውቋል፡፡ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች የቻይና ኤግዚም ባንክ ብድሩን ለመስጠት መስማማቱን ቢገልጹም፣ የብድር መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

       ከሁለቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዘውና 221 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የድሬዳዋ ደወሌ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡  

  የአዳማ አዋሽ መኢሶ ድሬዳዋ ደወሌ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ የአገሪቱን የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳልጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ወደ ውጭ የሚላክም ሆነ ከውጭ የሚገባ ጭነት የጉዞ ቆይታ እንዲሁም የተሽከርካሪዎችን የነዳጅ ፍጆታና የጥገና ወጪዎችን በመቀነስ አገሪቱ ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አወንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡

  ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ያለውን የንግድ መተላለፊያ መስመር ከማሻሻል በተጨማሪም የፍጥነት መንገዱ የ Intelligent Transportaion System ተብሎ የሚጠራው ዘመናዊ አሠራር የሚዘረጋበት፣ ከእግረኞችና ከእንስሳት ነፃ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ ይህ ሲደረግም የመንገድ ተጠቃሚዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ ያለሥጋት በፍጥነት እንዲያሽከረክሩ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

  የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ጊዜ ውስጥ በጠቅላላው በርዝመታቸው 761 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የፍጥነት መንገዶችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንዲሁም ግንባታቸውን ለማስጀመር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

  ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ሊገነቡ የሚችሉ የፍጥነት መንገዶችን መነሻ ማስተር ፕላን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከአዲስ አበባ በአራቱ በሮች በኩል ለሚወጡት መንገዶች ቅድሚያ በመስጠት ዝርዝር የአዋጭነት ጥናቶችን በቅርቡ እንደሚጀመር የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውለታ ከተፈጸመባቸው ውስጥ 202 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሞጆ ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ በዚህ ዓመት መጀመሩ ጠቅሷል፡፡ ይህ የፍጥነት መንገድ የአፍሪካ አገሮችን የሚያቋርጡ ‹‹የትራንስ አፍሪካ ሐይዌይ›› ተብለው የሚጠሩ መንገዶች አካል እንደመሆኑ፣ ከኬንያና ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ ለማቀላጠፍ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙትን ሐይቆችና ፓርኮች ለመጎብኘት የሚጓጓዙትን የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ፍሰት በማቀላጠፍ፣ ወደ ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል የሚደረገውን ጉዞ በማፋጠን በተለይም የመንገዱን አቅጣጫ ተከትለው ለሚገነቡ የኢንዱስትሪና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት በማቅረብ ኢትዮጵያ በዓለም ግንባር ቀደም የሆኑ ኩባንያዎችን ወደ ዘርፉ ለመሳብ የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍ እንደሚሆንም ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

  የአገሪቱ ቀዳሚ የፍጥነት መንገድ በመሆን አገልግሎት የሚሰጠው የአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት መገንባቱ ይታወሳል፡፡ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ከሚገነቡ የፍጥነት መንገዶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ ግንባታን የቻይና ኮንትራክተሮች ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች