Friday, August 19, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት መገዛት ባህል ይሁን!

  የኢትዮጵያን መልካም ስምና ዝና ከሚያጎድፉ ረሃብ፣ የከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ባልተናነሰ በእልህና በቂም ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ገመድ ጉተታ፣ አገሪቱንና ሕዝቡን ለዓመታት ጭንቅና መከራ ውስጥ መክተቱ መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት በበጎውም ሆነ በክፉ ጊዜ እርስ በርሱ እየተደጋገፈ ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች የጠበቃት አገሩ፣ በገዛ ልጆቹ መቅኖ እንድታጣ ሲደረግና የባዕዳን መዘባበቻ ስትሆን እንደማየት የሚያም ነገር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ካለፉት 40 ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭትና በቅራኔ የተሞላው የፖለቲካ ግንኙነት በርካታ ወርቃማ አጋጣሚዎችን አሳጥቷል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመቀባበል ይቅርና በቅጡ ለመነጋገርና ለመደራደር ባለመቻሉ ምክንያት በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ በየእስር ቤቱ ተጥለዋል፣ ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ያለፉት 26 ዓመታት ጉዞም በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ነው የቀጠለው፡፡ ይህ አሳዛኝ ምዕራፍ ተዘግቶ ኢትዮጵያውያን ለሰላማዊ፣ ለፍትሐዊና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያበቃቸው አዲስና ሥልጡን ምዕራፍ እንዲጀመር ከልብ መነሳት ይገባል፡፡ ለኩሩውና ለአስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

  በቁጭት፣ በእልህ፣ በንዴት፣ በቂም በቀል፣ በጥላቻና በመሳሰሉት ለአገር የማይጠቅሙ አረንቋዎች ውስጥ ሆኖ ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለዕድገት መነጋገር አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታጋሽ፣ ጨዋ፣ ኩሩና አርቆ አሳቢ በመሆኑ ይህንን አኩሪ የጋራ እሴት ለሚመጥን ፖለቲካዊ ግንኙነት መዘጋጀት የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ኃላፊነት ነው፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት ኋላቀር አስተሳሰብና ጀብደኝነት ሳይሆን፣ በመርህ ላይ የተመሠረተ ውይይትና ድርድር ለአገር እንደሚበጅ መቼም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ እኩል እናት እንድትሆን ከተፈለገ፣ ሁሉም ልጆቿ ያለምንም አድልኦ የሚሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ ዓውድ መፈጠር አለበት፡፡ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ ደግሞ መጀመርያ ከጀብደኛ ድርጊቶች መታቀብ፣ ለሕግ የበላይነት መገዛት፣ ከሕገወጥ ተግባራት መራቅ፣ የዴሞክራሲን እሴቶች ማክበር፣ ለሥልጣን የሚደረገው ትንቅንቅ ከአገርና ከሕዝብ ህልውና እንደማይበልጥ ማመን፣ ከአሻጥርና ከሴራ ፖለቲካ መላቀቅና ከምንም ነገር በላይ ሕዝብን ማክበር በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ሕዝብ በሚገባ ይረካል፡፡

  አገር በሚያስተዳድረው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እስካሁን ያለው የተበላሸ ግንኙነት የሚስተካከለው፣ ለአገር የማይጠቅሙ የተወሳሰቡና ፋይዳ የሌላቸው በግትርነት የተሞሉ እንካ ሰላንቲያዎችን በማስቆም ነው፡፡ ወደ ትክክለኛው ጎዳና መመለስ የሚቻለውም ራስን ለመላው ሕዝብ ፈቃድ ማስገዛት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ የአገሪቱ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ፣ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ሰላማዊና ዴሞክራሲያ ግንኙነት መጀመር አለበት፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊኖር የሚችለው መጀመርያ ኢሕአዴግ በቅርቡ በአመራሮቹ አማካይነት በገባው ቃል መሠረት ምኅዳሩን ወለል አድርጎ ሲከፍት ነው፡፡ እስካሁን የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሒደት የቀለበሱና የፖለቲካ ምኅዳሩን ያሽመደመዱ አላስፈላጊ ድርጊቶች ተወግደው፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት መልካም አጋጣሚ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ ከልቡ ተፀፅቶ ሕዝብን ይቅርታ ሲጠይቅ፣ ሌላው ቀርቶ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶች ተከብረው የአገሪቱ ፖለቲካም ከታሰረበት መፈታት ይኖርበታል፡፡ የእስካሁኑ አሳዛኝና አሳፋሪ የፖለቲካ ጉዞ ተገቶ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ታሳሪዎችን መፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ለእስር የሚዳርጉ ከመብትና ከነፃነት ጋር የሚቃረኑ ድርጊቶችን ማስወገድ ጠቃሚ ነው፡፡ ሕዝብንም ያስደስታል፡፡

  በተቃውሞ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ የአገር ጉዳይ ያገባናል በማለት በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች፣ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ተገዥ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት ለእውነተኛ ውይይትና ድርድር መቅረብ አለበት ሲሉም፣ በእነሱ በኩል ያሉትን ክፍተቶችና ችግሮችም አንጥረው ለማውጣት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር የምትፈጠረው ራስን ለሕዝብ ፍላጎት በሚመጥን ደረጃ ማዘጋጀት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የአንድ ጎራ ደጋፊ መሆን እንደማይችሉ በመገንዘብ፣ ድጋፍና ተቃውሞን በአግባቡ ማስተናገድ የግድ ይላቸዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በስፋት እንዲከፈትና ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግሉ እንዲቀጥል፣ በሠለጠነ መንገድ የተበላሸው ግንኙነት መታደስ አለበት፡፡ ከቂም፣ ከጥላቻና ከበቀል የፀዳ አስተሳሰብ በመያዝ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራስን ማዘጋጀት የወቅቱ ግዴታ ነው፡፡ እልህና ግትርነት የትም እንደማያደርሱ በመተማመን ካረጀውና ካፈጀው አስተሳሰብ መውጣት ይገባል፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል አሰልቺ፣ አስመራሪና ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩበትም፣ በፅናት ታግሎ የሕዝብን ልብ መግዛት መቻል ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው በዚህ መንገድ የሚጓዝ ፓርቲን ነው፡፡ ሕዝብን ማክበር የሚጀመረውም ከዚህ ነው፡፡

  በማኅበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉ ወገኖችም ይህንን አጋጣሚ በጥንቃቄ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው በተለይ የወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበትና ንቃተ ህሊናቸውን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከአጠቃላይ የሕዝቡ ቁጥር ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣቱና ታዳጊው ትውልድ የጥላቻና የቂም በቀል ፖለቲካ ሰለባ እንዳይሆን፣ ይልቁንም የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ተረካቢ ስለሆነ የዴሞክራሲ እሴቶችን መቅሰም አለበት፡፡ ባለፉት ሁለት ትውልዶች በተበላሹ ግንኙነቶች ምክንያት ደብዛው የጠፋው ፖለቲካ እንዳይከሰት ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍንና በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር አገር እንድትገነባ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ጎራዎች ተሠልፈው አገርን ለትርምስ፣ ዜጎችን ለዕልቂት የዳረጉ ተግባራት የማኅበራዊ ሚዲያው አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ አገራችን በዚህ የተሳሳተና አውዳሚ አቅጣጫ ስትጓዝ፣ ከብሔራዊ ጥቅሞቻቸው አንፃር ለማዳከም የሚጥሩ ባዕዳን አደጋ መታሰብ አለበት፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያ ካሁን በኋላ ዴሞክራሲ በምልዓት እንዲሰፍንና ለጭቆናና ለአምባገነንነት መራቢያ የሚሆኑ አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዲቆሙ ሞጋችና ጠያቂ ትውልድ መፍጠር ሲገባ፣ አገሪቱን የሚያተራምሱና የሕዝቡን ደኅንነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ አላስፈላጊ ተግባራት መቀንቀን የለባቸውም፡፡ ከሥልጣን በላይ አገር አለች፡፡ ሕዝብ አለ፡፡ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት መገዛት ይገባል፡፡ ሕዝብም የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡

  የዚህች አገርና የእዚህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ዋስትና በአንድነት መቆም መቻል ነው፡፡ ይህ አንድነት የተለያዩ ማንነቶችን፣ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችን፣ እምነቶችንና የመሳሰሉ ልዩነቶችን የሚያከብር ሲሆን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩ ክብርና ዘለዓለማዊነት በጋራ ይቆማል፡፡ ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረ የአገር ፍቅር ስሜት ይበልጥ አብቦ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትገነባ ዘንድ ቅንነትና በጎ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በአምባገነንነት አስተሳሰብ ስላልሆነ፣ ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች መገዛት ተገቢ ነው፡፡ ያረጁና ያፈጁ ለአገር የማይጠቅሙ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ለዚህ ዘመን ትውልድ ስለማይመጥኑ አሽቀንጥሮ መጣል ይገባል፡፡ በብሔርተኝነት ካባ ውስጥ የአገርን ህልውና የሚንዱ ተግባራትም ሆኑ፣ ሥልጣንን ለብቻ ለመቆጣጠር የሚደረጉ ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊቶች ፋይዳ የላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ በሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ላይ ለተመሠረተ የፖለቲካ ግንኙነት መገዛት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ነው፡፡ በእኩልነት ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር ነው፡፡ ከጋራ እሴቶቹ የሚመነጩትም በአንድነት መቆም፣ የጋራ ግብና ራዕይ ይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ መቀባበል ነው፡፡ በዚህ መንፈስ የዓመታት ስህተቶችን ማረምና አዲስ ምዕራፍ መጀመር የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን ደግሞ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት መገዛት ባህል ይሁን!

   

     

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  ከጉምሩክ ውጪ ፍተሻ ተፈቅዶላቸው የነበሩ አስመጪዎች ገደብ ተጣለባቸው

  የጉምሩክ ኮሚሽን ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎችን ከጉምሩክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ አቀረበ

  መንግስት ስኳር ኢንተርፕራይዞችን ወደግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ባለሐብቶች እንዲሳተፉ...

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...