Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ፔጆና መስፍን ኢንጂነሪንግ በውቅሮ መገጣጠሚያ ፋብሪካ አዋቅረዋል

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የፈረንሳዩ ፔጆ መኪና አምራች፣ ከሚያመርታቸው የቤት አውቶሞቢሎች መካከል የተወሰኑ ሞዴሎችን በኢትዮጵያ መገጣጠም ጀመረ፡፡ የፔጆ ተሽከርካሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መገጣጠም የጀመሩት በፔጆና በመስፍን ኢንጂነሪንግ መካከል በተደረሰ ስምምነት መሆኑ ታውቋል፡፡

  በትግራይ ክልል ከመቐለ 40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ውቅሮ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የመስፍን ኢንጂነሪንግ የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ አማካይነት የሚገጣጠሙት አውቶሞቢሎች ሦስት ዓይነት ሞዴሎች ናቸው፡፡

  መገጣጠሚያ ፋብሪካው ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በይፋ በተመረቀበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በመጀመሪያው ዙር በፋብሪካው ተገጣጥመው ለገበያ ከሚቀርቡት ሦስት የፔጆ ሞዴል አውቶሞቢሎች በተጨማሪ ሌሎች የቤት አውቶሞቢሎችም ይገጣጠማሉ፡፡

  መስፍን ኢንጂነሪንግ በውቅሮ ከተማ የፔጆ አውቶሞቢሎችን በመገጣጠም የጀመረው ሥራ ሌላም ትልቅ ራዕይ የተሰነቀበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህም በአገሪቱ ትልቁን የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ መንደር ወደ መመሥረት የሚሸጋገርበት እንደሚሆን መነገሩ ነው፡፡

  ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው ግዙፉ የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ፣ በሒደትም ወደ ሙሉ የመኪና አምራችነት ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቀት እየተገጣጠሙ የሚገኙት የፔጆ ሥሪት አውቶሞቢሎችም በመስፍን ኢንጂነሪንግ የተጀመረውን የመገጣጠም ሥራ ለመንደርደሪያነት እንደሚያግዙ ተገልጿል፡፡

  የመስፍን ኢንጂነሪንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃብተ ሃዱሽ እንደሚገልጹት፣ የተሽከርካሪ ተጠቃሚዎችን ቁጥርና የአገሪቱን የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ተሽከርካሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

  መስፍን ኢንጂነሪንግ ተሽከርካሪዎችን ከመገጣጠም ወደ ማምረት ለመሸጋገር የሚያስፈልገውን ጥናት በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና ለማምረቻ ቦታ ግንባታም 50 ሔክታር መሬት እንደሚያስፈልገው አስታውቋል፡፡ ቦታውን የማግኘቱ ሒደት እንደተጠናቀቀም ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል፡፡

  የፈረንሳዩ አውቶሞቢል አምራች ፔጆ፣ ከመስፍን ኢንጂነሪንግ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በውቅሮ ሥራ የጀመረው መገጣጠሚያ ፋብሪካ፣ ለፔጆ ኩባንያ በአፍሪካ ሦስተኛው ተቋም ለመሆን በቅቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር በሞሮኮና በናይጄሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች አሉት፡፡

  የኢፈርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አዜብ መስፍን እንደገለጹት፣ መስፍን ኢንጂነሪንግ ከዚህ ቀደም የቻይናዎቹን ጄሊ የቤት አውቶሞቢሎች ሲገጣጥም ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ ከፈረንሳዩ ኩባንያ ጋር የፔጆ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም መጀመሩ የኩባንያው እንቅስቃሴ እያደረገ መምጣቱን አመላካች እንደሆነ ያሳያል ብለዋል፡፡ መስፍን ኢንጂነሪንግ፣ ከጄሊና ከፔጆ የቤት አውቶሞቢሎች በተጨማሪ ከታዋቂው የጀርመን ኤምኤኤን (MAN) ኩባንያ ጋር በቅርቡ ባደረገው ስምምነት መሠረት፣ የኤምኤኤን ከባድ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁንም ከ250 በላይ የኤምኤኤን ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ለደንበኞቹ ማስረከብ እንደጀመረ ከመስፍን ኢንጂነሪንግ ኃላፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

  ከአራቱ የመስፍን ኢንጂነሪንግ ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች አንዱ በሆነው በአውቶሞቲቭ ዘርፍ የቤትና የከባድ ተሽከርካሪዎችን ከመገጣጠም ባሻገር፣ ከህንድ ኩባንያ ጋር በመሆን ትራክተር ገጣጥሞ ለገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚኝ ታውቋል፡፡

  በመስፍን ኢንጂነሪንግ የሚገጣጠሙት የፔጆ ተሽከርካሪዎች አሁን ባለው የመገጣጠም አቅም መሠረት በዓመት እስከ አንድ ሺሕ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ማቅረብ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ እንደ ገበያው ሁኔታም የምርት መጠኑን መጨመር እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

  በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የፔጆ ኩባንያ የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ክርስቶፈር ኡመር እንደገለጹትም፣ በኢትዮጵያ በሦስት ሞዴሎች የተጀመረው የመገጣጠም ሥራ ሌሎች ተጨማሪ ሞዴሎችን በማስከተል ዓመታዊ የመገጣጠም አቅሙን እያሳደገ ይሄዳል፡፡

  በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም ኩባንያቸው ሊመጣ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡ ከኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች እንደተገለጸው በአሁኑ ወቅት ለገበያ የሚቀርቡት ሦስቱ የፔጆ ተሽከርካሪዎች ዋጋ ከውጭ መጥተው ይሸጡ ከነበረበት ይልቅ እስከ 15 በመቶ ቅናሽ ይኖራቸዋል፡፡

  በመስፍን ኢንጂነሪንግ የፔጆ ተሽከርካሪዎች የምረቃ ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ብሪጅት ኮሬት፣ የትግራይ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር መብራህቱ መለስ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

  መስፍን ኢንጂነሪንግ ከአንድ ሚሊዮን ብር ባነሠ ካፒታል የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የሚያንቀሳቅሰው ካፒታል ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወይም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

    

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች