Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በሎጂስቲክ አገልግሎት መስክ ያልተፈቱ ችግሮች

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ዕቃዎችን ለማጓጓዝ የሚጠየቀው ዋጋ ከፍተኛ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ የሎጂስቲክ ዋጋ ከሌሎች አገሮች ጋር በንጽጽር ይታይ ከተባለም ሰፊ ልዩነት ያለው ሆኖ ይገኛል፡፡ ዓርብ ሰኔ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. የአገሪቱን የሎጂስቲክ አገልግሎት በተመለከተ ተካሂዶ በነበረ የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ ለአገሪቱ የሎጂስቲክ አገልግሎት ዋጋ መወደድ አንዱ ምክንያት የአገሪቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ዘመናዊ አለመሆኑ ነው፡፡

  በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በአጽንኦት እንደተገለጸውም ከፍተኛ ሆኖ የሚገኘውን የሎጂስቲክ ዋጋን ዝቅ ሊያደርጉ የሚችሉ ዘመናዊ አገልግሎቶች በትራንስፖርት ዘርፉ ውስጥ አለመታየታቸው ትልቅ ችግር ሆኗል፡፡ በውይይት መድረኩ የመወያያ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የኢትዮ ትራክ ኩባንያ መሥራች ዶ/ር አዛሪያስ ሙላቱ እንደገለጹት፣ በሎጂስቲክ ዘርፍ አንዱ ችግር ዘመናዊ የሎጂስቲክ አገልግሎትን በአግባቡ መተግበር አለመቻል ነው፡፡

  የውይይቱ ተሳታፊዎች በሎጂስቲክ አገልግሎት መስክ ያሉትን ችግሮችም ጠቁመው ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በሳተላይት የታገዙ አቅጣጫ መጠቆሚያ ሥርዓት (ጂፒኤስ) የተተከለላቸው ተሽከርካሪዎች የተፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ያልተቻለበት አጋጣሚ በመፈጠሩ ዘርፉን ለማሳደግና ወጪን ለመቀነስ አላስቻለም፡፡

  በኢትዮጵያ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ዋጋ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ለመወዳደር ከባድ ስለሚሆን የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን ማዘመንና ወጪ ቆጣቢ ማድረግ ተገቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

  አገልግሎቱን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስታጠቅ ብቻ ወጪን መቀነስ እንደማይቻል የጠቀሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ ሎጂስቲክን የሚመለከቱት መመርያዎች ሊስተካከሉ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

  ኔትወርክና የሎጂስቲክ አገልግሎት

  የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመን አንዱ መፍትሔ የጂፒኤስ አገልግሎት በመትከል ተሽከርካሪዎች ወጪ ቆጣቢና አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ነው፡፡ ጠቀሜታውም የጐላ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ጂፒኤስ ተተክሎላቸውም ቢሆን ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡

  ይህም የጂፒኤስ አገልግሎት የሚሰጠው በኔትወርክ በመሆኑ ነው፡፡ በኔትወርክ ችግር ሳቢያም ተሽከርካሪዎች ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ፡፡ ምንም እንኳ ኔትወርክ በማያገኙበት ጊዜ እንቅስቃሴያቸውን የሚያመለክት ሪፖርት ቢያቀርቡም በወቅቱ ዕርምጃ ለመውሰድ ግን የኔትወርኩ መቆራረጥ እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡

  የኔትወርክ ችግር በዚህ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ተሽከርካሪው የጂቡቲን ድንበር ከተሻገረ በኋላ ግንኙነት የሚቋረጥ በመሆኑ የጂፒኤስ አገልግሎቱን ጐዶሎ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል፡፡

  ዶ/ር አዛርያስም ይህ ችግር እንዳለ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በአገሪቱ 80 በመቶ የኔትወርክ ሽፋን መኖሩ ቢገለጽም፣ በተጨባጭ ግን በበርካታ አካባቢዎች የኔትወርክ መቆራረጡ እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ የጂፒኤስ አገልግሎት እንዲሠራ ዓለም አቀፍ ኔትወርኮችን መጠቀም አስፈላጊ ስለመሆኑም በመፍትሔነት ተቀምጧል፡፡

  የሎጂስቲክስ ዋጋና ተያያዥ ችግሮች

  የሎጂስቲክ ወጪን እንዴት መቀነስ ይቻላል የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ በመጥቀስ አስተያየታቸውን የገለጹት፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን የወከሉ ባለሙያ ናቸው፡፡ የሎጂስቲክ አገልግሎት ወጪ እጅግ ከፍተኛ የሚሆነው ከመነሻው ጀምሮ ነው ያሉት እኚህ ባለሙያ፣ የጭነት አገልግሎቱ ከመነሻው ወደብ ጀምሮ አገር ቤት እስኪደርስ ድረስ ብዙ የሚነካኩ ነገሮች ስላሉ ወጪውም በዚያው ልክ እየናረ እንደሚመጣ አብራርተዋል፡፡

  ትልቁ ችግር ተቀናጅቶ ያለመሥራት ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ ‹‹በሎጂስቲክ ሥራ ውስጥ የሚጠቀሱ እንደ ጉምሩክ፣ መንገድ ትራንስፖርት፣ የወደብ ድርጅትና የመሳሰሉት በቅንጅትና በእኩል ፍጥነት የማይሠሩ ከሆኑ አገልግሎቱ ይጓተታል፡፡ በተፈለገው ጊዜ ዕቃን ወደሚፈለገው ቦታ ማድረስ ስለማይቻል የማጓጓዣ ዋጋው ይጨምራል፡፡››

