[የክቡር ሚኒስትሩ ቢዝነስ ፓርትነር ስልክ ደወለላቸው]
- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዛሬ ነው የምትደውለው?
- የበዓል ቀን ቴክስት አድርጌ ነበር፣ አልደረስዎትም እንዴ?
- አንተ ገንዘብ ዝም ብሎ ሲፈስልህ እየጠገብክ ነው ማለት ነው?
- ክቡር ሚኒስትር በእውነት ቴክስት አድርጌ ነበር፡፡
- ለማንኛውም ይሁንልህ፡፡
- በዓሉ እንዴት ነበር ግን?
- ይኼኛው ገናማ ልማታዊ ነበር እኮ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እስረኞች ይፈታሉ መባሉን አልሰማህም?
- እሱማ ሰምቻለሁ፡፡
- የተፈረደባቸውና ጉዳያቸው በዓቃቤ ሕግ እየታየ ያሉ እስረኞች ብቻ ሳይሆኑ ወደፊትም የሚገቡት ይፈታሉ ተብሏል፡፡
- እርስዎንም ስለሚመለከት ነው በጣም ደስ ያለዎት?
- እንዴት?
- ወደፊት ከሚገቡት መካከል መኖርዎ አይቀርም ብዬ ነው?
- ምንድነው የምትቀባጥረው?
- ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩት ለሌላ ጉዳይ ነው፡፡
- ለምን ጉዳይ?
- መቼም በዓልን ቤትዎ ነው ያሳለፉት?
- ቤት ተጎልቼ ቲቪ ሳይ ነው የዋልኩት፡፡
- ስለዚህ ቲቪ እየኮመኮሙ ነዋ የሳለፉት?
- ምን ቲቪ ብቻ ቢራውንም ስኮመኩም ሰክሬ ነበር፡፡
- ብዙ ጠጡ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ጠጥቼ ሳይሆን በማስታወቂያው ነው እንጂ የሰከርኩት፡፡
- በነገራችን ላይ ጥሩ ነጥብ ነው ያነሱት፡፡
- አንተም ታዝበኸው ነበር?
- እኔማ አገሪቷ ያደገችው በመጠጥ ብቻ ነው እንዴ እስክል ድረስ የቢራ ማስታወቂያዎቹ አስገርመውኝ ነበር፡፡
- አንተ ደግሞ ባገኘኸው አጋጣሚ ልማቱን መተቸት ትወዳለህ፡፡
- እኔ እንኳን የታዘብኩትን ልንገርዎ ብዬ ነው፡፡
- ለማንኛውም ስለቲቪ ለምን ጠየቅከኝ?
- አንደኛው ቴሌቪዥን ጣቢያ ያቀረበው ፕሮግራም የአገሪቷን ዕድገት ራሱ እንድጠይቅ እያደረገኝ ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- አገሪቷ እንደዚህ አድጋለች እየተባለ ዜጎች ግን የመጠጥ ውኃ ለማግኘት ምን ያህል ፍዳ እንደሚያዩ ሳይ አዘንኩ፡፡
- ዕድገት እኮ ሒደት ነው እንጂ ሁሉም ነገር በአንዴ አያድግም፡፡
- ለማንኛውም ይህን ችግር ያሳየው ጣቢያ የሠራውም ሥራ አስገርሞኛል፡፡
- ምን ሠርቶ ነው እንደዚህ የምታደንቀው?
- የመጠጥ ጉድጓድ ቆፍሮ ውኃ ለዜጎች አውጥቷል፡፡
- ጥሩ ሥራ ነው፡፡
- አገሪቷ ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች በእንደዚህ ዓይነት በጎ ተግባር ሲሳተፉ እኮ የዜጎችን ሕይወት በደንብ መቀየር ይቻላል፡፡
- በሐሳብ ደረጃ ጥሩ ነው፣ ሐሳቡም ይበረታታል፡፡
- የእናንተ ችግር ግን ሐሳብን ወደ ተግባር መቀየሩ ላይ ነው፡፡
- ሰውዬ በበዓሉ የደወልከው ልትሳደብ ነው እንዴ?
- አደዋወሌማ አንድ ነገር ፕሮፖዝ ለማድረግ ነው፡፡
- ምንድነው ፕሮፖዝ የምታደርገው?
- እኔና እርስዎ በምንሠራው ቢዝነስ ስምም እንደዚህ ዓይነት በጎ ሥራ ብንሠራ ለማለት ነበር፡፡
- ሰውዬ ምን ነካህ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- አገር በዕርዳታ ልታድግ አትችልም ሲባል አልሰማህም?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- በየመንገዱ የለማኝ መዓት እያጨናነቀን መሆኑን ረሳኸው?
- እ…
- አገሪቷ ውስጥ የለማኝ ቁጥር በጣም እያደገ መጥቷል፡፡
- ሌላኛው የዕድገቱ መገለጫ ነው ማለት ነው?
- ምን ይላል ይኼ?
- እርስዎ ለማኝ በዝቷል ስላሉኝ ነው፡፡
- አገር የሚያድገው በሥራ እንጂ በዕርዳታ አይደለም፡፡
- ለነገሩ እዚህ አገር በሥራ ብቻ ሳይሆን በስርቆትም ይታደጋል፡፡
- እ…
- ያው እንደ እርስዎ ማለቴ ነው፡፡
- ሰውዬ ጤና የለህም እንዴ?
- ለማንኛውም ኮርፖሬት ሶሻል ሪስፖንሲቢሊቲ የሚባል ነገር ያውቃሉ?
- ጠንቅቄ ነው የማውቀው፡፡
- ስለዚህ እሱን እንወጣ እያልኩዎት ነው፡፡
- እሱንማ እየተወጣሁ ነው፡፡
- እንዴት?
- የእኔ ኮርፖሬት ሶሻል ሪስፖንሲቢሊቲ የሚያገለግለው አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡
- ለማን ነው?
- ለራሴ!
[አንድ የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ደወለላቸው]
- እንኳን አደረስዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዛሬ እንዴት ትዝ አልኩህ?
- እንኳን አደረስዎ ለማለት ነው፡፡
- እንኳን አብሮ አደረሰን፡፡
- በዓል እንዴት ነበር?
- በዓሉማ በጣም ልማታዊ ነበር፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እስረኞች ሊፈቱ ነው፣ እስር ቤቱ ሊዘጋ ነው፣ ከዚህ በላይ ልማት የት አለ?
- ለነገሩ ዜናውን ሰምቼ ተደስቻለሁ፡፡
- ሁላችንም ተደስተናል፡፡
- መግለጫችሁም አስደሳች ነበር፡፡
- ስነግርህ ከዚህ በኋላ አስደሳች ነገር ብቻ ነው ያለን፡፡
- የእናንተ ተሞክሮ የሚያሳየው ግን ሌላ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- የምትፈጽሙት ያወራችሁትን ተቃራኒ ነዋ፡፡
- ምንድነው የምትቀባጥረው?
- ያን አሰቃቂ እስር ቤት እንዘጋለን ስትሉ ሰው ሌላ ነገር ደግሰውልን ነው እያለ ነው፡፡
- ሌላ ምን?
- በየቤታችን ሊገርፉን ነው እያለ ነው፡፡
- ሰው መቼም ይቀልዳል አይደል?
- ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተከለከለ ብቸኛ ነገር ቀልድ ስለሆነ ነዋ፡፡
- ለማንኛውም ይኼ ውሳኔ የተወሰነው የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ነው፡፡
- ይኼማ የሁልጊዜ ዲስኩራችሁ ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ሰው አሁንም አልተዋጠለትም፡፡
- ታዲያ በውኃ ያወራርደዋ?
- ውኃውስ ቢሆን በሳምንት አንዴ አይደል እንዴ የሚመጣው?
- ምን ሆነሃል ሰውዬ?
- ያው እናንተ ወሬ ታወራላችሁ እንጂ ተግባሩ ላይ የላችሁበትም፡፡
- የአሁኑን ውሳኔ ወደኋላ እንደማንልበት ተማምለን ነው የጨረስነው፡፡
- የማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ ይማማላሉ ይባላል አይደል?
- አትተማመኑም እያልከኝ ነው?
- ውስጡን ለቄስ አይሻልም?
- ዛሬ ሰው ነገር ነገር እያለው ነው ልበል?
- ለማንኛውም ዘፋኙ እንዳለው እንዳትሆኑ፡፡
- ምንድነው ዘፋኙ ያለው?
- ጉራ ብቻ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ደወለላቸው]
- እንኳን አደረስዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳን አብሮ አደረሰን፡፡
- በዓሉ እንዴት ነበር?
- ልማታዊ በዓል ነበር፡፡
- ለነገሩ እኔም በጣም ተደስቼ ነው በዓሉን ያሳለፍኩት፡፡
- ምን ተገኘ?
- ለሕዝቡ የሰጣችሁት የገና ስጦታ አስደስቶኛል፡፡
- የትኛው ስጦታ?
- የታሰሩ ፖለቲከኞች ይፈቱ መባሉና እስር ቤቱ መዘጋቱ ነዋ፡፡
- ከዚህ በኋላ የሕዝቡን ጥያቄ በሚገባ እንመልሳለን፡፡
- ለነገሩ ከዚህ በኋላ አገሪቷ ዝም ብላ አንደምትመነደግ ገብቶኛል፡፡
- ከዚህ በኋላማ ልማት ብቻ ነው፡፡
- ስለዚህ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ተዘጋጅታችኋል ማለት ነው?
- እያንዳንዱ የሕዝቡ ጥያቄ ይመለሳል ስልህ?
- ከእናንተ አካሄድ ግን በርካታ አገሮች መማር ይገባቸዋል ባይ ነኝ፡፡
- እንዴት ማለት?
- ለምሳሌ እናንተ እስር ቤቱ ተዘግቶ ሙዚየም እንዲሆን ወስናችኋል፡፡
- ትክክል ነው፡፡
- እንደ ሳዑዲ ያሉ አገሮች ደግሞ ሆቴል ወደ እስር ቤት እየቀየሩ ነው፡፡
- ስማ ኢትዮጵያ እኮ ለበርካታ አገሮች አርዓያ የምትሆን አገር ነች፡፡
- አሁን የደረስንበት የዴሞክራሲ ደረጃ ብዙዎች የሚያስቀና ይመስለኛል፡፡
- ምንም አልተሳሳትክም፡፡
- በነካ እጃችሁ ግን ሳዑዲ ያለው ሆቴልም እንዲዘጋ ብታደርጉ ደስ ይለኛል፡፡
- የትኛው ሆቴል?
- ሪትስ ካርልተን ሆቴል ነዋ፡፡
- ለምንድን?
- እንዲፈቱ ነዋ፡፡
- ማን?
- ጧሪያችን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እየተወያዩ ነው]
- ሰሞኑን በተወሰነው ውሳኔ በጣም ነው የተገረምኩት ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ ነው የገረመህ?
- በኢሕአዴግ መዋቅር ውስጥ ብዙ ዓመት ስለሠራሁ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ይተላለፋል ብዬ አልጠበቅኩም፡፡
- የትኛው ውሳኔ?
- ባለፈው ሳምንት ፖለቲከኞች ይፈታሉ መባሉ አስገርሞኛል፡፡
- ምን ይገርማል?
- ከዚያም ባለፈ ማዕከላዊ ይዘጋል መባሉ አስደንቆኛል፡፡
- ለሕዝቡ የሚያስብ መንግሥት ከዚህም በላይ ሌላ ርቀት መሄድ አለበት፡፡
- ለነገሩ የሕዝቡ ጥያቄ ተጀመረ እንጂ መቼ ተነካ?
- ማለት?
- ሕዝቡ ከዚህ የባሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉት፡፡
- የምን ጥያቄ?
- የልማት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ፍትሐዊነትና የመሳሰሉት፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- ይኼ ለመጀመር ጥሩ ነው፣ ግን ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ይፈልጋሉ፡፡
- አንድ ነገር ስላልገባህ ነው፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- መንግሥት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መንደፉን ታውቃለህ?
- በሚገባ እንጂ፡፡
- ለተከታታይ ዓመታት ያስመዘገብነውን ዕድገት የውጭ ተቋማት ሳይቀሩ መስክረዋል፡፡
- እሺ?
- አሁን ሕዝቡ እየጠየቀ ያለው ትራንስፎርሜሽኑ የታለ እያለ ነው፡፡
- ትራንስፎርመሩማ በየጊዜው እንደ ፈንዲሻ እየፈነዳ ነው፡፡
- እኔ ያልኩህ ትራንስፎርሜሽን ነው፡፡
- እሱስ የታለ?
- ይኸው ተጀመረ፡፡
- እንዴት?
- እስር ቤቱን ወደ ሙዚየም ቀየርነው፡፡
- እሺ?
- ከዚያም አልፎ ገራፊዎቹን ወደ አስጎብኚነት ልንቀይራቸው ነው፡፡
- ኪኪኪ…
- ምን ያስቅሃል?
- ገርሞኝ ነዋ፡፡
- እሱ ብቻ አይደለም፡፡
- እሺ?
- ጥፍር ነቃዮቹንም በአነስተኛና ጥቃቅን አደራጅተን ትራንስፎርም ልናደርጋቸው ነው፡፡
- ወደ ምን?
- ወደ ጥፍር አስዋቢነት!