የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለስድስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ለውድድር ከቀረቡት የመጨረሻ አምስት ዕጩዎች መካከል፣ ሦስቱን ለመጨረሻ ውሳኔ የዩኒቨርሲቲው አመራር ቦርድ መምረጡን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራር ቦርድ ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ የምልመላና ምርጫ ኮሚቴ ካቀረበለት አምስት ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የመረጣቸው በቀለ ጉተማ ጀቤሳ (ፕሮፌሰር)፣ ጀይሉ ዑመር ሁሴን (ዶ/ር) እና ጣሰው ወልደ ሃና ካህሳይ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡
ቦርዱ ለመጨረሻ ውሳኔ ለትምህርት ሚኒስቴር ማቅረቡን የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመርያ መሠረት ለስድስት ዓመታት ዩኒቨርሲቲውን የሚመራ ፕሬዚዳንት ለመቅጠር ኅዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የወጣውን የቅጥር ማስታወቂያ በግልጽ ውድድር በማድረግ፣ ከኅዳር 16 ቀን ጀምሮ ፍላጎቱ ያላቸው 22 ምሁራን ከአገር ውስጥና ከውጭ ማመልከታቸው ይታወሳል፡፡
‹‹ፕሬዚዳንት መሆን ቢችሉ ምን ምን ሥራዎችን ለዩኒቨርሲቲው ይሠራሉ?›› የሚለው በስትራቴጂክ ዕቅድ ማስቀመጥ መሠረታዊው መሥፈርት በመሆኑ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ያቀረቡ ሲሆን፣ በቂ የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው ዘጠኙ እንዲቀነሱ መደረጉ፣ በቀሪዎቹ 13 ምሁራን ላይ በተደረገው የጥያቄና መልስ ክንውን መሠረት በተሰጠው ምዘናዊ ድምፅ ለፍፃሜ ግማሽ ያለፉት አምስቱ በቀለ ጉተማ (ፕሮፌሰር)፣ ጣሰው ወልደ ሃና (ፕሮፌሰር)፣ ጄይሉ ኡመር (ዶ/ር)፣ ማስረሻ ፈጠነ (ፕሮፌሰር) እና ፍቅሬ ደሳለኝ (ፕሮፌሰር) መሆናቸው መግለጹ ይታወሳል፡፡
ቦርዱ በሳምንቱ መገባደጃ ‹‹ምርጥ ናቸው›› ካላቸውና ለመጨረሻ ውሳኔ ለትምህርት ሚኒስቴር ከላካቸው ሦስቱ ፕሮፌሰር በቀለ፣ ፕሮፌሰር ጣሰውና ዶ/ር ጄይሉ መካከል ትምህርት ሚኒስቴር አንዱን መርጦ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትነት እንደሚመድብ ይጠበቃል፡፡
በ1943 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሚል መጠሪያ ከተቋቋመ በኋላ በሒደት ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተሸጋገረው ዩኒቨርሲቲው፣ ዘውዳዊ ሥርዓቱ በ1967 ዓ.ም. ሲያከትም ለአጭር ጊዜ ‹‹ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ›› ከተባለ በኋላ አሁን የያዘውን መጠርያ ይዞ ዘልቋል፡፡ በሰባት አሠርታት ጉዞውም 11 ፕሬዚዳንቶች እንዳስተዳደሩት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