  ሌላው የሎጂስቲክስ ችግር የዕቃ ማጓጓዣው ዘዴ አንድ ዓይነት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ዕቃዎች የሚጓጓዙት በተሽከርካሪዎች ብቻ መሆኑ ለአገልግሎቱ የዋጋ ንረት ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

  መንግሥት የሎጂስቲክስ ዋጋ እንዲቀንስ የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጉን የጠቆሙት እኚሁ ተወካይ፣ በተለይ ለማጓጓዣ የሚወጣው የጨረታ ዋጋ የተጋነነ በመሆኑ በድርድር ጭምር ዋጋው ቅናሽ የሚደረግበትን አግባብ እስከመከተል ተደርሷል ይላሉ፡፡ በጨረታ መሥራት ግዴታ ቢሆንም ከጨረታ በኋላ በድርድር ዋጋ የማስቀነስ ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ ይህም ተደርጐ ዋጋው ውድ ሆኖ ይገኛል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራሮች ያስከተሉትን ጉዳት በመመልከት አሠራሩ የሚሻሻልበት መንገድ ተጠንቶ ለመንግሥት መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱ የሎጂስቲክ አገልግሎት ለምን ውድ እንደሆነ ፍተሻ በሚደረግበት ጊዜ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ተጠቃሽ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ባለንብረቶቹ ለዋጋ መናር ከሚያቀርቧቸው መካከል አንዱ ምክንያት የመሠረተ ልማት አለመሟላት ነው፡፡

  ‹‹ባልተመቻቸ መሠረተ ልማት ውስጥ የምንሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበትን ተሽከርካሪ ያለዕድሜው ስለሚገድለው ወጪያችንን በአጭር ጊዜ ለመመለስ ዋጋ ከፍ ማድረጉ የግዴታ አማራጭ ስለሆነ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የጐማና የመለዋወጫ ዋጋን በማሰብ ጭምር ካልተሠራ አዋጭ አይሆንልንም የሚል ምክንያት እየሰጡ ነው፡፡

  ለሎጂስቲክስ ዋጋ መናር የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት አንዱ መንስዔ ሆኖ የቀረበበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ በዕቅድ ያለመሥራት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ የተሰነዘረው አስተያየት ምሳሌ ያደረገው የመንግሥት የማዳበሪያና የዕርዳታ ግዥዎች እንዲሁም ግብዓቶች በዕቅድ የሚስተናገዱበትን አሠራር በተገቢው አኳኋን ቀድሞ ያለማቀድ ነው፡፡

  አንዳንዴ እነዚህ ምርቶች በአንድ ጊዜ ተጭነው የጂቡቲን ወደብ ያጥለቀልቃሉ፡፡ በ10 እና በ15 መርከቦች ተጭነው የሚመጡት እነዚህ ምርቶችና ዕቃዎች በቶሎ መነሳት አለባቸው ተብሎ የሚፈጠረው ትርምስ ለትራንስፖርት ዋጋ መወደድና እጥረት ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸው ተስተውሏል፡፡

  ከጂቡቲ ወደብ በቀን ማስተናገድና ማጓጓዝ የሚቻለው እስከ 800 ተሽከርካሪዎች ብቻ ሲሆን፣ ከዚያ በላይ እስከ 1200 ተሽከርካሪዎች ዕቃ ማንሳት አለባቸው ከተባለ ግን ከአቅም በላይ በመሆኑና ችግሩን ይበልጥ ስለሚያባብሰው መንግሥት እነዚህን ምርቶች በዕቅድ ቢያስመጣ ተመራጭ ነው ተብሏል፡፡

  የትራንስፖርት ድርጅቶችም ለአሽከርካሪዎች የሚከፍሉት ክፍያ አነስተኛ መሆን፣ ከሎጂስቲክስ አገልግሎት ጋር የተሳሰሩ መሥሪያ ቤቶች ደካማ አገልግሎት ለችግሩ መባባስ ተጠያቂዎች ናቸው ተብሏል፡፡  

  ለሎጂስቲክስ አገልግሎት የታሰበው መፍትሔ

  በውይይት መድረኩ ላይ መገንዘብ እንደተቻለው ለሎጂስቲክ አገልግሎት ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት በተሽከርካሪዎች ብቻ ዕቃ ማጓጓዝ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ያለውን ችግር ለመቅረፍ የባቡር ትራንስፖርት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ አገልግሎት ሲጀመር በተወሰነ ደረጃ ለዕቃ ማጓጓዣ የሚወጣው ወጪ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በመጪው ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ከጂቡቲ አዲስ አበባ የተዘረጋው ባቡር አገልግሎት ይጀምራል መባሉ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

  ነገር ግን እንዲህ ያሉ መፍትሔዎች ከተተገበሩ በኋላ ከጂቡቲ ተነስተው ወደ ተለያዩ ደረቅ ወደቦች የደረሱ ዕቃዎች በቶሎ የማይነሱ ከሆነ አሁንም የሎጂስቲክ ወጪው ተቃሏል ለማለት እንደማይቻል ተገልጿል፡፡

  በአሁኑ ወቅት በሞጆ ደረቅ ወደብ ብቻ ከ12 ሺሕ በላይ ኮንቴይነሮች ተከማችተው ያለመነሳታቸውን መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡ ኮንቴይነሮቹ እስከ 300 ቀናት ሳይነሱ የቆዩ ናቸው፡፡ ብዙ በቆዩ ጊዜም የዋጋ ንረትን እያስከተሉ እንደመጡ ተነግሯል፡፡

  የተጋነነ የቀረጥ ዋጋ፣ የአገልግሎት አሰጣጡ መንቀርፈፍና የመሳሰሉት ለሎጂቲክ ችግሮች መባባስ ምክንያት መሆናቸውን ተሳታፊዎች ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች